Tuesday, February 11, 2014

ደራሲና የአንድነት አመራር አባል፣ አቶ አንዳርጌ መስፍን ፖሊስ ፊት እንዲቀርቡ ታዘዙ

February 10/2014

ወጣቱ ፖለቲከኛና ደራሲ አቶ ዳንኤል ተፈራ ፖሊስ ጣቢያ እንዲቀርብ መጠየቁ በስፋት መዘገቡ ይታወቃል። አቶ ዳንኤል መጀመሪያ ላይ እንዲቀርብ የተጠየቀዉ በስልክ፣ ሲሆን፣ ሕጋዊ መጥሪያ ወረቀት ካልመጣለት በቀር ለመቅረብ ፈቅደኛ ሳይሆን እንዳልቀረ ለማወቅ ተችሏል።
ከአቶ ዳንኤል ተፈራ በተጨማሪ፣ የአንድነት ብሄራዊ ምክር አባል የሆኑትና በርካታ መጽሃፍት በመጻፍ የሚታወቁት አዛዉንቱ 
አቶ አንዳርጌ መስፍንን፣ ፖሊስ ለመከሰስ እንደተዘጋጀ፣ እንዲቀርቡም እንዳዘዘ ለማረጋገጥ ችለናል።
አቶ አንዳርጌ መስፍን ከጻፏቸው በርካታ መጽሃፍት መካከል «ጥቁር ደም» የሚለው ታዋቂ መጽሃፍ ይገኝበታል። ከአቶ መለስ ዜናዊ ሕልፈት በኋላም፣ «የመለስን ራእይ እናስቀጥላለን» የሚል አቶ መለስን እንደ አምላክ የማቅረብ የፕሮፖጋንዳ ዘመቻ ከልክ ባለፈበት ወቅት «በሞት መንፈስ አገር ሲታመስ» የሚል መጽሃፍን የጻፉ ደራሲ ናቸው።
አቶ አንዳርጌ መስፍን፣ በአንድነት ፓርቲ ዉስጥ በአዲሱና ከዚያም በፊት በነበረው የብሄራዊ ምክር ቤት አባል አመራር አባል ሆነው እያገለገሉ ሲሆን፣ የፍኖት ጋዜጣ ኤዲቶሪያል ቦርድ ዉስጥ ሰርተዋል።
ኢሕአዴግ በአቶ ዳንኤል ተፈራና አንዱ አንዳርጌ መስፍን ላይ ምን አይነት ክስ እንደሚያቀርብ ገና የታወቀ ነገር ባይኖርም፣ የአንድነት አመራር አባላትን እና ደጋፊዎች ለማስፈራራት፣ ለፍርድ ቤት መመሪያ በመስጠት፣ እስከ ስድስት ወራት የእስራት ቅጣት ሊበየንባቸዉ እንደሚችል የአንድነት አመራር አባላት ይናገራሉ።
በዚህ ጉዳይ ላይ አስተያየት የሰጡን የአንድነት ፓርቲ የሕዝብ ግንኙነት ክፍል ሃላፊ አቶ ሃብታሙ አያሌዉ ፣ አቶ ዳንኤልም ሆነ አቶ አንዳርጌ መስፍን ፍጹም ሰላማዊ፣ ሰው አክባሪና አገር ወዳድ እንደሆኑ በመግለጽ፣ በነርሱ ላይም ሆነ በሌሎች የአመራር አባላት ላይ እየተደረገ ያለው ጥቃት፣ በሕዝብ ዘንድ የበለጠ ተቀባይነትን ድጋፍ እያገኘ የመጣዉን የአንድነት ፓርቲ ሆን ብሎ ለማዳከም ሲባል በፖለቲካዊ ዉሳኔ የሚደረግ እንደሆነ አስረድተዋል።
«ወያኔ የሚል ቃል ተጠቅመሃል» በሚል ክስ እርሳቸዉም ቀርቦባቸዉ ከአሥራ አንድ ጊዜ በላይ፣ ፍርድ ቤት እየተመላሱ እንደሆነ የገለጹት አቶ ሃብታሙ «ያለ ምንም ጥርጥር ወደፊት እንሄዳለን። መታሰሩ በጣም ቀላል ነገር ነዉ። የሰላማዊ ትግሉ ይቀጥላል» ሲሉም የርሳቸውም ሆነ የሌሎች የአመራር አባላት መታሰር አንድነትን እንደ ፓርቲ፣ ትግሉን እንደ ትግሉ የሚያጠናክር እንጂ የሚጎዳ እንዳለሆነ አሳስበዋል።

No comments:

Post a Comment