January 18/2014
” ብአዴን የህወሀት በቅሎ መሆኑ ያብቃ” የብአዴን አባላት
” ብአዴን የህወሀት በቅሎ መሆኑ ያብቃ” የብአዴን አባላት
ባለፈው ወር በአማራ ክልል ርዕሰ ከተማ ባህርዳር የተካሄደውን የብአዴን እና የኢህአዴግ ከፍተኛ አመራሮች ስብሰባ ላይ የተላለፈውን ውሳኔ ተከትሎ የዞን እና የወረዳ የድርጅት ጉዳይ ሃላፊዎች ኢህአዴግ አሸባሪ እያለ ከሚጠራቸው የፖለቲካ ድርጅቶች ጋር በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ ግንኙነት ይኖራቸዋል ተብሎ በሚጠረጠሩት ወጣቶች ላይ የቁጥጥር ዘመቻ እንዲካሄዱ ትእዛዝ ተላልፎላቸዋል።
ጥር 8፣ 2006 ዓም በሁሉም የአማራ ክልል ወረዳዎች በተደረገው የብአዴን ስብሰባ ላይ ወጣቶች መረጃ በማስተላለፍ እና ለአሸባሪዎች መሳሪያ የሚሆኑ ሰዎችን በመመልመል ላይ በመሆናቸው የግንኙነት ሰንሰለቱን ለመበጠስ አባላቱና አመራሩ ጠንክረው መስራት እንደሚገባቸው ተገልጾላቸዋል። እያንዳንዱ አባል በአሸባሪዎች ፕሮፓጋንዳ ሳይዘነጋ ጠንክሮ እንዲሰራም ትእዛዝ ተላልፎለታል።
“ከየትኛውም የሀገሪቱ ክልል ወጣቶች ባላይ የአማራ ክልል ወጣቶች ከአሸባሪዎች ጋር ግንኙነት እንዳላቸው መረጃ አለኝ” ያለው ኢህአዴግ በክልሉ እነዚህን ወጣቶች የመቆጣጠርና የመከታተል ዘመቻ በዘርፈ ብዙ ስልቶች ታጅቦ መካሄድ እንዳለበት አሳስቧል።
“በመሰረተ ቢስ አሉባልታዎች ከኢህአዴግ የኮበለሉና ወስጣቸው የሸፈተ የብአዴን አባላትም ሀቁን ተገንዝበው ከኢህአዴግ ጋር እንዲቀጥሉና ሀገሪቱን ወደ ላቀ እድገት እንዲያሸጋግሩ የድርጅት ጉዳይ ሀላፊዎች በስብሰባው ላይ ተናግረዋል፡፡
የመወያያ አጀንዳዎች ትምህርትና የመኖሪያ ቤት ሊዝ ጉዳይ ቢሆኑም የስብሰባው ውሎ ግን ከአጀንዳዎች ውጭ አሸባሪዎች በሚሏቸው አካላት ላይ ነበር ያሉት ስማቸው እንዳይገለፅ የፈለጉ የድርጅት አባላት፣ መንግስት በመኖሪያ ቤት ሊዝ ያቀረበው ጉዳይ ግን ከፍተኛ ተቀዋውሞ አስነስቷል ብለዋል፡፡ ህጉ የማንንም ኢትዮጵያዊ ምጣኔ ሀብታዊ አቅም ያላገናዘበ፣በአሰራር ውጣ ውረድ የተበተበና በዘፈቀደ እንዲወጣ የተደረገ ይመስላል ያሉት አባላቱ በተለይ የመንግስት ሠራተኞችን ከጨዋታ ውጭ ያደረገ ነው ብለዋል፡፡
አዲሱ የክልሉ ፕሬዚዳንት አቶ ገዱ አንዳርጋቸው ከብአዴን እየኮበለለ የሚጠፋውንና ለአሸባሪዎች መጠቀሚያ እየዋለ ነው ያሉትን ሃይል እንቅስቃሴ ለመግታት እርምጃ መውሰድ መጀመራቸውንም የሚደርሱን መረጃዎች ያመለክታሉ።
በአማራ ክልል የሚገኙ ወጣቶችና የብአዴን አባላት ” ብአዴን የህወሀት በቅሎ መሆኑ ያብቃ” በማለት ጥያቄዎችን እያነሱ ነው።
በክልሉ ውስጥ የተንሰራፋው ሙስና፣ የመልካም አስተዳደር እጦትና አፈና መባባስ አባላቱን ለተስፋ መቁረጥ መዳረጉንም ወጣቶች ይናገራሉ።
No comments:
Post a Comment