February 7/2014
አንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትሕ ፓርቲ (አንድነት)
UNITY FOR DEMOCRACY AND JUSTICE PARTY (UDJ)
=================================
UNITY FOR DEMOCRACY AND JUSTICE PARTY (UDJ)
=================================
አንድነት መግለጫ – የሕግ የበላይነት እንዲረጋገጥ የማድረግ ትግላችን ተጠናክሮ ይቀጥላል!!!
ከአንድነት ለዴሞክራሲ እና ለፍትህ ፓርቲ (አንድነት) የተሰጠ መግለጫ!!!
ፓርቲያችን አንድነት ከቆመላቸው ክቡር አላማዎች አንዱ የሕግ የበላይነት እንዲሰፍን ማድረግ ነው፡፡ የህግ የበላይነትና ፍትሃዊነት ለአንድ ሀገር ምሰሶ ሆነው እያለና እንዲሁም ለህግ የበላይነት መስፈን ትልቁ ባለድርሻ ገዢ የሆነው ፓርቲ ሊሆን እንደሚገባ እየታወቀ የተገላቢጦሽ ሆኖ ህግ አስከብራለሁ የሚለው አካል ሕግ ሲጥስ፤ ሰብአዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶችን ሲገፍ ዝም ማለት አይቻልም፡፡ ህገ ወጥነትን መታገልና ብሎም ለሕግ ማቅረብ ግዴታ እንደሆነ አንድነት ያምናል፡፡
እንደሚታወቀው ፓርቲያችን ህጋዊ መብቱን ተጠቅሞ ሠላማዊ በሆነ መንገድ ለሦስት ወር የቆየ ሚሊዮኖችን ያሳተፈ ህዝባዊ ንቅናቄ ማድረጉ የሚታወስ ነው፡፡ በዚህ ሂደት ግን ህጋዊ ከለላ ሊሰጡን ከሚገባ የመንግሥት አካላት የተለያዩ ጥቃቶች ተፈጽመውብናል፡፡ ስልጣናቸውን ካለ አግባብ በመጠቀምም ቁሳዊና ሞራላዊ ጥቃት አድርሰውብናል፡፡ ጥቃቱ በመላ ኢትዮጵያ እንቅስቃሴ ባደረግንባቸው ሁሉ ሲሆን አባሎቻችንና አመራሮች እንዲታሰሩ ተደርጓል፣ በራሪ ወረቀቶች ተነጥቀዋል፣ ተዋክበዋል፡፡
በክልል ከተሞች ያየነው ማሰርና ማዋከብ ዋና ከተማ በሆነችው አዲስ አበባ በድጋሚ ሲፈፀም ስናይ ግን እጅግ አዝነናል፡፡ የሠላማዊ ሠልፍ እውቅና ደብዳቤ የሰጠን የአዲስ አበባ መስተዳድር፤ ህግ የጣሰ ድርጊቱን ማስቆም ያልቻሉት የአዲስ አበባ ከንቲባና ያለምንም ማስረጃ፣ ህጋዊ ወረቀት እንዳለን እያወቀ በጠዋት አስሮ ማታ ሲፈታ የነበረው የአዲስ አበባ ፖሊሲና ማስቆም ያልቻሉት የፖሊሲ ኮሚሽነሩ ለደረሰብን ህገ ወጥ ድርጊት ዋነኛ ተጠያቂዎች ናቸው ብለን እናምናለን፡፡
ፓርቲያችን በህገ መንግሥቱ አንቀጽ 9 መሠረት ህገ መንግሥቱን ተቀብሎ የተቋቋመ መሆኑ እየታወቀ የአዲስ አበባ አስተዳድር ዋና ስራ አስፈፃሚ ሆኖ እያለ እንዲሁም የአዲስ አበባ ፖሊስን የእለት ተእለት ሥራ የሚቆጣጠር ሆኖ እያለ ሠላማዊና ህጋዊ እንቅስቃሴያችንን ለመገደብ ስልጣናቸውን ያላግባብ በመጠቀም አባሎቻችን በገፍ እንዲታሰሩ፣ አመራሮቻችንን ከቅስቀሳ ቦታ ላይ አፍሰው በመውሰድ ታስረው እንዲውሉ፣ የቅስቀሳ ቁሳቁሶች እንዲነጠቁና ፖስተሮች እንዳይለጠፍ ተደርጓል፡፡
በህገ መንግሥቱ አንቀጽ 3ዐ ላይ በግልጽ እንደተቀመጠው አንድነት ፓርቲ አላማውን ለማሳካትና በህገ መንግሥቱ የተሰጡትን መብቶች ለመጠቀም የመቃወምና ሠላማዊ ሠልፍ የመጥራት መብት ቢኖረውም ይሄ መብቱ ህግ በመጣስ እንዲቆም ተደርጓል፡፡ ስለዚህ የአዲስ አበባ መስተዳድር በአዋጅ ቁጥር 3/83 አንቀጽ 7 መሠረት የአንድነት የሠላማዊ ሠልፍ ጥያቄ ተቀብሎ የማስተናገድና የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን መስሪያ ቤት የማዘዝና ጥበቃ የማድረግ ኃላፊት ቢጣልበትም ኃላፊነቱን መወጣት ባለመቻሉ በህግ እንዲጠየቅ አድርገናል፡፡
የፖለቲካ ፓርቲዎች አዋጅ ቁጥር 573/2ዐዐዐ አንቀጽ 46 ላይ በግልጽ እንደተቀመጠው ፓርቲያችን የቅስቀሳ ሥራ ለመስራት ምንም ተጨማሪ ፈቃድ የማያስፈልገው ቢሆንም ፖሊስ ይህንን በተላለፈ መልኩ ያለ በቂ ምክንያት እስር ፈጽሟል፡፡ ህግን ባልተከተለ መልኩ በአባላትና ደጋፊዎች ላይ ወከባና ማስፈራሪያ በመፈፀማቸው በህግ እንዲጠየቁ አድርገናል፡፡
ማንም ሰው ወይም አካል ከህግ በላይ ሊሆን አይችልም፡፡ ህገ ወጥነትን መታገስም በራሱ ወንጀልን ማበረታታት ነው፡፡ ስለዚህ የሕግ የበላይነት እንዲረጋገጥ የማድረገ ትግላችን ተጠናክሮ ይቀጥላል፡፡ በቅርቡም በመንግስት ከፍተኛ አመራሮችና በአጠቃላይ በገዢው ፓርቲ ላይ ክስ ለመመስረት በሂደት ላይ መሆናችን እንዲታወቅ እንፈልጋን፡፡ ይህ ህግን በማስከበር ላይ ትኩረቱን ያደረገው ንቅናቄ ‹‹Millions of voices for justice›› የህግ የበላይነት እስከሚከበር ተጠናክሮ የሚቀጥል ይሆናል፡፡ በዚህ አጋጣሚ የፍትሕ ተቋማቱ ግራ ቀኙን በመመርመር ለህግ የበላይነት መረጋገጥ እንደሚሰሩ ተስፋ እናደርጋለን፡፡
የሚሊዮኖች ድምፅ ለፍትህ!!!
አንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ
ጥር 29 ቀን 2006 ዓ.ም
አዲስ አባባ
አንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ
ጥር 29 ቀን 2006 ዓ.ም
አዲስ አባባ
No comments:
Post a Comment