Monday, March 24, 2014

የሽረ ባጃጆች አድማ መቱ: መንግስትም አገደ

March 24/2014

አብርሃ ደስታ ከመቀሌ

የሽረ እንዳስላሴ ከተማ ባለስልጣናት ከ450-500 የሚሆኑ የባጃጅ ሹፌሮች ሰብስበው ኩንትራት (ኮንትራክት) እየጫናቹ ነው፤ መንግስት የማይፈልገውን አገልግሎት እየሰጣቹ ነው በሚል ሰበብ ማስፈራራታቸው ተከትሎ የባጃጅ ሹፌሮች የስራ ማቆም አድማ በማድረግ ባጃጆቹ ከከተማ ዉጭ በማስቆም ተቃውሞአቸውን እየገለፁ ይገኛሉ። የመንግስት አካላትም አድማው ተከትሎ ባለባጃጆቹ መንግስት ባዘዛቸው መሰረት ለመስራት ፍቃደኛ ካልሆኑ ፍቃድ እንደማይሰጣቸው በመግለፅ እንዳይንቀሳቀሱ አግዷቸዋል። አሁን ባለባጃጆቹ አድማ ላይ ናቸው፤ መንግስትም አግዷቸዋል። በከተማው ምንም የባጃጅ እንቅስቃሴ አይታይም።

ብዙ የከተማው ኗሪዎች ታክሲ አጥተው በመንግስት አካላት ላይ ጫና በመፍጠራቸው ባለስልጣናቱ አምስት ሚኒባሶች ከመነሃርያ የታክሲ አገልግሎት እንዲሰጡ ቢያዙም ህዝቡ በቂ አገልግሎት ማግኘት አልቻለም። ባለ ባጃጆቹ መንግስት መፍትሔ ካልሰጣቸው ሰለማዊ ሰልፍ እንደሚወጡ ለዓረና ፅሕፈትቤት (የሽረ ከተማ ቢሮ) አስታውቀዋል። ከወር በፊት በመቐለ ከተማ ተመሳሳይ ችግር እንደነበር ይታወቃል።
በሌላ ዜና ዓረና ከሀገረሰላም ህዝብ ጋ ተወያየ።
ትናንት እሁድ (መጋቢት 14, 2006 ዓም) ዓረና ፓርቲ በደጉዓ ተምቤን ወረዳ ሀገረሰላም ከተማ ህዝባዊ ስብሰባ አካሂደዋል። ለእሁዱ ስብሰባ ቅዳሜ ቅስቀሳ የተደረገ ሲሆን የሀገረሰላም ህዝብ በጥሩ ሁኔታ ተቀብሎናል።
የህዝቡን ስሜት ያስደነገጣቸው ባለስልጣናት የከተማው ወጣቶች ሰብስበው በስድስት መኪኖች ጭነው ስልጠና አለ፣ ስራ ይሰጣችኋል፣ አበል ይሰጣችኋል ወዘተ በማለት ሕዋነ ወደሚባል ከተማ ሲያጓጉዟቸው አመሹ። ሌሊትም ቁጥራቸው በዉል ያልታወቁ ወጣቶች ሲጓጓዙ አደሩ። ቁጥራቸው ያልታወቀ ወጣቶችም ቅዳሜ ማታ በፖሊሶች እየታደኑ ታስረዋል፤ የዓረና ስብሰባ እስኪጠናንቀቅ ድረስ። ጥረቱ ግልፅ ነበር። ወጣቶቹ በዓረና ስብሰባ እንዳይሳተፉና በአባልነት እንዳይመዘገቡ ለማራቅ ነው፤ ዓረና ከወጣቶች ጋር እንዳይገናኝ ለማድረግ ነው። በብዙ አከባቢዎች በዓረና ስብሰባ የሚሳተፉ ወጣቶች ናቸውና።

ወጣቶቹ ከከተማ በመውጣታቸው ምክንያት የስብሰባው ተሳታፊ ብዙ አልነበረም። ነገር ግን ከብዙ የገጠር ጣብያዎች የተወከሉ አርሶአደሮች፣ መምህራንና የተመሪዎች ተወካዮች ነበሩ። እናም ስብሰባው የተሳካ ነበር ማለት ይቻላል።
አንዳንድ የህወሓት ካድሬዎች (የከተማው የካቢኔ አባላት) በዓረና አባላት ላይ ችግር ለመፍጠር ሞክረው ነበር። አልጋ እንዳንይዝ ባለሆቴሎችን ያስፈራሩ ነበር፣ በአንዳንድ አባሎቻችንም አክታ የመትፋትና የመሳደብ እንዲሁም ለመረበሽ ጥረት ሲያደርጉ ነበር። ግን እነዚህ ተግባራት የፈፀሙ የከተማው የካቢኔ ሐላፊዎች በተናጠል (በግል) የሰሩት እንጂ እንደ የዓዲግራቱ ቀውስ ሆን ተብሎ በፓርቲ ደረጃ የተፈፀመ አልነበረም። ምክንያቱም በሀገረሰላም ካድሬዎች ችግር ሲፈጥሩ ፖሊስ ያስቁመው ነበር። በዓዲግራት ግን ፖሊስ የችግሩ ተሳታፊ ነበረ።
እሁድ ጧት ስብሰባ የጠራንበት የከተማው ማዘጋጃቤት በፖሊሶችና ካድሬዎች ተከቦ ለስብሰባ የመጣ ህዝብ ለማስፈራራት ጥረት ተደርጓል። ብዙዎች እንዲመለሱ ተደርጓል። ባጠቃላይ የህወሓት ባለስልጣናት በዓረና አባላት ላይ ይፈፅሙት የነበረ ግፍ ወደ ተሰብሳቢው ህዝብ አሸጋግረውታል።

አሁን ጥቃት የሚፈፀመው በዓረናዎች ሳይሆን ጥያቄ በሚያነሳና በዓረና ስብሰባ ለመሳተፍ ፍላጎት ባለው ሰለማዊ ህዝብ ላይ ነው። የህዝብ የመሰብሰብ መብት እየጣሱ ነው ማለት ነው። የደጉዓ ተምቤን ህዝብ ለውጥ እንደሚፈልግ አረጋግጦልናል።

No comments:

Post a Comment