Friday, January 24, 2014

የውጭ ኢንቨስተሮች የመንግሥት ተቋማት ለሙስና የተጋለጡ ናቸው አሉ

January 24/2014

በኢትዮጵያ ኢንቨስት በማድረግ ላይ የሚገኙ የውጭ ኢንቨስተሮች በሙስና ላይ ስላላቸው አመለካከት ለማወቅ በተካሄደ ረቂቅ ጥናት አብዛኛዎቹ ኢንቨስተሮች መንግሥት የሚያካሂዳቸው ግዥዎች ግልጽነት እንደሚጎላቸው አመለከቱ፡፡

በመንግሥት ተቋማት ጉዳይን ለማስፈጸም ከፍተኛ ሙስና መኖሩን ገለጹ፡፡

የፌዴራል የሥነ ምግባርና የፀረ ሙስና ኮሚሽን ከለጋሾች ባገኘው የገንዘብ ድጋፍ ሰላም ዴቨሎፕመንት በተባለ ኩባንያ አማካይነት ባስጠናው ረቂቅ ጥናት፣ መንግሥት የሚያካሂዳቸው ግዥዎችና ኮንትራቶች ግልጽነት እንደሚጎድላቸው ኢንቨስተሮቹ አመልክተዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ለረቂቅ ጥናቱ ምላሽ የሰጡ የውጭ ኢንቨስተሮች አራት አገልግሎት ሰጪ መሥሪያ ቤቶችን ከፍተኛ ሙሰኞች ብለዋቸዋል፡፡ በረቂቅ ጥናቱ ላይ ዛሬ በሒልተን ሆቴል ውይይት ይደረጋል፡፡

በኢትዮጵያ ኢንቨስት በማድረግ ላይ የሚገኙ 350 ኩባንያዎችን ቃለ መጠይቅ በማድረግ ረቂቅ ጥናቱ ተዘጋጅቷል፡፡ ኢንቨስተሮቹ ከላቲን አሜሪካና ከአንታርቲካ በስተቀር 42 አገሮችን የሚወክሉ ናቸው፡፡

ጥናቱ በሦስት ጉዳዮች ላይ ያነጣጠረ ሲሆን፣ እነሱም ሕግና ደንብ፣ የቢሮክራሲ ማነቆና ቢዝነስ ለመሥራት ያለው ቅለትና የሙስና ሁኔታ ናቸው፡፡

ከ350 ምላሽ የሰጡ ኢንቨስተሮች መካከል 20 በመቶ የሚሆኑት የመንግሥት የግዥ ኮንትራቶች ክፍያ የሚፈጸመው ግልጽ ባልሆነ መንገድ ነው ይላሉ፡፡ አገሪቱ ውስጥ ቢዝነስን ለማቀላጠፍ አስቸጋሪ መሆኑን የገለጹት ደግሞ 71 በመቶ የሚሆኑት ናቸው፡፡ ለዚህ በዋናነት ያነሱት ምክንያት ሙስና መንሰራፋቱን ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ውስብስብ የሆነውን የግዥ ሒደት በእንቅፋትነት ጠቅሰዋል፡፡

በሌላ በኩል 67.4 በመቶ የሚሆኑ ምላሽ የሰጡ ኢንቨስተሮች በበኩላቸው፣ በቢሮክራሲ ምክንያት የሚገጥሙዋቸውን ችግሮቻቸውን ለመፍታት ለመንግሥት ባለሥልጣናትና ሠራተኞች ጉቦ እንደሚሰጡ ሲገልጹ፣ የተወሰኑት ደግሞ ጉዳያቸውን በፍጥነት ለማስፈጸም ጉቦ ከመስጠት ሌላ አማራጭ ስለሌላቸው ጉቦ እንደሚሰጡ በረቂቅ ጥናቱ ተመልክቷል፡፡

እነዚህ ኢንቨስተሮች በመንግሥት አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ላይ ያላቸው የሙስና ደረጃ በጥናቱ በመቶኛ ተገልጿል፡፡

በረቂቅ ጥናቱ ምላሽ ከሰጡት መካከል 18.9 በመቶ ያህሉ የኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን፣ 8.3 በመቶ ትራንስፖርት ባለሥልጣን፣ 7.4 በመቶ የመሬት አስተዳደርና 6.5 በመቶ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ኮርፖሬሽን ከፍተኛ ጉቦኛ መሥሪያ ቤቶች ናቸው በማለት ገልጸዋቸዋል፡፡ ይህ ረቂቅ ጥናት ዛሬ በሒልተን ሆቴል ውይይት እንደሚደረግበት ታውቋል፡፡

የፀረ ሙስና ኮሚሽን ቀደም ሲል ኪሊማንጃሮ በተባለ የውጭ አገር አማካሪ ኩባንያ አማካይነት ባካሄደው ጥናት፣ ኢትዮጵያውያን በአገሪቱ ስላለው የሙስና ሁኔታ ላይ ያላቸውን አስተያየት ማቅረቡ አይዘነጋም፡፡

በዚህ ጥናት በፍትሕ አካላትና በበርካታ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ላይ ጥያቄ የቀረበላቸው የኅብረተሰብ ክፍሎች በተቋማቱ ላይ እምነት እንደሌላቸው መግለጻቸው ይታወሳል፡፡  

No comments:

Post a Comment