Saturday, January 4, 2014

አይ ስብሐት ነጋ! (ፕ/ር መስፍን ወልደ ማርያም)

January 4, 2014
                                        ፕ/ር መስፍን ወልደ ማርያም

በቅርቡ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ከጋዜጠኛነት ተማሪዎች ጋር ባደረገው ውይይት ላይ ሁለት ሰዎች ጽፈው አይቻለሁ፤ ዶር. በድሉ ዋቅጅራ በ
ፋክት ላይ፣ ናስ በላይ አበበ በኢትዮ-ምኅዳር ላይ፤ ሁለቱም ሰዎች አልወደዱለትም ማለት ያንሳል፤ የሚወዱለትና የሚያጨበጭቡለት መኖራቸውም ሳይታለም የተፈታ ነው፤ ነገር ግን ስብሐት ነጋም ሆነ ደጋፊዎቹ አደባባይ ወጥተው ለመከራከር አይችሉም፤ ናስ በላይ አበበ እንደሚነግረን ‹‹አቶ ስብሐት ነጋ የውጭ ሰው እንዳይገባ ከተማሪዎቹ ጋር ተደራድረው ነበር የመጡት፤ ስለሆነም ነበር ከፍተኛ ጥበቃ አልፈን የገባነው፤›› ብቻውን ተናግሮ በጭብጨባ የሚሸኝበት መድረክ በመፈለጉ በከባድ ጥያቄም ቢሆን የሚያጣድፉት ሰዎች እንዳይኖሩ ማረጋገጡ በተማሪዎቹም ቢሆን ውሎ አድሮ ትዝብት ላይ ይጥለዋል።በኢትዮጵያ ውስጥ ሥልጣን ሳይኖረው ባለሙሉ ሥልጣን፣ እውቀት ሳይኖረው ባለሙሉ እውቀት የሆነ ሰው ስብሐት ነጋ ብቻ ነው፤ እንዲያውም ከዚያም አልፎ ራሱን የቻለ ሉዓላዊ ነጻነት ያለው ግለሰብ ነው ለማለት የሚቻል ይመስለኛል፤ በዚህ ግለሰብ ላይ የማደንቃቸው ሁለት ነገሮች ናቸው፤ በሉዓላዊነቱ የተጎናጸፈውን ሥልጣን ሙሉ በሙሉ ይጠቀምበታል፤ ይቆጣኛል ወይም ይቀጣኛል ብሎ የሚፈራው የለም፤ ስብሐት ነጋ የሚፈራው ምንም ነገር የለም፤ ሁለተኛ በሉዓላዊነቱ ያለውን ሙሉ ነጻነት በሙሉ ልብ ይጠቀምበታል፤ ናስ በላይ ከበደ እንዳለው ‹‹የቅብጠት መዘላበድ›› ሊሆን ይችላል፤ ስብሐት ነጋ የተናገረው ነገር ትክክል ይሁን አይሁን ጉዳዩ አይደለም፤ ዋናው ነገር መናገሩ ነው።
ዶር. በድሉ ዋቅጂራ ስለስብሐት ነጋ ከኢትዮጵያዊነት መውደቅ በሚል በጻፈው ላይ ዶር. ዳኛቸውን እንደሚከተለው ይጠቅሳል፤ ‹‹ከኢትዮጵያዊነት መውደቅ ማለት፤ በቃ በአጭሩ (ኢትዮጵያዊ ሆኖ)ኢትዮጵያዊ አለመሆን ነው፤›› በቅንፍ ውስጥ ያለው የኔ ነው፤ ልክ ነው፤ አንድ ግለሰብ በማናቸውም ምክንያት ከኢትዮጵያዊነት ቢወድቅ ኢትዮጵያዊነቱ የከሸፈ ነው ለማለት ይቻላል፤ ነገር ግን ከኢትዮጵያዊነት መውደቅንና ኢትዮጵያዊነትን መጣልን ለይተን ማየት ያስፈልጋል፤ አንድ ሰው በማናቸውም ምክንያት ከፍተኛውን የኢትዮጰያዊነት ባሕርይና ግዴታ መሸከም አቅቶት ቢወድቅ ለዚያ ሰው ኢትዮጵያዊነቱ ከሸፈ፤ ለስብሐት ነጋና ለጓደኞቹ ከከሸፈባቸው የቆየ ይመስለኛል፤ ከራሱ አልፎ የሌሎችን ኢትዮጵያዊነት ለማክሸፍ የሚሞክር ደሞ ከመክሸፍ አልፎአል፤ ከኢትዮጵያዊነት መውደቅ ማለት የከሸፈ ኢትዮጵያዊነት ነው ማለት ነው።
TPLF power broker, Sibehat Negaስብሐት ነጋ ዋና ዓላማው በሙሉ ነጻነት የመጣለትን እንደመጣለት መናገር ነው፤ ምሳሌዎችን እንጥቀስ፤– ሀ) ‹‹ከኢትዮጵያ ሕዝብ በላይ የኤርትራ ሕዝብ ኢትዮጵያዊነት አለው፤›› ስብሐት ነጋ ስለኢትዮጵያ ሕዝብ፣ ስለኤርትራ ሕዝብ፣ ስለኢትዮጵያዊነት ያለው እውቀት የሚባል ነገር እንዲህ ያለው መዘባረቅ ነው፤ ስብሐት ነጋ ጨረቃ ከጸሐይ የበለጠ ትሞቃለች ቢልም አይደንቀኝም፤ አልከራከረውም፤ ስብሐት ነጋም ብቻውን መናገር እንጂ መከራከር አይፈልግም፤ ለ) ‹‹የኢትዮጵያ ሕዝብ ከኤርትራ ሕዝብ የበለጠ የኤርትራን መሬት ይፈልጋል፤›› እንደምሳሌ ያነሣው አሰብን ነው፤ ባድመን አላነሣም!  እሱና ጓደኞቹ የኢትዮጵያን ወጣቶች በከሸፈ ጦርነት ውስጥ የማገዱት ባድመ ለሚባል መንደር ነው እንጂ አሰብ ለሚባል ወደብ አልነበረም፤ በዚያን ጊዜ ጦርነቱን በመቃወም ድምጼን ያሰማሁት ኢትዮጵያዊ ወይም ኤርትራዊ ሆኜ አልነበረም፤ ሰው ሆኜ ነው፤ ዛሬ ስብሐት ነጋ ሲዘላብድ ኢትዮጵያዊነት የማይታይበትን ያህል ኤርትራዊነትም አይታይበትም፤ በዚህም ጉዳይ ላይ መከራከር አይፈልግም፤ ሐ) ‹‹ለማንኛውም ሰማያዊ ፓርቲ ሰልፍ መከልከላቸው የማውቀው ብዙ ነገር የለኝም፤ ይከልከሉም አልልም፤ አይከልከሉም አልልም፤ መብታቸው ነው፤›› ይህ መዘላበድ ካልሆነ ምንድን ነው? ምን ቁም-ነገር ይዞ ነው ይህንን የተናገረው? የገለባ ክምር ውስጥ አንድ ፍሬ መፈለግ ይቀላል።
አንድ ሌላ የስብሐት ነጋ ዘዴ (ዘዴ ካልነው!) ጉዳዩን በሚገባ ሳያጣራ እንደመጣለት ይናገርና ‹‹አላውቅም›› ይላል! የማያውቀውን መዘባረቅ ግን ይችላል፤ ሰማያዊ ፓርቲ ‹‹የምን ፓርቲ እንደሆነ አይታወቅም፤ የእስላም ፓርቲ ነው?›› ስብሐት ነጋ እውቀትን የሚሻ ቢሆን ለፓርቲዎች እውቅናን የሚሰጠውን መሥሪያ ቤት ያውቀዋል፤ ለምን ብሎ ይጠይቅ? ለምን ብሎ እውነቱን በማወቅ ይታሰር? ትክክለኛ መረጃ ባለማወቅ እንደልብ የመናገርን ነጻነት ይገድባልና ‹‹አላውቅም›› ማለት ለመዘላበድ ይጠቅማል፤ ምንም እንኳን የሰላዮች ሠራዊት እንዳለው ብናውቅም ስለእስላሞችና ስለሰማያዊ ፓርቲ የተናገረውን እንደፖሊቲካ ከወሰደው ደረጃውን ከማሳየት አያልፍም፤ ሰማያዊ ፓርቲን በሁሉም ዘንድ ለማስጠላት የሚከተለውን ይላል፤ ‹‹እስላሞች ወንድሞቻችን የሚሉት ደግሞ የት ያውቁናል? ሲቀጠቅጡን የነበሩ፤ ተራ ሕዝቡም አይወዳቸውም፤›› የጤፍ ቅንጣት የምታህል የማሰብ ተግባር ቢኖርበት ስብሐት የተናገረው ያልተጠረነፉትን እስላሞች በሙሉ የሰማያዊ ፓርቲ ደጋፊ የሚያደርግ መሆኑን መረዳት ይችል ነበር።
ስብሐት ነጋ አንድ መቶ ሃያ ዓመታት ያህል ወደኋላ ቢሄድ ኤርትራ የሚባል አገር አያገኝም፤ በዚያ መሬት ያሉ ሰዎች ላላቸው ወይም ለሌላቸው የኢትዮጵያዊነት ስሜት የስብሐት ነጋን ምስክርነት እንደማይፈልጉ በጣም እርግጠኛ ሆኖ መናገር ይቻላል፤ ለሌሎቻችን ኢትዮጵያዊነትም ቢሆን የስብሐት ነጋ ምስክርነት አያሻንም፤ አሰብን አንሥቶ ብዙ ወጣቶች ያለቁበትን ባድመን ሳያነሣ መቅረቱ በአንድ በኩል፣ አሰብንም ሆነ ባድመን ከሚፈልጉ ወገኖች መሀል እሱ መውጣቱን በጣም ግልጽ አደረገ፤ ወዴት እንደገባ ግን ገና አልነገረንም!!!

No comments:

Post a Comment