Saturday, January 25, 2014

የሁለት አመት ህዝባዊ ንቅናቄ ዛሬም ተደገመ! (ድምፃችን ይሰማ)

January 24, 2014

የትግላችን ማረፊያ ድል ብቻ መሆኑን ዛሬም አውጀናል!

አርብ ጥር 16/2006
Ethiopian Muslims protest Jan 23, 2014
የዛሬዋ እለት ለህዝበ ሙስሊሙ ካለፉት ስድስት ወራት ለየት ያለ ክስተትን አስተናግዳ ያለፈች ጁሙዓ ነች፡፡ ህዝበ ሙስሊሙ ላለፉት ስድስት ወራት ለመንግስት በጥሞና የማሰቢያ ጊዜ ለመስጠት ከማንኛውም የአደባባይ የተቃውሞ ስነ ስርአቶች ተቆጥቦ ቆይቶ ነበር፡፡ መንግስት የእፎይታ ጊዜውን በአግባቡ ሊጠቀም ያለመፍቀዱ እንዳለ ሆኖ የሰላማዊ ትግሉን ሁለተኛ አመት ለማሰብም ‹‹730 ቀናት ለሃይማኖት ነጻነት›› በሚል ለሁለት ሳምንታት የሚቆይ ዘመቻ ታውጇል፡፡ የዛሬዋ ጁሙአ የዘመቻው ኦፊሴላዊ መክፈቻ ነበረች – ደማቅ መክፈቻ! ህዝበ ሙስሊሙ በበርካታ የአገሪቱ ከተሞች በሚገኙና የትግሉን መንፈስ አማክለው በቆዩ መስጊዶች በከፍተኛ ቁጥር ተሰባስቦ በመስገድ ለትግሉ ቀጣይ እርከን ሙሉ ዝግጁነቱን በከፍተኛ ወኔ አሳይቷል፡፡
በአዲስ አበባ አንዋር መስጂድ ከጁምአው አስቀድሞ መምጣት የጀመረው ከፍተኛ ቁጥር ያለው ህዝብ አንዋርና አካባቢውን ለመሙላት ቅጽበትም አልወሰደበትም፡፡ የህዝቡ ቁጥር እንዲታይ ያልፈለጉት ፖሊሶች እንደተለመደው መኪኖችን ለህዝቡ በማስቆምና መስገጃውን እንዲያነጥፍ በመፍቀድ ፋንታ ለመከልከልና ግርግር ለመፍጠር የሞከሩ ሲሆን ለማረጋጋት የሞከሩ ወጣቶችንም ለማሰር ሙከራ አድርገው ሳይሳካላቸው ቀርቷል፡፡ መዲና ህንጻ ላይ የኢቲቪ ካሜራዎች ተደግነው ህዝቡን ሲቀርጹ የነበሩ ሲሆን ህዝቡም በመሸማቀቅ ፋንታ እነሱኑ መልሶ ሲቀርጻቸው ማየት በእርግጥም አስገራሚ ነበር፡፡ ከጁምአው ስግደት በኋላ ደማቅ የዱአ ስነስርአት ተደርጎ ሰው የተበተነ ሲሆን በመምጫና መመለሻ ሰአቶችም በድልና ነስር ኒያ የአንድ ብር ሰደቃ ለችግረኞች ተሰጥቷል፡፡ በሺዎች ፊት ላይ ይታይ የነበረው ደስታና የማይሸነፍ ወኔ በእጅጉ ማራኪ እንደነበር ሁላችንም እዚያው የመሰከርነው የትግላችን ደማቅ ትእይንት ነበር፡፡
የክልል ከተሞችም እንዲሁ በከፍተኛ ድምቀት መርሀ ግብሩን አከናውነዋል፡፡ ለአዲስ አበባ አጎራባች በሆነችው አዳማ ከተማ አቡበክር መስጂድ በህዝበ ሙስሊሙ አሸብርቆ መዋሉና የዱዓና የሰደቃ ፕሮግራሙም ባማረ ሁኔታ መጠናቀቁን ማወቅ ተችሏል፡፡ በተመሳሳይ በጂማ ፈትህ መስጂድ ደማቅ ሆነ የዱአና የሰደቃ ፕሮግራም የተካሄደ ሲሆን በቀደሙ ደማቅ ተቃውሞዎቻቸው የሚታወቁት ሻሸመኔና መቱ ከተማም በደማቅ ሁኔታ ለትግሉ ያላቸውን አጋርነት ገልጸው አልፈዋል፡፡
ካሁን ቀደም የመንግስት የሀይል እርምጃ ሰለባ የነበረችው አጋሮ ከተማም በአል አዝሀር መስጂድ ላይ በከፍተኛ ቁጥር ለጁምአ በተገኘው ህዝበ ሙስሊም ዱአና ሰደቃ ደምቃ ውላለች፡፡ በዚያው በኦሮሚያ ክልል በደሌ ከተማ የሚገኘው መስጂደ ራህማ ላይም ተመሳሳይ ደማቅ ፕሮግራም ተካሂዶ የዋለ መሆኑ ተዘግቧል፡፡
ካሁን ቀደም በራሷና በሀምሳ ያክል በዙሪያዋ በሚገኙ ወረዳዎች ላይ አስገራሚ ተቃውሞ ያካሄደችው ዶዶላ ከተማም በፈትህ መስጂድ ላይ ከፍተኛ ቁጥር ያለውን ህዝበ ሙስሊም አስተናግዳ ውላለች፡፡ በዶዶላ በኢማሙ አማካኝነት ከሰላት በፊት አላህ ትግሉን ለድል እንዲያበቃው ዱአ የተደረገ ሲሆን ሰደቃውም በተሳካ ሁኔታ ተካሂዷል፡፡ ዶዶላ በጥልቅ ዱአ ውስጥ ሆና ሳለች በርቀት በደምቢ ከተማ የሚገኙ ሙስሊም ነዋሪዎች ደግሞ በታላቁ መስጂዳቸው ተሰባስበው ተመሳሳይ የአጋርነት ፕሮግራም እያካሄዱ ነበር፡፡
በግዙፍ የቀደሙ ተቃውሞዎቿ የምትታወቀው ወልቂጤም የዛሬው የጁምአ ውሎ ተጋሪ ነበረች፡፡ በረቢእ መስጂድ የተሰባሰቡ ምእመኖቿ የኢትዮጵያ ሙስሊሞች ትግል አጋር መሆናቸውን አስመስክረውባት ውለዋል፡፡
ገና በማለዳው ከ 50 ሺህ በላይ በራሪ ወረቀቶች ተበትነው ያደሩባት የደሴ ከተማም በዳውዶ መስጂድ በተሰባሰቡ ሙስሊም ነዋሪዎቿ አማካኝነት እስከ ድል ጫፍ የሚያብበውን የትግል ስሜት ያሳየች ሲሆን የዱአና የሰደቃ ፕሮግራሙም በድምቀት ተካሂዶባታል፡፡ በተመሳሳይ ሰአት በኸሚሴ ኹለፋኡ ራሺዲንም ደማቅ የዱአና የሰደቃ ፕሮግራም ተካሂዶ መዋሉ ታውቋል፡፡
በምስራቅ ኢትዮጵያ በሐረር ከተማ 4ኛ ኢማን መስጂድ፣ በአፋር ሎጊያ ከተማና በድሬዳዋ ከተማ አሸዋ ቢላል መስጂድ የተሰባሰቡ ሙስሊም ነዋሪዎችም ደማቅ የዱአና የሰደቃ ስነስርአት አድርገው ተመልሰዋል፡፡ በተመሳሳይ በሐዋሳ ከተማ ዐረብ መስጂድና ቤሎችም በርካታ ከተሞች ህዝበ ሙስሊሙ ዳግም ድምጹ አንድ መሆኑንና ወኔውም አንዳች እንዳልጎደለ ያለማወላወል አረጋግጦ አልፏል፡፡ /በተለያዩ የውጭ አገራት ከተሞች የተደረጉ ፕሮግራሞችን ለብቻ የምናወሳቸው ይሆናል!/
የዛሬው ስኬታማ መርሀ ግብር በተለያዩ ከተሞችና መስጂዶች የተደረገ ቢሆንም ያስተላለፈው መልእክት ግን አንድ እና አንድ ነው፡፡ ያም ህዝበ ሙስሊሙ ከድል ደጃፍ ሳይደርስ በምንም መልኩ ሰላማዊ ትግሉን እንደማያቆም ነው፡፡ ህዝበ ሙስሊሙ ዲኑ ላይ የሚሰነዘረውን ጥቃት እየተመለከተ እንዴትስ እጁን አጣጥፎ ሊቀመጥ ይችላል? ህዝብ የአገር ዋነኛ መሰረት መሆኑ እየታወቀ የሚፈጸምበትን በደል ተቋቁሞ የጥሞና ጊዜ መስጠቱስ እንደምን በስህተት ሊተረጎም ተገቢ ሆነ? አዎን! የዛሬው ከረጅም የጥሞና ጊዜ በኋላ የተደረገው መርሀ ግብር መልሶ ያለፈው እኒህን ጥያቄዎች ነው፡፡ ህዝብ እንደማይሸነፍና መንግስትም ለህዝብ ፍላጎት በትክክል ተገዥ እስኪሆን ድረስ ሰላማዊ ትግሉ እንደማይገታ፣ ብሎም ለድል መብቃቱ እንደማይቀር ልቦና ላለው ሁሉ ያስገነዝባል፡፡
በቀጣዮቹ ሁለት ሳምንታት የሚኖሩት መርሃ ግብሮች በሙሉ የሁለት አመት ትግላችንን በመንፈስም በተግባርም ድጋሚ እንድናልፍባቸው የታሰቡ ናቸው፡፡ ይህንን ደግሞ ዛሬ ‹‹ሀ›› ብለን ስንጀምር በህዝብ ውስጥ የተቀጣጠለ ቁጣ መብረጃው ድል ብቻ እንደሆነ ባመለካተ ህዝባዊ ወኔ ነው፡፡ ቀጣዩ የትግላችን ጉዞ እንቀደሙት ሁሉ ህዝባዊ መሰረቱን ይዞ ይቀጥላል፡፡ አሁን የምንገኝበት የእፎይታ ጊዜ በትግላችን ውስጥ እንዳለፉት እና እንደሚመጡት ምዕራፎች አንዱ ወሳኝ እርከን ነው፡፡ የእፎይታ ጊዜውን በዓላማው አምኖበት እና ለኢስላማዊ አንድነት ቅድሚያ ሰጥቶ፣ የመንግስት ግብታዊ አካሄድ እና ለከት የለሽ የጭቆና መብዛት የፈጠሩበትን ቁጣ ዋጥ አድርጎ ለመርሁ ተገዥ የሆነው መላው ሙስሊም ማህበረሰብ ‹‹የጀግኖች ጀግና›› ቢባል ያንሰው ይሆን?
በትግል ላይ መስዋእት መሆን እና በትእግስት መፅናት ሁሉም የአንድ ትግል ማዕዘናት ናቸው፡፡ ይህን መስፈርት ደግሞ ኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች በተግባር እያሳየን እንገኛለን፡፡ ላለፉት ሁለት አመታት በጀግንነት እና በመሰዋእትነት ፀንተናል፡፡ ዛሬ ደግሞ የቀደመውን ጀግንነታችንን እንደያዝን በትግል ቃልኪዳናችን ፀንተናል፤ ወደፊትም እስከድል ደጃፎች ድረስ ጸንተን እንቀጥላለን፤ ድልም ከአላህ እንጂ ከሌላ አይደለምና!
‹‹ሁለት ጁሙአዎችን በሁለት አመት የትግል ወኔ!››
ድምጻችን ይሰማ!
አላሁ አክበር!

No comments:

Post a Comment