February 14/2014
ከገዛኽኝ አበበ
አሁን አሁን በፊስቡክ፣ በየሚዲያው እና በየማህበራዊ ድህረ ገጹ እንደምናየው እና እንደምንሰማው ወያኔ ወይም የወያኔን የልብ አጀንዳ ለማስፈጸም ጎንበስ ቀና እያሉ ያሉ ቅጥረኞች ድርጅቶች ነን ባዮች የኢትዮጵያን ሕዝብ ለማደናገር በየሚዲያው መንቀሳቀስ ጀምረዋል :: እነዚህ ግለሰቦች ወይም ድርጅቶች በአንድ ጎኑ ወያኔን የሚቃወሙ እየመሰሉ በሌላ በኩል ደግሞ የወያኔን መንግስት ለመፋለም ቋርጠው የተነሱትን ጠንካራ እና እራሳቸውን በማደራጀት ላይ የሚገኙትን ፣ ለወያኔ መንግስት አስፈሪ እና ስጋት በመሆን ላይ ያሉትን እራሱም ስጋት ይሆኑብኛል ብሎ የሚፈራቸውን የፖለቲካ ድርጅቶችን ወይም የፖለቲካ ሰዎችን በማሳደድ እና በመቃወም የሚሰሩትን ስራ እና ትግላቸውን በማጣጣል ፣በማንቋሸሽ የበሬ ወለደ ያህል የሃሰት ቅስቀሳቸውን ሲደሰኩሩ መስማት የተለመደ ነገር ሆኖል:: በእነዚህ የፖለቲካ ድርጅቶች ላይም ሆነ የፖለቲካ ሰዎች ላይ በየሚዲያው የሚደረገው የሀሰት የወሬ ዘመቻ (propaganda) ሕዝብን ግራ ለማጋባት እና የወያኔን የስልጣን እድሜ ለማራዘም የወያኔ መንግስት በስፋት በየ አቅጣጫው ያሰማራቸው ለወያኔ እየሰሩ ያሉ አስመሳዬች የወያኔ ምልምሎች ሲሆኑ ስራቸውም የተቀዋሚዎችን የፖለቲካ ትግል መሰለል እና ማዳከም ሲሆን ይህም የሚያሳየው በሀገር ውስጥም ሆነ በውጭም እየተደረገ ያለው ፖለቲካዊ የትግል ጉዞ የወያኔን ባለስልጣኖች ምን ያህል እረፍት እንደነሳቸው እና እንቅልፍ እንዳሳጣቸው ነው : :
ከዛሬ ዘጠኝ ዓመት በፊት ማለትም በ1997 ዓ.ም በኢትዮጵያ ሕዝብ ዘንድ የነበረውን የፖለቲካ መነቃቃት ሁላችንም የምናስታውሰው ሲሆን ከማንኛውም ኢትዮጵያዊ አይምሮ ሊጠፋ በማይችል ሁኔታ የኢትዮጵያ በታላቅ ሀገራዊ ስሜት እና ወኔ ፖለቲካዊ መነቃቃት ውስጥ የነበረበት ጊዜ እንደነበር እ እና ኢትዮጵያ በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ የወያኔን የኢሕአዴግን መንግስት የስልጣን እድሜ ሊያሳጥር የሚችል ጥሩ አጋጣሚ ተፈጥሮላት እንደነበር ሁሉም ሰው የሚስማማበት ሀቅ ሲሆን በጊዜው አብዛኛው የኢትዮጵያ ሕዝብ በወያኔ መንግስት ላይ የነበራቸውን የመረረ ጥላቻ በአደባባይ በመውጣት ለአለም ሕዝብ ያሳዩበት ወቅት ነበር ::በጊዜውም ሕዝቡም በወያኔ መንግስት ላይ ያለውን የመረረ ጥላቻ በግልጽ በማሳየቱ ወጣት ወገኖቻችን በአንባባ ገነኑ የወያኔ መንግስት እንደ ሌባ እና እንደወንበዴ ተቆጥረው በግፍ የተጨፈጨፉበት እና የተገደሉበትን ጊዜ ማንም የኢትዮጵያ ሕዝብ ሊራሳው የማይችል እውነታ ነው :: በዛን ወቅት የኢትዮጵያ ሕዝብ ለውጥ በመፈለግ እና በወያኔ የዘረኝነት አገዛዝ በመማረር ታሪክን ሊሰራ ቆርጦ መነሳቶን በተግባር አስመስክሮል:: ለዚህም ማስታወሻ ይሆነን ዘንድ በሚያዚያ 30/1997 በታሪክ ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ የወያኔን አንገት ባስደፋ እና ቅስም በሰበረ መንገድ ከ2.5 ሚሊዮን የሚበለጥ ሕዝብ ማንም ሳያስገድደው አደባባይ በመውጣት ያሳየው ትዕይንት ማረጋገጫ ነው: ::
በወቅቱ በነበረው የሕዝቡ አንድነትእና ህብረት ፣ ሕዝቡ ለለውጥ በነበረው ጉጉት ያደርግ የነበረው እንቅስቃሴ ለወያኔ መንግስታት አስደንጋጭ ከመሆኑ የተነሳ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በፍርሀት ደንብረው በደብረ ዘይት በሚገኘው አየር ሀይል ተሸሸገው ህዝቡ መብራት ጠፍቶበት፣ ደግሞም ዝናብ ዘንቦ ወደ ቤቱ ከተመለሰ በኋላ ወደ መንበራቸው መመለሳቸውን በጊዜው የነበሩ የአይን አማኞች ተናግረዋል:: : ከዛም በመቀጠል ግንቦት 7 19 97 የነበረው ክስተት በየሰው ፊት ላይ ይነበበ የነበረውን ተስፋ ለመግለጽ ያስቸግር ነበር :: ወጣቶች በሙሉ ሀይላቸው ፖለቲካ እንቅስቃሴ ውስጥ የገቡበት፣ ሁሉም ሰው ፍርሃት እና የፍርሃት ምንጭ የሆነውን የወያኔን አገዛዝ ደህና ሰንብት ያለ ይመስል ነበር በወቅቱ ይሆን እንጂ ምን ያደርጋል በጊዜው ተፈጥሮ የነበረውን የፖለቲካ መነቃቃት በአንዳንድ የበግ ለመድ በለበሱ አስመሳይ ፖለቲከኞች እንደነ አቶ ልደቱ አያሌው በመሳሰሉ ሰዎች በጊዜው የነበረው የፓለቲካ መነቃቃት (revival ) መኮላሸቱ እና እንደ ጉም በኖ መጥፋቱ እስከ ዛሬም ድረስ አብዛኛውን ለውጥ እና ነጻነት ናፋቂ ሀገር ወዳት ኢትዮጵያ ዜጎችን የሚያስቆጭ እና የሚያንገበግብ ሲሆን ወያኔን ለማንበረከክ እና ከስልጣን ለማስወገድ የነበረው ወርቃማ ዕድል መበላሸቱ አብዛኛውን የኢትዮጵያን ሕዝብ አስቋጥቷል ተስፋም አስቋርጦል:: በጊዜውም በነበረው ክስተት የአብዛኛው የኢትዮጵያ ሕዝብም ልብ ተሰብሮል:: እስከዛሬም ድረስ አንዳንድ ሰዎች በኢትዮጵያ የሚደረገውን ማንኛውንም ፖለቲካዊ ትግል በጓሬጥ እና በጥርጣሬ ዳር ላይ ቆመው እየተመለከቱት ይገኛል ::
የ19 97 ምርጫን ተከትሎ የተፈጠረውን የፖለቲካ መነቃቃት መኮላሸቱ እንደተጠበቀ ሆኖ ባለፉት ጊዚያቶች የነበሩት የፖለቲካም ሠዎች ሆኑ የፓለቲካ ድርጅቶች ባረጀ እና በገረጀፈ ጭፍን የፖለቲካ አመራር እና የትም በማያደርስ አመለካከት የወያኔን የስልጣን እድሜ እያራዘሙት ይገኛሉ:: እንደእኔ አመለካከት የወያኔ ኢሕአዲግ የስልጣን እድሜ እስከዛሬ ሊረዘም የቻለበት ዋንኛው ምክንያት በራሱ በኢሕአዲግ ጥንካሬ ሳይሆን በተቃዋሚዎች በደከመ እና በተልፈሰፈሰ የአመራር ችግር ነው:: በኢትዮጵያ ውስጥ ያለፉትን 22 አመታቶች ብዙ የተቃዋሚ ፓርቲ ተብለው ስም የተሰጣቸው ስብስቦች ቢፈጠሩም በኢትዮጵያ ፖለቲካ ላይ አንዳችም የፈየዱት ነገር ሳይኖር ብዙ ጊዚያቶች አልፈዋል:: አሁን አሁን ግን እንደምናየው እንደነ አንድነት፣ አራናት ትግራይ እና ሰማያዊ ፓርቲ ያሉ በወጣቶች የተገነቡ የፓለቲካ ፓርቲ ድርጅቶች መፈጠራቸው በኢትዮጵያ ፖለቲካ ተስፋ ቆርጦ የነበረው ሕዝብ ላይ እስትንፋስ እየዘሩበት ይገኛሉ:: ከምርጫ 97 በኋላ በነበሩት አመታቶች በኢትዮጵያ ፖለቲካ ልቡ ተሰብሮ እና ተስፋ ቆርጦ የተኛውን የኢትዮጵያ ሕዝብ እየቀሰቀሱት ቢሆንም ራዕያቸውን ወደ ፊት ለማስጓዝ ብዙ የቤት ስራ ከፊታቸው የሚጠበቅባቸው ይመስለኛል:: በራቸውንም ነቅተው ከጠላት ወያኔ በመጠበቅ በጥንቃቄ መጓዝ ይገባቸዋል:: ምክንያቱም እስከዛሬ ወያኔ እንደ እስስት እየተለዋወጠ እና እንደ እባብ እየተሽለኳለኳ ስንቶቹን የፖለቲካ ፖርቲ ድርጅቶችን እንደሽመደመዳቸው አይተናልና ::
በምርጫ 97 ጊዜ የነበረውን ቅንጅት ማንም ሰው በአጭር ጊዜ ውስጥ እንደዛ ፍርክስክሱ ይወጣል ብሎ የጠበቀም የገመተም አልነበረም ነገር ግን ባልተጠበቀ ሁኔታ ባልተገመተ ሰአት ብትንትኑ ሊወጣ የቻለበት ምክንያት ጥንቃቄ በጓደለው አካሄድ እና በተዝረከረከ አሰራር የተነሳ ለጠላታቸው የወያኔ መንግስት መጠቀሚያ መሆናቸው ነበር :: ወያኔም እንደ እባብ ተሹለክልኮ በመካከላቸው ለመግባት እና ለመበታትን ጊዜም አልወሰደበትም ነበር : :: በወቅቱም የቅንጅት መፈራረስ ወያኔ እና የወያኔ ካድሬዎች ጮቤ ያስረገጠ ክስተት የነበር ሲሆን ወያኔ እንዳለመው እና እንዳሰበው ለተወሰነም ጊዚያቱችም ቢሆን የኢትዮጵያ ፖለቲካ ተዳፍኖ የጠነከረ የፖለቲካ ድርጅት በሌለበት በማን አለብኝነት ለአጭር ጊዜም ቢሆን ተረጋግቶ እንዲቀመጥ አስችሎታል:: ይሁን እንጂ አሁን ላይ ግን ነገሮች ሁሉ እየተቀየሩ እና እየተለወጡ በውስጥም በውጭም ያለው የፖለቲካው ትግል እሳት እየነደደ እና እየተፋፋመ ሲሆን በቅርብ እንኮን እንደምንመለከተው የህወሃት ወያኔ መንግስት የሚመካበት የትግራይ ህዝብ ሳይቀር የህውሃት መንግስት ለትግራይ ሕዝብ እንደማይመጥን ለወያኔ መንግስት በግልጽ በአደባባይ እየነገሩት ይገኛሉ::በወያኔ መንግስት የስልጣን አገዛዝ መገዛት ያልሰለቸው እና ያልመረረው ብሔር እና የሀገሬቱ ዜጋ የለም :: ለሆዳቸው እና ለጥቅማቸው ህሊናቸውን ሽጠው ከሚኖሩት ከራሱ ከወያኔ ካድሬዎች በስተቀር በመሆኑም እየተፋፋመ ያለው የፓለቲካው ትግል መነቃቃት መላውን ሀገር ወዳድ የኢትዮጵያ ዜጎችን ከዳር እስከዳር ማዳረሱ እና ማነቃነቁ የማይቀር ሀቅ ነው :: ስለዚህ የፖለቲካውን እሳት እያጋጋሉ እና እያፋፋሙ ያሉ የፖለቲካ ድርጅቶችም ሆነ የፖለቲካ መሪዎች ባለፈው ከነበረው ስህተት በመማር በራቸውን ከጠላት ወያኔ ተጠንቅቆ በመጠበቅ ትግሉን ማስቀጠል እና ማፋፋም ይጠብቅባቸዋል :: ወጣቱ ለለውጥ ልቡ ተነሳስቷል የወያኔ ኢህአዲግም የስልጣን ዘመን የጭቆና አገዛዝ የሚከስምበት ጊዜ እሩቅ አይሁንም ::
ኢትዮጵያ በቆራጥ ታጋይ ልጆቿ ከወያኔያዊ አገዛዝ ነጻ ትወጣለች::
ድል ለኢትዮጵያ ሕዝብ!!
No comments:
Post a Comment