Monday, March 24, 2014

ኑ! እንዋቀስ፤ ኢህአዴግንም እናፍርሰው! (ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ)

March 24/2014

(ይህ “ኑ! እንዋቀስ” የሚለው ስር ነቀል የለውጥ ጥሪ ቀጥታ የሚያነጣጥረው በኢህአዴግ አባላት ላይ ብቻ ነው፤ አመራሩን በፍፁም አይመለከትም)
ኢህአዴግ ራሱ በይፋ ሲናገር እንደተደመጠው፣ በአሁኑ ጊዜ የአባላቱ ቁጥር ወደ ሰባት ሚሊዮን ገደማ ደርሷል፡፡ ይህም የአገሪቱ ቁጥር አንድ ግዙፍ የፖለቲካ ፓርቲ ያደርገዋል፡፡ በርግጥ ግዙፍ እንጂ ጠንካራ እንዳላልኩ ልብ ይሏል፡፡ ምክንያቱም ጥንካሬ የሚለካው በአባላት ቁጥር ሳይሆን በድርጅት ፍቅር፣በዓላማ ፅናትና በሚሰጡት ልባዊ አበርክቶ ነው፡፡ እንዲህ ያለ አቋመ-ብርቱነት ደግሞ ድሮ በያ ትውልድ ጊዜ ቀርቷል፡፡ በዘመነ-ኢህአዴግ የተንሰራፋው ጥቅመኝነት (በእነርሱ ቋንቋ ኪራይ ሰብሳቢነት) ብቻ ነው፡፡ ለዚህም በደቡባዊቷ አዋሳ ከተማ ስድስተኛው የድርጅቱ ጉባኤ በተካሄደበት ወቅት፣ አቶ በረከት ስምኦን በብስጭት እየተትከነከነ በደፈናው ለጥቅም ድርጅቱን የተቀላቀሉ አባላት በርካታ መሆናቸውን አምኖ በአደባባይ መናገሩ አስረጂ ሊሆነን ይችላል፡፡ ይህን ንግግሩንም አፍታተን ስናብራራው እንደሚከተለው ሆኖ እናገኘዋለን፡- የግንባሩ አባላት ቁጥር ሰባት ሚሊዮን ገደማ የደረሰው በጥቅም በመደለል፣ በአንድ ለአምስት የጥርነፋ መዋቅር በፍርሃት ተጠፍንጎ በመያዙና በመሳሰሉት ነው (መቼስ አቶ በረከት ከድርጅቱ ጉምቱ መሪዎቹ አንዱ ነውና ዘርዝሮ እንዲያስረዳን
አይጠበቅበትም 


የሆነው ሆኖ አባላቱ እንዲህ የመብዛታቸው ምስጢር የድርጅቱ አምባ-ገነንነት ባህሪይ መገለጫ እንጂ አመላይ አጀንዳ አሊያም
ምትሀታዊ ችሎታ እንዳለው የሚያሳይ አይደለም፡፡ ይህ የትኛውም መሰል ሥርዓት ከተጠናወተው ሁሉንም ከመቆጣጠርና መጠቅለል
(Totalitarianism) አስተሳሰብ የሚሰርፅ ማኪያቬሊያዊ አስተምህሮ ነው፡፡ የሆነው ሆኖ ‹‹አምባገነኖች የአንድ እናት መንትያ ልጆች
ናቸው›› እንዲሉ፤ በ‹‹ቆራጡ መሪ›› ዘመነ-መንግስትም በጊዜው ከነበረው የሀገሪቱ ሕዝብ ቁጥር አኳያ መሳ-ለመሳ ሊባል በሚያስደፍር
ሁኔታ ሳር ቅጠሉ ሁሉ ሰማያዊ ካኪ ለባሽ የኢሠፓ አባል ሆኖ ነበር፡፡ ግና፣ ያ ካኪ ለባሽ ሕዝብ፣ የልቡን በልቡ ይዞ ‹‹ቪቫ መንጌ!›› እያለ
አሳስቆ በስተመጨረሻ ጉድ እንደሰራው ሁሉ፤ ‹‹ይህ የህዝብ ማዕበል…›› ተብሎ በአቶ መለስ ዜናዊ የተሞካሸው የ97ቱ የቅዳሜው መሬት
አንቀጥቅጥ የሰልፍ ትዕይንትም፣ በድጋፍ ሳይሆን በግዳጅ የሰመረ መሆኑን ለማየት፤ አይቶም ለመመስከር ከሃያ አራት ሰአት ጊዜ በላይ
አልወሰደብንም፡፡ እንዴት? ቢሉ በማግስቱ (ሚያዚያ 30) ለተቃውሞ ከወጣው ሕዝብ የቅዳሜዎቹም በብዛት መሳተፋቸውን በራሳቸው
አንደበት ‹‹ትላንት ለቲሸርት፤ ዛሬ ለነፃነት!›› በሚል ሕብረ-ዝማሬ ከአደባባዩም አልፎ ከተማዋን በሚያናውፅ የለውጥ ጩኸት
የመሰከሩበት ‹‹ፖለቲካ›› መቼም ቢሆን አይዘነጋምና፡፡

እንግዲህ ይህ ሁሉ ታሪካዊ ሀቅ የሚገልፅልን አንድ ታላቅ እውነት-በጥቅም እየደለሉ አባልን ማብዛት በክፉ ቀን የማይታደግ መሆኑን ነው፡
፡ ጥቅመኝነት ግፋ ቢል የአብዮታዊ ዲሞክራሲ ‹‹ፀበል›› ያስጠምቅ፣ ‹ኢህአዴግ ጌታ ነው!›ን ያስፎክር ያሸልል ይሆናል እንጂ
የኢትዮጵያን ትንሳኤ መሻትን አያስቀይርም፡፡ ነብር ዥንጉርጉርነቱን እንደማይለውጠው ሁሉ የኢህአዴግ አባላትም ምንም ቢሆን ምን፣
እንደሌላው ሕዝብ የሀገር አንድነት የሚያሳስባቸው፣ ብሔራዊ ውርደት (ረሀብተኝነት) በቁጭት የሚያንገበግባቸው፣ ከዘውግ ልዩነት
የሕዝብ ለሕዝብ መተማመንና አንድነታዊ ጥንካሬው የሚበልጥባቸው፣ የኃይማኖት ነፃነት የሚያስተቃቅፋቸው… ናቸው ብዬ አምናለሁ፡፡
ምክንያቱም ጥቅመኝነት የእጦትን ክፍተት ለመሙላት ለጊዜው ያሰግዳል እንጂ ክብርንና ማንነትን አስሽጦ በባርነት ቀንበር አያሳድርም-
በተለይም ዥንጉርጉርነቱን ጠንቅቆ ለሚያውቀው ኩሩ-ሀበሻ! 

ደግሞስ ምን ያህሉ አባል ነው፣ የድርጅቱን መታወቂያ በመያዙ ብቻ የረባ ጥቅም ያገኘው? በግላጭ እንደሚታየው በግል ጥቅምም ሆነ በተጭበረበረው የዘውግ ፖለቲካ ሳቢያ ኢህአዴግን የተቀላቀሉ የአብዛኞቹ አባላት የኑሮ ደረጃ ዛሬም እንደ ብዙሃኑ የኢትዮጵያ ህዝብ ከችግር የመቆራመድ አስከፊ ሕይወት አልተላቀቀም፡፡ ፓርቲውን መታከካቸውም በማይጨበጥና በማይታይ እንቅልፍ የለሽ ሕልም አናውዞ ይበልጥ ደቁሷቸዋል እንጂ በቀን ሶስቴ መመገብ እንኳ አላስቻላቸውም፡፡ ሌላው ቀርቶ የድርጅት አባልነታቸው እንደተርታው ሕዝብ በአድሎአዊ አሰራር መማረርን እንዳላስቀረላቸው በርግጠኝነት መመስከር ይቻላል፡፡

ይህ አይነቱም እርግጠኝነት ነው ‹ኑ! እንወቃቀስ (እንነጋገር)፤ እንተማመንምና ሀገርና ትውልድ እየገደለ ያለውን ፓርቲያችሁን አብረን
ተጋግዘን እናፍርሰው› የሚል የማንቂያ ደውል ላሰማችሁ ገፊ-ምክንያት የሆነኝ፡፡ እናም ድርጅታችሁን ትመረምሩ ዘንድ ወደድኩ፡-
ድርጅታችሁ ሥልጣን ላይ ተፈናጥጦ ባሳለፋቸው ሁለት አስርታት የተጓዘበትን መንገድ በአስተውሎት ብትመረምሩ፤ በእርግጠኝነት እንደ
ግዙፍ ዐለት ካገጠጡ ሀገራዊ ውድመቶች እና ከበባድ ኪሳራዎች ጋር መፋጠጣችሁ አይቀሬ ነው፡፡ ይህም ሆኖ በቅድሚያ በተልካሻ
ፕሮፓጋንዳ ያሰለቸንን የብሔር ጉዳይ (የተወሰኑ ሰዎችን አማልሎ አባል ለማድረግ አስተዋፆ እንዳለው ባይካድም) ወደጎን ብለን፤
የትኛውም ብሔረሰብ ባህላዊ እሴቶቹን ማክበር፣ በአፍ መፍቻ ቋንቋው መጠቀም… የፖለቲካ ፓርቲ በችሮታ የሚሰጠው ሳይሆን፣
የማንም ተፈጥሮአዊ መብት መሆኑን ማስረገጥ አስፈላጊ ይመስለኛል፡፡ ይህ ማለት ግን የድርጅታችሁ ሀቲት፡- ‹አንዱ በሌላው እድሜውን
ሙሉ ሲጨቆን እንደኖረ፤ ከተቀረው የኢትዮጵያ ሕዝብ የተለየ እንደሆነ፤ ከብሔራዊ ሰንደቅ ዓላማችን ይልቅ የክልሉን እንዲያስቀድም
መቀስቀስና መስበክን የብሔር ብሔረሰብ መብትን ማክበር ነው› የሚለውን አምኖ መቀበል አይደለም፡፡ በግልባጩ ስርዓቱ እንዲህ አይነት
ጉዳዮችን ሰማይ ጥግ አጉኖ፣ ሕዝብን ከፋፍሎና በጥርጣሬ (በጎሪጥ) ወደሚተያይበት ጠርዝ ገፍቶ፣ የሥልጣን ዕድሜውን ያራዘመበት
ሁለት አስርታትን ያሳለፈ ስልቱ መሆኑን መረዳት አይሳናችሁም ብዬ አስባለሁ፡፡

ሌላ ሌላውን ትተን እንኳ የኢህአዴግን አመሰራረት ብንመለከት ግንባሩን ከፈጠሩት አራቱ ድርጅቶች መካከል ከሞላ ጎደል ህወሓት እና
ኢህዴን/ብአዴንን እንደ ፖለቲካ ድርጅት መውሰድ ይቻል ይሆናል እንጂ፤ ኦህዴድና ደኢህዴን፣ በህወሓት ‹‹አባ መላ››ዎች እንደ
የፋብሪካ ሳሙና በሚፈለጉበት መጠንና ቅርፅ ተጠፍጥፈው ከተሰሩ በኋላ በኦሮሞና በደቡብ ኢትዮጵያ ተወላጆች ላይ እንደ አለቅት
የተጣበቁ የመሆናቸውን ምስጢር እነርሱም ራሳቸው የሚክዱት አይመስለኝም (ምናልባት በሽግግሩ የመጀመሪያ ዓመት ላይ
እንደአስተዋልነው ከኦህዴድ ይልቅ፣ ኦነግ ኦሮሚኛ ተናጋሪዎችን ወክሎ ቢቀጥል ኖሮ ይህ ጉዳይ በዚህ አውድ ላይነሳ ይችል ነበር፡፡ የሆነው
ግን ተቃራኒው ነው፤ የራሱ የፖለቲካ ቁመናና ራዕይ የነበረው በኃይል ተገፍቶ፤ በምትኩ በሌሎች እስትንፋስ ህልው ሆኖ
‹‹የሚያስተዳድረው››ን ሕዝብና ራሱንም ጭምር ቀን ከሌት ‹‹ከብሔር ጭቆና ነፃ አወጣናችሁ›› ስለሚሉት ሞግዚቶቹ ገድል መተረክን
‹‹ፖለቲከኛነት›› አድርጎ የወሰደው ኦህዴድን ያነገሰ ነውና)

በነገራችን ላይ የፖለቲካ ፓርቲን እንደ ፋብሪካ ምርት ጣጣ-ፈንጣጣው ተጠናቅቆለት ሲያበቃ የመጫኑ አሰራር በሁለቱ ክልሎች ብቻ
ተገድቦ የቀረ አይደለም፤ አጋር ፓርቲዎችንም ይመለከታል፡፡ ከአፋር እስከ ጋምቤላ እና ቤንሻንጉል፤ ከሀረር እስከ ሶማሌ ሲተገበር
በትዝብት የተመለከትነው ጉዳይ ነው፡፡ መቼም ገና ከስር መሰረቱ ‹‹እኛ እናውቅልሀለን!›› በሚሉ ‹‹የፖለቲካ ሞግዚቶች›› የተፈጠረ
ድርጅት በምደባ ቦታውን ያገኙ የአመራር አባላቱን በቅምጥል ኑሮ ከማንፈላሰስ በዘለለ፣ ‹‹እወክለዋለሁ›› ለሚለው ሕብረተሰብ ትርጉም
ያለው ስራ ይሰራል ተብሎ የሚታሰብ አይደለምና ‹በኦሮሚያ ሙስና እንደሰላምታ እጅ መጨባበጥ ተዘውታሪና ተራ ነገር ነው›፣ ‹በአፋር
ባጀት መቀለጃ ሆኗል›፣ ‹በሐረር ቤተሰባዊ ኢምፓየር ተገንብቷል›፣ ‹ቤንሻንጉል በድህነት ማቀቀ›፣ ‹ሶማሌ ክልል የአስተዳዳሪው አብዲ
ርስተ-ጉልት ሆነ› ጂኒ ቁልቋል እያሉ ሮሮዎችን ማሰማት ለውጥ አያመጣም፡፡ ምክንያቱም እነዚህ ህወሓትን እንደ ‹‹ግል አዳኝ››
በመቀበላቸው ብቻ ‹‹የአስተዳዳሪነት›› ካባ የተደረበላቸው ምስኪን የአመራር አባላት በቀላል ጉዳይ ላይ እንኳ የመወሰን ሥልጣን
የላቸውምና ነው፡፡

ይህ እንግዲህ በቀጥታ ከኢህአዴግ ስነ-ተፈጥሮ ጋር የሚጋመድ ችግር ነው፡፡ ሆኖም የመንግስት ሥልጣን መዘውር ከጨበጠ በኋላ
የጨፈለቃቸውን የዴሞክራሲና ሰብዓዊ መብቶች ተከትሎ በሁሉም የሀገሪቱ አካባቢዎች የደረሱ የአያሌ ሰላማዊ ዜጐች ግድያ፣ እመቃ፣
ከስራና ቤት ንብረት መፈናቀል፣ ስደትን… አንድ በአንድ ጠቅሰን ለማውገዝ ብንሞክር ሰማይ-ብራና፣ ቀይ ባህር-ቀለም ሆነው
ካልተመቻቹልን በቀር የሚደፈር አይመስለኝም፡፡ በርግጥ በኢህአዴግ ውስጥ ታላቅና ታናሽ ንጉሠ-ነገሥት የሆኑት ህወሓትና ብአዴን
ብረት ነክሰው፣ ሳንጃ ወድረው በትጥቅ ትግል ያለፉ ከመሆናቸው አኳያ ለየትኛውም አይነት ቅራኔም ሆነ ልዩነት ከመግደልና መጋደል
ውጪ ያለ ሌላ ሰላማዊ አማራጭ ላይዋጥላቸው እንደሚችል መዘንጋት የለበትም፡፡ ኦነግ ከሽግግር መንግስቱ ከተገፋበት ጊዜ አንስቶ
በኦሮሚያ፣ በአዋሳ፣ በሶማሌ… ግፉአን ያለቁበትን፤ እንዲሁም በድህረ-ምርጫ 97 የታየው የጎዳና ላይ ጭፍጨፋ ይህንኑ ሀቅ ያስረግጣሉ፡፡
ኩነቱም ግንባሩ በመጣበት አይነት የነፍጥ የበላይነት ያለፉት ሶቪየት ህብረት፣ ቻይና፣ ቬትናም፣ ኩባ፣ ኤርትራ ባሉ ሀገራት ከታየው
የሕዝቦች እልቂት፣ የተቀናቃኝ ድምፆች መታፈን፣ የጋዜጠኞች መጨፍለቅ… ጋር ቀጥታ ዝምድና አለው፡፡ እነዚህ ሀገራትንም ሆነ
ኢህአዴግን የተለየ ሃሳብ ለማስተናገድ ትዕግስቱም ፍላጎቱም እንዳይኖራቸው ያደረገው ይህ ከውልደታቸው ጀምሮ ከደም-አጥንታቸው
ጋር የተዋሃደው ተፈጥሮአቸው ይመስለኛል፡፡

በአናቱም ኢህአዴግ ከአባላቱ ይልቅ የአመራሩ ‹‹ፓርቲ›› ብቻ ስለመሆኑ ለመረዳት የውስጥ አሰራሩን መፈትሽ የተሻለ ይሆናል፤
እናንተም በቅርበት እንደምታውቁት በድርጅቱ ያልተፃፈ ሕግ ከላይ ወደታች የሚወርድ መመሪያን ትክክል ሆነም አልሆነ ‹‹ለምን?›› ብሎ
መጠየቅ የሚያስቀስፍ ሀጢያት ነው፡፡ በዴሞክራሲያዊ መንገድ ለመወያየት መሻት፣ ጥያቄ ማቅረብ፣ ሃሳብን መቃወም፣ ስህተቶችን
ማጋለጥ… አሳድዶ በድንጋይ የሚያስወግር አሊያም ከሀገር ሀገር የሚያሰድድ ታላቅ ጥፋት ተደርጎ ይቆጠራል፡፡ ይህ ሁናቴም ነው
የአስተዳደር ድክመቶቹንም ሆነ አውዳሚ ጉድለቶቹን በፍጹም ለሕዝብ እንዳይደርሱ ገትሮ መያዝን የማይዘናጋበት ዋነኛ መንግስታዊ ስራ
ያደረገው (የነፃው ፕሬስ ጋዜጠኞችን እና የተቃዋሚ ፓርቲ አባላትን በውሃ ቀጠነ ወደ እስር ቤት ሲያግዝ መክረሙን ልብ ይሏል)
በጥቅሉ ድርጅቱ ለአመራሮቹ ከ4 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ በተደረገባቸው ዘመናዊ “V8” መኪናዎች እንዲምነሸነሹ እና በቢሊዮን
የሚቆጠር የሀገር ሀብት እንዲዘርፉ የሚያስችል ስልጣን ከማጎናፀፉ ባለፈ፤ እናንተ (ብዙሀኑ አባላት) ያተረፋችሁት ምንድር ነው?
በአነስተኛና ጥቃቅን ከመደራጀት፣ ‹‹ኮብል-ስቶን›› ፈልጦ ከመደርደር የዘለለስ ማን ምን ሊጠቅስ ይችላል? እስቲ! የተራቆተችና በድህነት
ወጀብ የተንገላታች ሀገራችሁን በዓይነ-ልቦናችሁ ለማስተዋል ሞክሩ፡፡ ያን ጊዜም ገና ጀንበር ስታዘቀዝቅ ስጋቸውን ለመቸርቸር ጎዳናዎችን
የሚያጥለቀልቁ እምቦቀቅላ እህቶቻችን፣ ‹‹ማምሻም ዕድሜ ነው›› እንዲሉ የመፅዋች ዓይን እየገረፋቸው በልመና ቁራሽ ሕይወታቸውን
ለማቆየት የሚውተረተሩ አዛውንትና ህፃናት፣ በየጎዳናው በየሰፈሩ ሲንገላወዱ የሚውሉ ስራ-አጥ ወጣቶች፣ በቀን አንዴ ለመመገብ ላይ
ታች የሚማስኑ ለፍቶ አዳሪዎች… ምድሪቷን እንዳጨናነቋት ይገለፅላችኋል፡፡ የዚህ ሁሉ መንስኤም የፈጣሪ ቁጣ ሳይሆን ፅንፈኛው
ድርጅታችሁ በሚከተለው በተግባር ያልተፈተነ (የሀገሪቱን ተጨባጭ እውነት ያላገናዘበ) ርዕዮተ-ዓለም፣ ፖሊሲ፣ አድሎአዊ አሰራር፣
ሙስና እና ለኃላፊነት የማይመጥኑ ‹‹አስፈፃሚዎች›› ችግር ስለመሆኑ ለአፍታም ቢሆን ጥርጣሬ አይግባችሁ፡፡ እናም ጉዳዩ የሀገር ነውና
በግልፅ እንወቃቀስ (እንነጋገር)፤ ስለምንድነው በአባልነት በምታገለግሉት ኢህአዴግ የሚመራው መንግስት ‹ዛሬም በስኬት ጎዳና
እየጋለብኩኝ ነው› ብሎ እንደ ቁራ እየለፈፈ በተግባር ግን፡- መብራት፣ ውሃ፣ መንገድ፣ ኔት-ወርክ እንደ አደይ አበባ በዓመት አንዴ ብቻ
ብቅ የሚለው? በአገልግሎት ተቋማት መጠቀምስ እንዲህ የአሲምባን ያህል ያራቀው ማን ነው? ፍትሕን የጠሉትን መበቀያ መሳሪያ
አድርገው ያረከሱት እነማን ናቸው? ሰርቶ መብላት የማይጨበጥ ጉም የሆነብንስ በማን የተነሳ ነው? …በርግጥ ይህንን ጥያቄ ለጠቅላይ
ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ብናቀርብለት እንደ መለስ ዜናዊ በተረት መሳለቁ ባይሆንለትም፣ ‹‹ሰለሜ ሰለሜ››ን እየጨፈረ፤
እነ‹‹ሚካኤል ስሁል›› በቀደዱለት ልክ ዳናኪራውን እያስነካው ‹‹ሰው በእንጀራ ብቻ አይኖርም!›› ብሎ ከመዘባበት አይመለስም፡፡
መቼስ እንደዚህ ሕዝብ የተናቀ የትም አይገኝም፡፡

ኢህአዴግ መፍረስ ያለበት ለምንድን ነው?

ይህንን አጀንዳ ለማንሳት መግፍኤ የሆነው ከላይ ለማሳያ ያህል የተጠቀሱት ስርዓታዊ ጥፋቶች በግላጭ የመታየታቸው እውነታ ብቻ
አይደለም፤ ይልቁንም ድርጅቱ ከስሁት መንገዱ ለመታረም (ለመታደስ) ፍፁም ዝግ-በር የመሆኑ ጉዳይ ጭምርም ነው፡፡ አዎን፣ እነዚህ
አሁን ሁላችንንም እያማረሩ ያሉ አብዛኞቹ ችግሮች የተከሰቱት አንጋፋው ድርጅታችሁ የ‹‹ኢትዮጵያ ሕዝብ አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ
ግንባር›› የሥልጣን መሰረቱን ለማፅናት ይሁነኝ ብሎ ከደፈጠጣቸው መብቶች ጋር ተያይዘው ከመሆናቸው በዘለለ ለኢኮኖሚያዊ
ጥያቄዎች በቂ ምላሽም ሆነ ሁነኛ መፍትሔ የሌለው ፀረ-ሕዝብነቱ የተረጋገጠ፣ ለመታረም ዝግጁ ያልሆነ፣ ተስፋችንን ያሟጠጠ ስርዓት
ስለሆነም ነው፡፡ በ1970ዎቹ መጀመሪያ እነበረከት ስምኦን ልባቸው ከኢህአፓ ለመኮብለሉ አብይ ምክንያት አድርገው ያቀረቡትን ችግር
ታዬ የተባለ ታጋይ ‹‹ሞናሊዛ›› በሚለው ግጥሙ ግሩም አድርጎ ገልጦት እንደነበረ በ1993 ዓ.ም ‹‹ፅናት›› በሚል ርዕስ የተጋድሎ
ታሪካቸውን ባሳተሙበት መጽሐፍ ላይ ተርከውታል፡፡

‹‹አንተ ሌዎናርዶ የሮማ ጅል
የሰራሀትን ልታሻሽል
ልታፈርሳት ልትገነባት
ደግመህ ደጋግመህ ልትሰራት
ሰልሰህ ልትሰራት ስትችል
ጣኦት አደረግካት በሞትህ አጉል አጉል
ለራስህ ፍጡር እግዚኦ ልትል››

ይህ ግጥም በሰፈረበት ገፅ ላይ የተጠቀሰው የግርጌ ማስታወሻ ደግሞ ሊተላለፍ የተፈለገውን መልዕክት እንዲህ በማለት አብራርቶታል፡-
‹‹ታዬ የሚባል የኢህአፓ ታጋይ ‹ራሳችን የፈጠርነውን ድርጅት ማስተካከል አለብን› የሚል እምነት የነበረው ሲሆን፣ ዳ ቪንቺ እራሱ
ለሳላት ሞናሊዛ ፍቅር እንደተማረከ ሁሉ እኛም የፈጠርነውንና የተበላሸውን ድርጅት አመለክነው፤ ማስተካከልም ተሳነን በማለት ፓርቲው
ላይ እምነት ማጣቱን ‹ሞናሊዛ› በሚል ርዕስ በፃፈው ውብ ግጥም ገለፀ፡፡›› (ገፅ 61)

እነሆም አብዮታዊ ግንባሩ፣ ከመስራቾቹ አንዱ የሆነው ኢህዴን/ብአዴን፣ ያን ጊዜ ኢህአፓን መክሰሻ ባደረገበት ‹‹ድርጅታዊ አምልኮ››
ራሱም ተጠልፎ ከወደቀ ዓመታት ነጉደዋል፡፡ ታዬ እንዳለውም መሪዎቹ ኢህአዴግን ናቡከደናፆር አሰርቶት እንደነበረው አይነት እጅግ
ግዙፍ ‹‹አምላክ›› (ጣኦት) አድርገው ሀገርና ሕዝብን እየገበሩለት (እየሰዉለት) ነው፡፡ ርዕዮተ-ዓለምም ሆነ ፖሊሲ (በተለይ መሬትን
በተመለከተ) ‹‹የሚቀየረው በመቃብራችን ላይ ነው›› ሲሉም አስረግጠው ተናግረዋል፡፡ የትምህርት ፖሊሲውም እንዲህ ትውልድን
እየገደለም እንዲሻሻል ያልተሞከረው በዚሁ እምነታቸው ይመስለኛል፡፡ ይህ ሁኔታም ነው እናንተም የምትስማሙባቸውን ታላላቅ ሀገራዊ
ችግሮችን ለመፍታት ኢህአዴግን ከማፍረስ ውጪ አማራጭ እንዳይኖር ያደረገው፡፡ ከእንግዲህ ወዲያም ከጥፋቱ ታርሞ ለሀገር የሚጠቅም
ዲሞክራሲያዊ የህዝብ ሥርዓት ሊያነበር ይችላል ብሎ ተስፋ ማድረግ ተላላነት ነው፡፡ እንኳን እናንተ ከተማ ላይ የተቀላቀላችሁት አባላት
ቀርቶ፣ ከበርሃ አቅፈው ደግፈው እዚህ ያደረሱት አንጋፋ ታጋዮችና አንዳንድ አመራሮቹም በድርጅቱ ተስፋ ቆርጠው ጥለውት መሄድ
ከጀመሩ ሰንብቷል፡፡ ታጋይ የውብዳር አስፋው ‹‹ፊኒክሷም ሞታ ትነሳለች›› በሚለው መጽሐፏ እውነታውን እንዲህ በማለት ገልፀዋለች፡-
‹‹የድርጅቱ አመራር የወሰዳቸውን የተሳሳቱ እርምጃዎች ቀድሞ ከነበረኝ የድርጅቱ ግንዛቤ ጋር በማጣመር ለዓመታት የታገሉለትንና
የደከሙለትን አባላት በነፃ እንዲንቀሳቀሱ ያላስቻለ ድርጅት፣ ለሕዝብ ነፃነትና ለዲሞክራሲ እታገላለሁ ቢል ከይስሙላ የማያልፍ ከንቱ
መፈክር መሆኑን ደምድሜ፣ ከመጋቢት 5 ቀን 1993 ዓ.ም ጀምሮ ራሴን ከድርጅቱ አገለልኩ፡፡ ይህም በሕይወቴ ጉዞ ዋነኛውና ወሳኝ
እርምጃ ነበር፡፡›› (ገፅ 16)

እንግዲህ ከ1968 ዓ.ም ጀምሮ በተለያዩ የድርጅት፣ የሴቶች ጉዳይና የመንግስት ሥራዎች ተሰማርታ ልጅነቷን በትግል የጨረሰችው የአቶ
ገብሩ አስራት ባለቤት፣ የውብዳር አስፋው እንዲህ አይነቱን ከባድ ውሳኔ በማሳለፍ ከኢህአዴግ ከተቆራረጠች እነሆ አስራ ሶስት ዓመታት
ነጉደዋል፡፡ በግልባጩ እናንተ ደግሞ እስካሁን ድረስ አንቀላፍታችኋል-ገና አልነቃችሁም፡፡ እናም እውነት እውነት እላችኋለሁ፡- ከዚህ
በላዔ-ሰብ ሥርዓት ለመገላገል የምንችለው፣ ዛሬውኑ ይህንን ቅድሚያ ሊሰጠው የሚገባ ዋነኛና ወሳኝ እርምጃ በቆራጥነት መውሰድ
ስትችሉ ብቻ ነው፡፡ አለበለዚያ…

(የዚህ ጽሑፍ ሃሰበ-መልዕክትን በቅንነት ትቀበሉታላችሁ በሚል መተማመን አፈፃፀሙን፡- በምን አይነት መንገድ ተቀራርበን ልንወያይ እንችላለን? በየትኞቹ ጉዳዮች ላይ መግባባት ይቻላል? ሃሳቡንስ ከግብ ለማድረስ ምን ያህል ጊዜ ይወስዳል? የሚሉትንና መሰል ጥያቄዎችን በሌላ ዕትም ተገናኝተን በስፋት እንመክርባቸዋለን)

አትዮጵያ ለዘላለም ትኑር!

No comments:

Post a Comment