February 26/2014
ባለፈው የካቲት 17 ቀን 2006 ዓ.ም በቦሌ አካባቢ አንድ የጥበቃ ሠራተኛ 3 ጊዜ ጥይት ወደ ሰማይ ከተኮሰ በኋላ ራሱን እንዳጠፋ በዘ-ሐበሻ ድረገጽ ላይ ዘግበን፤ ለምን ራሱን ሊያጠፋ እንደቻለ የሚገልጽ መረጃ አለመገኘቱን ዘግበን ነበር።በአዲስ አበባ ከተማ ታትሞ የሚወጣው ሪፖርተር ጋዜጣ በዛሬው ዕትሙ እንደገለጸው ሟች በሱፈቃድ በጋሻው ራሱን ለማጥፋት የወሰነበት ደብዳቤ በኪሱ ተገኝቷል፤ ሲል ዘግቧል። ሟች ጊዜውን ባይጠቅሰውም በተወለደበት አካባቢ ነዳጅ የጫነ ተሳቢ ፍሬን ተበጥሶ ከሞት ማምለጡን፣ መሞት ካለበት ደግሞ ራሱን በራሱ ማጥፋት እንዳለበት መወሰኑን የሚገልጽ ደብዳቤ ጽፎ በኪሱ መገኘቱ ተዘግቧል።
የሪፖርተር ዘገባ እንደወረደ፦
ወጣቱ የጥበቃ ሠራተኛ በሱፈቃድ በጋሻው በኪሱ ውስጥ ከተገኙት የተለያዩ መታወቂያዎች መረዳት እንደተቻለው፣ አጋር የጥበቃ ሠራተኞች ማሠልጠኛ ተቋም ተቀጣሪ ነው፡፡ በተጨማሪም የኮሌጅ ተማሪ መሆኑን በሚገልጸው መታወቂያ ላይ እንደሠፈረው ከሆነ፣ በ1982 ዓ.ም. የተወለደና የ24 ዓመት ወጣት ነው፡፡ በምን ምክንያት ከፖሊስ ባልደረባነት እንደለቀቀ ባይታወቅም፣ የ13ኛ ኮርስ የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን አባል እንደነበር በቅርብ ከሚያውቁት ወዳጆቹ ለማወቅ ተችሏል፡፡
በባንኩ አሠራር አንድ የጥበቃ አባል 24 ሰዓት ሠርቶ 24 ሰዓታት የሚያርፍ በመሆኑ፣ ሟች በሱፈቃድም የካቲት 17 ቀን 2006 ዓ.ም. ጠዋት አዳሪ ጓደኛውን ከቀየረ በኋላ፣ ባንኩን ለመጠበቅ የቻለው ለ24 ሰዓታት ሳይሆን ለሰባት ሰዓታት ብቻ ነው፡፡ ወጣቱ ‹‹ኑሮ መሮኛል›› በማለት እያማረረ እያለ በመሀል የያዘውን ጠመንጃ ቃታ በመሳብ አንድ ጊዜ ወደ ላይ ሲተኩስ፣ አብረውት የነበሩ ሴት ፈታሽና ሌሎች የባንኩ ተጠቃሚዎች በመደናገጥ ወደ ውስጥና ወደ ውጭ ሽሽት ይጀምራሉ፡፡ ሁለተኛውን ጥይት በመተኮስ ወደ ሚሊኒየም አዳራሽ በኩል በፍጥነት መራመድ መቀጠሉን በሥፍራው የነበሩ የዓይን እማኞች ተናግረዋል፡፡
ሦስተኛውን ጥይት ወደ ላይ ከተኮሰ በኋላ አራተኛውን አንገቱ ሥር በመደገን ተኩሶ፣ ራሱን ማጥፋቱን የዓይን እማኞቹ አስረድተዋል፡፡
ሟች በሱፈቃድ ተወልዶ ያደገው በጉለሌ አካባቢ እንደሆነ፣ አሁንም ከቤተሰቡ ጋር እየኖረ እንደሚገኝ፣ ጊዜውን ባይጠቅሰውም በተወለደበት አካባቢ ነዳጅ የጫነ ተሳቢ ፍሬን ተበጥሶ ከሞት ማምለጡን፣ መሞት ካለበት ደግሞ ራሱን በራሱ ማጥፋት እንዳለበት መወሰኑን የሚገልጽ ደብዳቤ ጽፎ በኪሱ መገኘቱም ተሰምቷል፡፡
ከዘ-ሐበሻ የተወሰደ
ከዘ-ሐበሻ የተወሰደ
No comments:
Post a Comment