Wednesday, March 12, 2014

በሐረር ከተማ አንድ የገበያ ማዕከል በእሳት ቃጠሎ ወደመ

march12/2014

የተቃጠለው ንብረት ከአሥር ሚሊዮን ብር በላይ ተገምቷል

በሐረሪ ክልል ሐረር ከተማ ውስጥ በታችኛው ሸዋበር አካባቢ በሚገኘውና ‹‹መብራት ኃይል ግቢ የገበያ ማዕከል›› በሚል መጠሪያ የሚታወቀው የገበያ ማዕከል፣ የካቲት 30 ቀን 2006 ዓ.ም. ከምሽቱ 2፡35 ሰዓት ላይ መነሻው ባልታወቀ የእሳት አደጋ ሙሉ በሙሉ ተቃጥሎ መውደሙ ተጠቆመ፡፡

ከሦስት ዓመታት በፊት ‹‹በድንገት የተፈጠረ ነው›› በተባለ ተመሳሳይ ድንገተኛ የእሳት አደጋ ሙሉ በሙሉ መውደሙ ለሚታወሰው የሸዋበር የገበያ ማዕከል ተጐጂዎች፣ የክልሉ መንግሥት ‹‹ቋሚ የገበያ ማዕከል እስከሚገነባ ድረስ›› በሚል ከበፊቱ የገበያ ማዕከል ፊት ለፊት አስፓልት ተሻግሮ በሚገኘው የኤሌክትሪክ ኃይል ኮርፖሬሽን ይዞታ በሆነ ሰፊ ቦታ ላይ እንዲነግዱ ፈቅዶላቸው እንደነበር ይታወሳል፡፡

በወቅቱ ተጐጂ የነበሩ የከተማው ነዋሪ ነጋዴዎች ላለፉት ሦስት ዓመታት ሲነግዱ የክልሉ መንግሥት ዘመናዊ የሆነና ‹‹ደከር›› የተባለ የገበያ ማዕከል መገንባቱን በማስታወቅ ወደዚያ እንዲገቡ ሲወተውታቸው እንደነበር ጉዳቱ የደረሰባቸው አንዳንድ ነጋዴዎች ገልጸዋል፡፡

አዲስ የተገነባው የገበያ ማዕከል ከከተማው ወጣ ብሎ ገጠራማ ቦታ ላይ ስለሚገኝ ለገዥም ሆነ ለሻጭ የማያመች በመሆኑ፣ ሁሉም ነጋዴዎች አለመስማማታቸውን የገለጹት ተጐጂዎቹ፣ ድንገት ተነሳ የተባለው ቃጠሎ ምናልባት ሆን ተብሎ ቦታውን በዚህ አጋጣሚ ለማስለቀቅ የተደረገና የታሰበበት ሳይሆን እንደማይቀር መጠራጠራቸውን ገልጸዋል፡፡

የወደሙት ሱቆች ከ200 በላይ ሊሆኑ እንደሚችሉና ከአሥር ሚሊዮን ብር በላይ ግምት ይኖራቸዋል የሚሉት ነጋዴዎቹ፣ የተወሰነውን እንኳን ለማትረፍ በሚል የእሳት አደጋ ተሽከርካሪዎችን የጠሩ ቢሆንም፣ ውኃ ካለመኖሩም በተጨማሪ በወቅቱ ደረሱ የተባሉት የእሳት አደጋ ተሽከርካሪዎች የሚረጩት ውኃ እሳቱን ከማጥፋት ይልቅ ሲያባብስ በማየታቸው የሚረጨውን ፈሳሽም መጠራጠራቸውን ተናግረዋል፡፡

ቤተሰቦቻቸውን የሚረዱበት፣ ልጆቻቸውን የሚያስተምሩበትና ራሳቸውን የሚያስተዳድሩበት ንብረታቸው በእሳት እንደወደመባቸው ነጋዴዎች፣ መጋቢት 1 ቀን 2006 ዓ.ም.  ወደ ሐረር ከተማ ከንቲባ ቢሮ የሄዱ ቢሆንም ተስፋ የሚሰጥ ነገር ካለማግኘታቸውም በተጨማሪ፣ በፖሊስ እንዲበተኑ በመደረጋቸው በየጐዳናው ላይ ሲያለቅሱ መዋላቸውን ገልጸው፣ በየበረዳንው ላይ የተኙና የተወሰኑትም ራሳቸውን ስተው ወደ ሆስፒታል የገቡ መሆናቸውን አስረድተዋል፡፡

ከቃጠሎው የተረፈ ነገር ይኑር ወይም አይኑር ተጠግተው ማረጋገጥ ሳይችሉ የገበያ ማዕከሉ በግሬደር መታረሱን የገለጹት ተጐጂዎቹ፣ የክልሉ መንግሥት በገበያ ማዕከሉ ምን ያህል የንግድ ዕቃዎች ይንቀሳቀሱ እንደነበር ስለሚያውቅ፣ ቢያንስ ቢያንስ መቋቋሚያ የሚሆንና ሥራ የሚጀምሩበት ቦታና መነሻ ካፒታል ሊሰጣቸው እንደሚገባ ጠይቀዋል፡፡

ከሦስት ዓመታት በፊት የተቃጠለው የገበያ ማዕከል ያለምንም ግንባታ ታጥሮ መቀመጡን የገለጹት ነጋዴዎቹ፣ ቦታውን ለኢንቨስተሮች ለመስጠት አሁን የተቃጠለውም ለተመሳሳይ ጉዳይ ስለሚሆን የእነሱን ጉዳይ ለጊዜው እንጂ ግርግሩ ካለፈ በኋላ ዘወር ብሎ የሚያየው እንደሌለና ሥጋት እንደገባቸውም ገልጸዋል፡፡

በእሳት ቃጠሎ የወደመው የገበያ ማዕከል በአንድ በኩል ገደል በመሆኑ በርካታ ሌቦች ከእሳቱ ጋር እየተሻሙ ብዙ ንብረቶችን መዝረፋቸው በመታወቁ፣ ፖሊስ በርካቶቹን በቁጥጥር ሥር አውሎ የተወሰነ ዕቃ እያስመለሰ ቢሆንም፣ የትኛው ዕቃ የማን እንደሆነ መለየት ስለማይቻል ከመወረስ ያለፈ ፋይዳ እንደሌለው ነጋዴዎቹ ገልጸዋል፡፡

በሐረር ከተማ የታችኛው ሸዋበር መብራት ኃይል የገበያ ማዕከል የካቲት 30 ቀን 2006 ዓ.ም. ምሽት ላይ በደረሰው የእሳት ቃጠሎ ወደሙ ስለተባሉት ሱቆች ማብራሪያ እንዲሰጡ የክልሉ ማዘጋጃ ቤት፣ ፖሊስና የሚመለከተው አካልን ለማግኘት የተደረገው ጥረት ‹‹ስብሰባ ላይ ናቸው›› በሚል ምላሽ አልተሳካልንም፡፡ በሐረር ከተማ በታዋቂው የጀጐል ግንብ ውስጥ የሚገኘው ‘መጋላ ጉዶ’ ባህላዊ የገበያ ማዕከልና ሌሎች ከትናንሽ የባህል ገበያዎች መኖራቸው ይታወቃል፡፡ የካቲት 30 ቀን 2006 ዓ.ም. የተቃጠለው የታችኛው ሸዋበር መብራ ኃይል የገበያ ማዕከል ግን በኮንትሮባንድ የሚገቡ ትላልቅና አነስተኛ ዘመናዊ የኤሌክትሮኒክስ ዕቃዎች፣ ልብሶችና ሌሎችም ሸቀጣ ሸቀጦች የሚገኙበት ታዋቂ ገበያ መሆኑንም ነጋዴዎቹ አውስተዋል፡፡

በሐረር ከተማ የገበያ ማዕከል ላይ የደረሰውን የእሳት ቃጠሎ በሚመለከት የኢትዮጵያውያን ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኢዴፓ) መግለጫ አውጥቷል፡፡ የክልሉ መንግሥት የእሳት ቃጠሎ የደረሰባቸውን ወገኖች ማፅናናት ሲገባው በተቻኮለና በተመሳሳይ ቀን የተቃጠለውን የገበያ ማዕከል በግሬደር ማረሱን ተቃውሟል፡፡ ችግሩን ቆም ብሎ በማሰብ ሌላ ጉዳት እንዳይደርስ መጠንቀቅና መፍትሔ መስጠት እንዳለበትም ኢዴፓ አሳስቧል፡፡

No comments:

Post a Comment