Wednesday, January 1, 2014

አራት የፌዴራል ፖሊስ አባላት በግድያ ወንጀል ጥፋተኛ ተብለው ታሰሩ

Janaury1/2014
በቂም በቀል ተነሳስተውና አስበው፤ አንድን ሰው በእንጨት ዱላ ደብደበው ገድለዋል ሲል የፌዴራሉ ዐቃቤ ሕግ ክስ የመሰረተባቸው አራት የፌዴራል ፖሊስ አባላት ጥፋተኛ ሆነው በመገኘታቸው በ6 ዓመት ከ7 ወራት እና በ5 ዓመት ከ6 ወር ፅኑ እስራት እንዲቀጡ የፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት 3ኛ ወንጀል ችሎት በትናንትናው ዕለት የቅጣት ውሳኔ ሰጠ።
አንደኛ ተከሳሽ ምክትል ሳጅን ብሩክ ሽፈራው፣ ሁለተኛ ተከሳሽ ኮንስታብል ኃይላይ አርአያ፣ ሶስተኛ ተከሳሽ ኮንስታብል ፀጋዬ ወ/አረጋይ እና አራተኛ ተከሳሽ ሆነው የቀረቡት ኮንስታብል ታዬ ጭንዲን የፌዴራሉ ዐቃቤ ሕግ የመሰረተባቸው ክስ ሁለት ሲሆን፤ በ1ኛው ክስ ስር አንደኛ፣ ሁለተኛ እና ሶስተኛ ተከሳሾች ላይ የቀረበው ዝርዝር፣ ተከሳሾቹ በዋና ወንጀል አድራጊነት ተካፋይ በመሆን ሰውን ለመግደል አስበው ሰኔ 2 ቀን 2004 ዓ.ም በግምት ከሌሊቱ 6 ሰዓት ሲሆን በአዲስ አበባ ከተማ በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ቀበሌ 09/14 ልዩ ቦታው ጎፋ ማዞሪያ አካባቢ ጨካኝነታቸውን በሚያሳይ ሁኔታ 1ኛ ተከሳሽ ምክትል ሳጅን ብሩክ ሽፈራው ሟች ሃሚድ ወዳጆን በእንጨት ዱላ ጭንቅላቱን እና ጀርባውን ደጋግሞ ሲመታው፤ 2ኛ እና 3ኛ ተከሳሾችም የሟችን ጭንቅላት በዱላ በመምታት ጉዳት እንዲደርስበት ከማድረጋቸውም በተጨማሪ ራሱን በመከላከል በማይችልበት ሁኔታ በመግደላቸው በፈፀሙት ከባድ የሰው መግደል ወንጀል ተከሰዋል ይላል።
የፌዴራሉ ዐቃቤ ሕግ በ2ኛ ክስ ዝርዝር ስር የጠቀሰው አራተኛ ተከሳሽ ኮንስታብል ታዬ ጭንዲን ሲሆን፤ ኮንስታብሉ ከ1ኛ እስከ 3ኛ ያሉትን ተከሳሾች ለመርዳት አስቦ ከላይ በክሱ የተጠቀሰው ድርጊት ሲፈጸም የሟች ሀሚድ ወዳጆ ሶስት ጓደኞች ለመገላገል ሲሉ የታጠቀውን ክላሽ በመደገን እንዳይገላግሉ የከለከላቸው በመሆኑ በፈፀመው አባሪ በመሆን ከባድ የሰው መግደል ወንጀል ተከሷል ሲል ያትታል።
በዐቃቤ ሕግ የቅጣት ማክበጃነት የቀረበው ተከሳሾቹ የፖሊስ አባል ሆነው ህግና አሰራርን እያወቁ ተቃራኒ በሆነ መንገድ ወንጀል መፈፀማቸውና በግብረ አበርነት ጭካኔ የተሞላበት ድርጊት መፈፀማቸው የወንጀሉን ከባድነት ያሳያል ብሏል። ተከሳሾቹ በበኩላቸው እንደቅጣት ማቅለያ ያቀረቡት ሀሳብ ከዚህ ቀደም የወንጀል ሪከርድ የሌለባቸው መሆኑንና የቤተሰብ አስተዳዳሪዎች መሆናቸውን ሲሆን ፍርድ ቤቱም የሁለቱንም ወገኖች ሀሳብ ተቀብሎ መርምሯል።
የግራቀኙን የክስ ክርክር ሲያደምጥ የቆየው የፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት 3ኛ ወንጀል ችሎት አራቱንም የፌዴራል ፖሊስ አባላት በፈፀሙት ወንጀል ጥፋተኛ ናቸው ያለ ሲሆን፤ በትናንትናው ዕለት (ታህሳስ 22 ቀን 2006 ዓ.ም) ደግሞ 1ኛ እና 2ኛ ተከሳሾችን በ6 ዓመት ከ7 ወር ፅኑ እስራት ሲቀጣ 3ኛ እና 4ኛ ተከሳሾችን በ5ዓመት ከ6 ወር ፅኑ እስራት እንዲቀጡ ወስኖባቸዋል።


No comments:

Post a Comment