March 14, 2014
ከኢየሩሳሌም አርአያ
የሕወሐት አባል የሆነውና በአሜሪካ የሚኖረው ብስራት አማረ በርካታ ወንጀሎችን እንደፈፀመ የቅርብ ምንጮች አጋለጡ። ሕወሐት በረሃ እያለ የባዶ 6 እስር ቤት ዋና ሃላፊ የነበረው ብስራት አማረ የኢ.ህ.አ.ፓ አባላት የነበሩት እነ ፀጋዬ ገ/መድህን (ደብተራው) ጨምሮ በሕወሐት የተያዙትን በሙሉ ወረኢ ተብሎ በሚጠራው ስፍራ በነበረ እስር ቤት በጅምላ አሰቃይቶ እንደገደላቸው ምንጮቹ አረጋግጠዋል። በሺህ የሚቆጠሩ የትግራይ ሰዎች « ኢዲዩና ፊውዳል..» በሚል ባዶ 6 ተብሎ ይጠራ በነበረው እስር ቤት ተሰቃይተው እንዲገደሉ የተደረጉት በብስራት አማረ መሆኑን የጠቆሙት ምንጮቹ ከዚህ በተጨማሪ የድርጅቱን በርካታ አባላት እንዳስገደለ አያይዘው ገልፀዋል። እነተክሉ ሃዋዝ በዚህ ወንጀለኛ ከተገደሉት ይጠቀሳሉ ሲሉ ያክላሉ። በ1983ዓ.ም ሕወሐት/ኢህአዴግ አገሪቱን ከተቆጣጠረ በኋላ የሟቹ የደህንነት ሹም ክንፈ ገ/መድህን ምክትል የነበረው ብስራት አማረ ከቤተ መንግስት የጃንሆይ የነበረ ከፍተኛ ወርቅ በመዝረፍ መውሰዱን ያጋለጡት ምንጮቹ በዚህ የዘረፋ ወንጀል ሆለታ እስር ቤት እንዲገባ መደረጉን ያመለክታሉ። በነስብሃት ነጋና መለስ ዜናዊ ትእዛዝ እንዲፈታ ተደርጐ ወደ አሜሪካ የተሸኘው ብስራት አሜሪካ ሲጓዝ የዘረፈውን ወርቅ ይዞ እንደነበረ ጉዳዩን በቅርብ የሚያውቁ ምንጮች በግርምት ይገልፃሉ። ብስራት አማረ አሜሪካ ከመጣ በኋላ ቅርስ የሆኑትንና የዘረፋቸውን ወርቆች መሸጡንና አንዲት ሴት ለማሻሻጥ የተቀበለችውን 1ኪሎ ወርቅ ከወሰደች በኋላ እንደካደችው ማወቅ ተችሎዋል። ብስራት አማረ ስለዚሁ ጉዳይ ተበሳጭቶ የነገራቸው ምንጮች ማረጋገጫ ይሰጣሉ። የብስራት ታናሽ ወንድም የሆነውና በደህንነት ቢሮ ይሰራ የነበረው ታጋይ ጠስሚ (ጠስሚ -ትርጉሙ ቅቤ ማለት ነው) ከስራው በመልቀቅ የአስመጪና ላኪነት ትልቅ ቢዝነስ መክፈቱን የጠቆሙት ምንጮቹ አክለውም፥ ድርጅቱ የተከፈተው ብስራት አሜሪካ ከገባ በኋላ በላከለት ገንዘብ መሆኑን አስታውቀዋል። (ስለዚሁ ጉዳይ በ1995 ዓ.ም በኢትኦጵ ጋዜጣ መረጃው ይፋ መደረጉና የብስራት ወንድም ቅቤ ኢትኦጵ ቢሮ ድረስ በመምጣት የጋዜጣውን አዘጋጅ በድንጋጤ ተውጦ “የራሴን ቢዝነስ ተቋም ነው፤ እነማን መረጃ እንደሚሰጧችሁ አውቃለሁ። እባካችሁ የእኔንም፣ የወንድሜንም ስም አታንሱ?” በማለት ተማጽኖ አቅርቦ ነበር።) ብስራት አማረ ከሽማግሌው ስብሃት ነጋ ጋር ባለው የጠበቀ ግንኙነት ወደ ኢትዮጵያ ሲመላለስ መቆየቱን ያወሱት ምንጮቹ፣ ወንጀለኛውና ዘራፊው መቀሌ ሄዶ አስገደ ገ/ስላሴን እንደከሰሰ አስታውቀዋል። የደርግ ወንጀለኞች ከአሜሪካ በገዢው ፓርቲ እየተወሰዱ ነገር ግን የኢ.ህ.አ.ፓ አባላትንና ሌሎች ንጹሃን ዜጎችን በጅምላ የፈጀና የአገር ቅርስ የዘረፈ ወንጀለኛ ጠያቂ ማጣቱ አስገራሚ ነው ብለዋል ምንጮቹ። ጠያቂ አካል ካለ በወንጀለኛው ብስራት አማረ ላይ ለመመስከር ፈቃደኛ መሆናቸውን አክለዋል። ይህን ምስክርነትና ማረጋገጫ ሊሰጡ የሚችሉና በአሜሪካ የሚኖሩ ሶስት የቀድሞ የሕወሐት ሹሞች እንዳሉና የብስራትን ወንጀል ጠንቅቀው የሚያውቁ መኖራቸውን አያይዘው ጠቁመዋል።
No comments:
Post a Comment