January15/2014
የአውሮፓ ህብረት ኮሚሽን ለአንድነት ፓርቲ ባቀረበው ጥሪ መሰረት የፓርቲው ስራ አስፈፃሚዎችና ከ22 ከሚበልጡ የህብረቱ ሀገራት ከፍተኛ ዲፕሎማቶች ሰፊ ውይይት ማድረጋቸውን የአንድነት ፓርቲ ህዝብ ግንኙነት ክፍል አስታወቀ፡፡ የፓርቲው የህዝብ ግንኙነት ክፍል ኃላፊ አቶ ሀብታሙ አያሌው ለፍኖተነፃነት እንዳስታወቁት ትላንት ጥር 6 ቀን 2006 ዓ.ም በተደረገው በዚህ ውይይት የአንድነት ፕሬዝዳንት ፣የህዝብ ግንኙነትና የውጪ ግንኙነት ኃላፊዎች ተሳትፈዋል፡፡
በውይይቱ ወቅት የተለያዩ ሀገራትን የወከሉት የህብረቱ ዲፕሎማቶች አሁን ስለሳለው አጠቃላይ የሀገራችን የፖለቲካ ሁኔታ፣አንድነት እንደ ፓርቲ ያለበትን ሁኔታ በዝርዝር ለማወቅ ባቀረቡት ጥያቄ መሰረት የፓርቲው ፕሬዝደንት በፕሮጀክተር የታገዘ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም አንድነት ከግንኙነት ስትራቴጂ አንፃር በሀገር ውስጥ እንዲሁም በውጪ ማለትም ከኢትዮጵያ ዳያስፖራና ከአለም አቀፉ ህብረተሰብ ጋር ስለሚኖረው ግንኙነት የተብራራ ምላሽ ተሰጥቷቻዋል፡፡ ኢንጅነት ግዛቸው አንድነት በሚመለከት ባቀረቡት ገለፃ የፓርቲውን ርዕይ፣ተልዕኮና አላማ በሰፊው አብራርተዋል፡፡በመቀጠልም ስለአንድነት ፖሊሲዎችና መርሆዎች ጥልቅ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡አክለውም የአንድነት ፓርቲን ተቋማዊ አደረጃጀት በሚመለከት ገለፃ ሰጥተዋል፡፡ የሀገራችንን ወቅታዊ ሁኔታ በሚመለከትም የኢህአዴግ መንግስት ባለፉት አመታት አንዳችም አይነት የለውጥ አዝማሚያ እንዳላሳየ ይልቁኑም ተቋማዊ የአፈና ስርአትን እያጠናከረ እንደሚገኝ ፕሬዝዳቱ ማሳያዎችን በመጥቀስ አብራርተዋል፡፡
የኢህአዴግ መንግስት የተዘፈቀበትን ሙስና ግዝፈት የዘረዘሩት ኢንጅነር ግዛቸው የፀረሽብር ህጉ ከመንግስት የተለየ የፖለቲካ አቋም ያላቸውን ፖለቲከኞችና ጋዜጠኞች ለማጥቃት የተቀመጠ መሆኑን በአንድነት አመራሮችና በሌሎች የተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮችም ላይ የደረሰውን እስርና እንግልት በማሳያነት አስረድተዋል፡፡ አንድነት ከኢትዮጵያ ዳያስፖራ አባላት ጋር መልካም ግንኙነት እንዳለውና በበርካታ ሀገራትም የተቋቋሙ የአንድነት ድጋፍ ሰጪ ቻፕተሮች እንዳሉ ጠቁመዋል፡፡
ወደፊትም በተጠናከረ ደረጃ በሀገራቸው ፖለቲካ ላይ በቀጥታ የሚሳተፉበትን መንገድ እንደተቀየሰና የዲያስፖራው አባላትን በአባልነትና በድጋፍሰጪነት በንቃት ለማሳተፍ መታቀዱን ፕሬዝደንቱ ተናግረዋል፡፡ በውይይቱ ላይ ከፓርቲው ፕሬዝደንት ከኢንጅነር ግዛቸው ሽፈራው ጋር የተገኙት የህዝብ ግንኙነት ኃላፊው አቶ ሀብታሙ አያሌውና የውጪ ግንኙነት ሀላፊው ኢ/ር ዘለቀ ረዲ ተጨማሪ ማብራሪያ መስጠታቸውም ታውቋል፡፡
No comments:
Post a Comment