Monday, January 13, 2014

የህወሓት መፈክር፡ ‘የአማራ የበላይነት ይውደም!’ (በአብርሃ ደስታ)

January13/2014

ግርማይ ገብሩ የቀድሞ የህወሓት ታጋይና የአሁን የቪኦኤ (VOA) ዘጋቢና ደራሲ ነው። ዓላማዬ ስለ ግርማይ ገብሩ ለመፃፍ አይደለም፤ ግርማይ በፌስቡክ ገፁ ስላሰፈረው መረጃ ለመዋስ እንጂ። መረጃው ከዚህ በፊትም አውቀው ነበር። ግን ለማስረጃ ያህል ግርማይን ልጥቀስ: ምክንያቱም ግርማይ የህወሓት ታጋይ ነበርና።

ግርማይ በ1969 ዓም የህወሓት (ተሓህት) ሦስቱ መፈክሮች ሲጠቅስ የመጀመርያውና ዋነኛው አድርጎ የፃፈው “አፄነት፣ መስፍንነትና የአማራ የበላይነት ይወድማሉ” ይላል።

በትግርኛ “ካብ ጭርሖታት ህወሓት 1969 ዓም: ሃፀይነት፣ መስፍንነትን ናይ አምሓራ ዕብለላን ዓነውቲ እዮም!” ይላል። ግርማይ ገብሩ አልተሳሳተም። ከህወሓቶች ጋር የማልስማማበት ግን ነጥብ አለኝ።

እርግጥ ነው። እኔም አፄነትና መስፍንነትን እንደ ስርዓት አልቀበልም። ምክንያቱም አፄነትና መስፍንነት (እንደ ስርዓት) ላሁኗ ኢትዮጵያ አይመጥኑም። የአፄነትና መስፍንነት ስርዓት በኢትዮጵያ ታሪክ እዚ ግባ የሚባል ለውጥ አላመጣም። ስለዚህ እኛ የሚያስፈልገን ዘመናዊ (ከዘመኑ ንቃተ ህሊናችን ጋር አብሮ የሚሄድ) የህዝብ አስተዳደር (ዴሞክራሲ) እንጂ ንጉስነት (የሰው ገዢነት) አይደለም። የምንፈልገው የሕግ የበላይነት እንጂ የንጉስ የበላይነት አይደለም።

ግን አፄነትና መስፍንነት እንደ ስርዓት ባልቀበለውም የንጉሳውያን ቤተሰቦችና መሳፍንቶች መጥፋት አለባቸው ብዬ ግን አላምንም። እኔ ብሆን እነኚህ የንጉስ ቤተሰቦችና መሳፍንት ቁልፍ የመንግስት ስልጣን አልሰጣቸውም ነበር። በሀገራቸው በሰላም እንዲኖሩ ግን እፈቅድላቸው ነበር። ምክንያቱም እንደማንኛውም ሰው ዜጎች ናቸው፤ ለሀገራቸው በተቻላቸው መጠን አስትዋፅዖ አድርገዋል። ስለዚህ ንጉሳዊ ቤተሰብና መሳፍንት ስለሆኑ ብቻ መጥፋት አለባቸው ብዬ አልፈርድም። እንደ ጠላትም አላያቸውም፣ እንደ ዜጎች እንጂ።

ህወሓት ግን በመፈክር ደረጃ በጠላትነት ፈረጃቸው። በተግባርም አጠፋቸው፣ ገደላቸው። በንጉሳዊ ቤተሰብና መስፍንነት ዝንባሌዎች ሰበብ ብዙ የተምቤን፣ ዓጋመ፣ እንደርታ፣ ዓድዋ፣ ሽረ፣ አክሱም ወዘተ መሳፍንቶች እንዲጠፉ ተደረገ። ‘ትግራይ ከመሳፍንቶች ነፃ ወጣች’ ተባለ። እውነታው ግን ‘ትግራይ ተገደለች’ መባል ነበረበት። መሳፍንቶች ከስልጣን ማውረድ እየተቻለ መግደል ምን አመጣው (ህወሓቶች ከስልጣን ማውረድ እየተቻለ መግደል ለምን ያስፈልጋል)?

ባጠቃላይ መሳፍንቶቹ ሲወድሙ ትግራይ ወደመች። አሁን በትግራይ የተቃውሞ መንፈሱ የተዳከመው በመስፍንነት ሰበብ ብዙ ብቁ ሰው ስለተፈጀብን ነው የሚል እምነት አለኝ። በህወሓት የተገደሉብንን ያህን በሌላ ስርዓት አልተገደሉብንም። ስለዚህ መሳፍንቶች ከስልጣን በማውረድ (መሳፍንቶችን ሳይሆን መስፍናዊ ስርዓቱ) ከህወሓቶች ጋር እስማማለሁ። መስፍናዊ ስርዓቱ ለማጥፋት መሳፍንቶቹ ማጥፋት ከሚል የህወሓት መፈክር ወይ መርህ ግን አልስማማም።

ሌላውና መሰረታዊ የህወሓት ችግር “የአማራ የበላይነት ይውደም!” የሚል መፈክር ነው። እኔም ብሆን የማንም ሰው ወይ ብሄር ወይ ሌላ አካል የበላይነት አልቀበለም። የቴድሮስ ወይ ዮሃንስ ወይ ምኒሊክ ወይ ኃይለስላሴ ወይ መንግስቱ ወይ መለስ ወይ ኃይለማርያም ወይ አማራ ህዝብ ወይ ትግራይ ህዝብ ወይ ኦሮሞ ህዝብ ወይ ሌላ … የበላይነት አልቀበልም። እኔ የምቀበለው የበላይነት ‘የሕግ የበላይነት’ ብቻ ነው። የሌላ የማንም የበላይነት አልቀበልም።

እንደ ፖለቲካ ድርጅት አንድን ህዝብ ዒላማ አድርጎ መነሳት ግን ስህተት ብቻ ሳይሆን በሽታ ነው። ህወሓት (ተሓህት) የአማራን ህዝብ ዒላማ አድርጎ ሲነሳ፣ ሌሎች የህወሓት ተቃዋሚዎች ደግሞ በህወሓት ምክንያት የትግራይን ህዝብ ዒላማ ሲያደርጉ ዉጤቱ ምን ይሆናል? አንድን ህዝብ ከሌላ ህዝብ ጋር የማጣላት ስትራተጂ የፖለቲካ ዕብደት ነው። ህዝብና ገዢው መደብ አለመለያየት (አንድ እንደሆኑ አድርጎ ማሰብ) የፖለቲካ እውቀት ማነስ ዉጤት ነው። ስርዓቱ መቃወምና መታገል እየተቻለ ህዝብን ዒላማ አድርጎ በህዝቦች ላይ መተማመን እንዳይኖር መትጋትና በህዝቦች መካከል ጥላቻ እንዲነግስ መስራት ጠባብነት ነው።

አንድን ህዝብ የበላይነት ሊይዝ አይችልም። አንድን ቡድን ግን በአንድን ህዝብ ስም በመነገድ ሌሎችን ሊበድል ይችላል። የሰው የበላይነት (በህዝቦች ላይ) ሊተገብር ይችላል። ህዝብ እንደ ህዝብ ግን ሌላውን ህዝብ ሊበድል አይችልም። ህወሓት የትግራይን ህዝብ እንደሚወክል ይነግረናል። የትግራይን ህዝብ እወክላለሁ እያለ ሌሎች ህዝቦች (የትግራይን ጨምሮ) ይበድላል። ሌሎች ህዝቦች (የትግራይ ዉጭ ያሉ ኢትዮጵያውያን) ደግሞ በህወሓት ስርዓት ሲበደሉ በትግራይ ህዝብ የተበደሉ አድርገው ያስባሉ። ግን ስህተት ነው። መታረም አለበት። የትግራይ ህዝብ ለራሱ በህወሓት አገዛዝ የሚበደል ነውና።

“የአማራ የበላይነት” የሚባለው የህወሓት በሽታ እስካሁን ፈውስ አላገኘም። በመርህ ደረጃ ህዝብን ዒላማ አድርጎ ህዝብን ለመታገል መነሳት ስህተት ነው ብያለሁ። በፖለቲካ ህዝብን ዒላማ አይደረግም። ምክንያቱም የፖለቲካ ዓላማ ህዝብን ማገልገል እንጂ ህዝብን መጨቆን አይደለም። ስለዚህ ህዝብን የመበደል ዓላማ መያዝም መተግበርም የህሊና ወንጀል ነው። ህወሓቶች ይህን በሽታ (“የአማራ የበላይነት” መፈክር) አልተዋቸውም። አሁንም “ፀረ አማራ” እንቅስቃሴዎች አሉ። የህወሓት የአሁኑ ስትራተጂ “እኛ ከስልጣን የምንወርድ ከሆነ ከአማራ ጋር አብረን አንቀጥልም” የሚል ገንጣይ አስተሳሰብ እያራመዱ ይገኛሉ። “እኔ ከሌለሁ ሠርዶ አይብቀል …” ዓይነት ስትራተጂ መሆኑ ነው። በጣም የሚገርመው ነገር ፀረ ብአዴንም መነሳታቸው ነው። ለነሱ ከስልጣን ከሚወርዱ ኢትዮጵያ ብትበታተንና ትግራይን አስገንጥለው ትግራይን እየጨቆኑ ቢገዙ ይመርጣሉ።

ግን ይህን “አማራ” የሚባል ህዝብ መቼ ይሆን የበላይነት ይዞ ሌሎች ህዝቦችን የበደለው? አንድን ህዝብ እንዴት ሌላውን ህዝብ ይበድላል? ህዝብ ህዝብን ሊበድል አይችልም። ምክንያቱም አንድን ህዝብ ሌላውን ህዝብ መበደል ከጀመረ (ከቻለ) ህዝብ መሆኑ ቀርቶ ገዢ መደብ (elite) ሁነዋል ማለት ነው። ገዢ መደብ ከሆነ ደግሞ ህዝብ አይደለም። ገዢ መደብ ስርዓት ነው። ህዝብና ስርዓት ደግሞ ይለያያሉ።

ምናልባት የህዝብ የበላይነት አለ የምንለው ህዝብን የሚያስተዳደር (የሚገዛ) ስርዓት ከህዝቡ የወጣ ሲሆን ይሆን? ይህም አሳማኝ አይደለም። ምክንያቱም ገዢ ሁሌ ከህዝቡ ነው የሚወጣው (የቅኝ ግዛት ካልሆነ በስተቀየር)፤ ገዢ ከህዝቡ እንጂ ከማርስ አይመጣም። የኢትዮጵያ መሪ ከኢትዮጵያ ህዝብ ይወጣል። በኢትዮጵያ ብዙ ብሄሮችና ብሄረሰቦች አሉ። ስርዓቱ ከሁሉም ህዝቦች ሰዎች ይኖሩታል። መሪ ግን አንድ ነው የሚሆነው። ያ አንድ ሰው (መሪው) ከአንድ ብሄር ሊሆን ይችላል። ያ አንድ ሰው ስልጣኑ ተጠቅሞ ሌሎች ህዝቦችን ሊበደል (ወይ ሊጠቅም) ይችላል። ሰውየው የፈጠረው ስርዓት ለህዝቡ ቢጎዳም ቢጠምም ከስርዓቱ ይገናኛል እንጂ መሪው ከመጣበት ብሄር ጋር አይገናኝም። ስለዚህ ገዢዎች የሚወክሉት የፈጠሩትን ስርዓት እንጂ የመጡበትን ብሄር አይደለም።

የደርግ ስርዓት ሲበድለን፣ “አማራ በድሎናል” ይሉናል። የኃይለስላሴ ስርዓት ሲበድለን “አማራ በድሎናል” ይሉናል። የምኒሊክ ስርዓት ሲበድለን “አማራ በድሎናል” አሉን። የህወሓት ስርዓት ሲበድለንስ ማን በደለን ሊሉን ነው? የትግራይ ህዝብ? አይሆንም። ምክንያቱም የትግራይ ህዝብ የትግራይን ህዝብ ይበድላል? አንድን ህዝብ ራሱን ይበድላል? በደል ሁሉ ወደ አማራ ህዝብ ለምን? ስርዓትና ህዝብ ማገናኘት የፖለቲካ ኪሳራ ያስከትላል።

ግን እስቲ ይሁን፤ መሪዎች የመጡበትን ብሄር ይወክላሉ እንበል (ስህተት ቢሆንም)። እነሱ (መሪዎቹ) ሲበድሉ የመጡበት ብሄር በበዳይነት ተፈርጆ እንደ ጠላት ይቆጠር እንበል። የአማራ ህዝብ መቼ ይሆን በመሪዎቹ አድርጎ ሌሎች ህዝቦችን የገዛ (የበደለ)? ያለፉ ጨቋኝ ስርዓቶች አማራ ነበሩ ያለው ማነው? አማርኛ የተናገረ ሁሉ አማራ አይደለም። እስቲ የዘመናዊቷ ኢትዮጵያ መሪዎች እንመልከት።

ብዙ ግዜ የዘመናዊቷ ኢትዮጵያ ታሪክ የሚጀምረው ከአፄ ቴድሮስ ነው (ወይም ከዚሁ እንጀምር! ምክንያቱም ከአፄ ቴድሮስ በፊት ኢትዮጵያ በመሳፍንቶች ነበር የምትተዳደረው። በዘመነ መሳፍንት መሳፍንቶች የራሳቸውን ህዝብ (ብሄር) ይገዙና ይበድሉ ነበር)። “አማራ” ተብሎ ከተሰየመው አከባቢ የሚወለድ ገዢ ቴድሮስ ነው። አፄ ቴድሮስ ኢትዮጵያ አንድ ለማድረግ በዛን ግዜ የነበሩ መሳፍንቶች ተዋጉ። አፄ ቴድሮስ ዉግያው የጀመሩት በአማራ መሳፍንቶች (የጎጃም፣ ወሎና ጎንደር) ነበር። ቴድሮስ “ከአማራ ስለመጣሁ፣ አማራ ስለምወክል፣ የአማራ መሳፍንቶች ማጥፋት የለብኝም” አላሉም። (ህወሓት ለትግራይ መሳፍንቶች እንዳደረገው ሁሉ)። ስለዚህ አፄ ቴድሮስ አማራን ወክለው ሌላው ኢትዮጵያዊ አልበደሉም (ከበደሉም ለሁሉም ነው)። ስለዚህ “በአማራ ህዝብ ተገዛን” የሚለው ክስ “በአፄ ቴድሮስ ተገዛን” የሚል እንደማይሆን ተስፋ አደርጋለሁ።

የአማራ ተወላጅ የሆነ የኢትዮጵያ ገዢ ቴድሮስ ብቻ ነው ብዬ አስባለሁ (ጉዳዩ ለታሪክ ተመራማሪዎች ልተወው እንዳልሳሳት፤ ከተሳሳትኩ እታረማለሁ)። ዮሃንስ አማራ አልነበረም፣ ምኒሊክ አማራ አልነበረም፣ ኃይለስላሴ አማራ አልነበረም፣ መንግስቱ አማራ አልነበረም፣ መለስ አማራ አልነበረም፣ ኃይለማርያም አማራ አይደለም። ማነው አማራ?

ምናልባት “የአማራ ገዢዎች” የምንለው ግለሰቦቹ (ንጉሶቹና መሪዎቹ) ሳይሆን ስርዓቱ ነው ካልን ያው ስርዓቱማ ከሁሉም ህዝቦች ተወካዮች አሉበት። አማራ ለብቻው ገዥ ነበር ማለት አንችልም። ምናልባት ገዢዎቹ አማርኛ ስለሚናገሩ ነው ካልን ደግሞ አማርኛ የተናገረ ሁሉ አማራ አይደለም። አቶ መለስም አማርኛ ይናገር ነበር። አፄ ዮሃንስም አማርኛ ይናገሩ ነበር (አማርኛ የኢትዮጵያ ኦፊሽየላዊ የስራ ቋንቋ እንዲሆን የወሰኑት አፄ ዮሃንስ ናቸው የሚል መረጃ አለኝ፤ ‘መረጃ’ እንጂ ‘ማስረጃ’ አላልኩም)።

የአማራ ህዝብ እንደ ማንኛው የኢትዮጵያ ህዝብ በኢትዮጵያ ገዢዎች ሲሰቃይ የነበረ ነው። ባልበላበት በልተሃል፣ ባልገዛበት ገዝተሃል ሲባል ይገርማል፤ ልክ እንደ ትግራይ ህዝብ። የትግራይ ህዝብ ሳይበላ በልተሃል፣ ሳይገዛ ገዝተሃል ይባላል፤ ህወሓት በበላው፣ ህወሓት በገዛው። ህወሓት ትግርኛ ተናጋሪ ስለሆነ ከትግራይ ህዝብ ጋር የሚያገናኘው ነገር የለም (በፖለቲካ መልኩ)። ያለፉ ገዢዎች አማርኛ ስለሚናገሩ ከአማራ ህዝብ ጋር የሚያገናኛቸው ነገር የለም። ህዝብ ሌላ ገዢ ሌላ።

ባጭሩ ፀረ ህዝብ አቋም መያዝ ተገቢ አይደለም (ለማንኛውም ህዝብ)። ሰው የፈለገውን የፖለቲካ አመለካከት መያዝ ይችላል። “የቀድሞ ስርዓት አባላት …” ምናምን እያልን አንፈርጅ። የህወሓት አባላት ለሌሎች ሰዎች የቀድሞ ስርዓት አባላት፣ ናፋቂዎች ወዘተ እያላቹ ስትፈርጁ እናንተም ራሳችሁ ከህወሓት ስርዓት በኋላ “የቀድሞ ስርዓት አባላት ..” ምናምን እየተባላቹ ስማቹ ይጠፋል፣ የፈለጋችሁን የፖለቲካ ፓርቲ አባል የመሆን መብታቹ ይገደባል። አሁን በሌሎች ላይ የምትፈፅሙትን ስም የማጥፋት ተግባር በናንተ (በራሳቹ) ይፈፀማል።

ስለዚህ እናስተውል። ከጥላቻ ፍቅር ይሻለናል። ጥላቻ ይውደም። አሜን!

It is so!!!

No comments:

Post a Comment