Tuesday, December 31, 2013

በዶ/ር ብርሃኑ ነጋ “ዴሞክራሲና ሁለንተናዊ ልማት በኢትዮጵያ”ና በሁለት ተጨማሪ መጽሀፎች ላይ የቀረበ አጭር አስተያየት – ከፋሲል የኔዓለም (ጋዜጠኛ)

December 31/2013

በፖለቲካው ዓለም ጉልህ ስፍራ ያላቸው ዶ/ር ብርሃኑ ነጋ “ዲሞክራሲና ሁለንተናዊ ልማት በኢትዮጵያ” በሚል ርዕስ የጻፉትን አዲስ መጽሃፍ ያነበብኩት ዘግይቼ ነው ፤ ለመዘግየቴ ሶስት መሰራታዊ ምክንያቶች ነበሩኝ፣ አንዱና ዋናው ዶ/ሩ በተለያዩ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚ ጉዳዮች ላይ ያላቸውን አመለካከት በመገናኛ ብዙሃን በስፋት ስላቀረቡ በመጽሀፉ ውስጥ እምብዛም አዲስ ነገር ያቀርባሉ የሚል እምነት ስላልነበረኝ ነው። ሁለተኛው ምክንያት ደግሞ ዶ/ሩ ራሳቸው በከፊል የጠቀሱት ነው፣ “ በአገሪቱ ለዲሞክራሲያዊ ስርዓት የሚደረገው ትግል ውስጥ ጉልህ ሚና እየተጫወተ ያለ የተቃዋሚ ድርጅት አመራር አባል መሆኑን ሲመለከት፣ ከቅንጦትም ባሻገር በተወሰነ ደረጃ “ የስራ ፈትነት” ወይንም የበለጠ ጠርጣራ ( cynic) ለሆነ ሰው “ በተግባር ስራ ለመስራት ካለመቻል “ የመጣ፤ ተግባራዊ ድክመትን ለመሸፈን የሚደረግ ሙከራ ሊመስል ይችላል” የሚለው ነው። ሶስተኛው ምክንያቴ ደግሞ ፣ ፋሽን በሚመስል መልኩ በአገር ቤት የሚኖሩ ፖለቲከኞች በተከታታይ መጽሃፎችን በማሳተማቸው ለእነሱ ቅድሚያ ለመስጠት በመፈለግ ነው።

ዶ/ር ብርሃኑን ያነበብኩት ሁለቱ ታዋቂ ፖለቲከኞች፣ ዶ/ር መረራ ጉዲና “የኢትዮጵያ ፖለቲካ ምስቅልቅል ጉዞና የሕይወቴ ትዝታዎች -ከኢትዮጵያ ተማሪዎች ንቅናቄ እስከ ኢህአዴግ” እንዲሁም ኢ/ር ሃይሉ ሻውል “ ሕይወቴ እና የፖለቲካ እርምጃዬ” በሚሉ ርዕሶች ያሳተሙዋቸውን መጽሃፎች ካነበብኩ በሁዋላ በመሆኑ፣ በሶስቱም ስራዎች ላይ መጠነኛ ንጽጽር ለማድረግ አስችሎኛል።

ዶ/ር መረራ ከተማሪዎች እንቅስቃሴ እስከ ዛሬ ያለውን የአገራችንን ፖለቲካ ግሩም በሆነ መንገድ አቅርበዋል፤ መጽሃፉ ብዙ አስቂኝ ገጠመኞች የተካተቱበት በመሆኑ ፣ በቋንቋና በዓርትዖት በኩል የሚታይበትን ጉልህ ችግር አይተን እንዳላየን እንድናልፈው ያስገድደናል። መጽሀፉ በጥሩ ዓርታዒ እንደገና ቢታረምና ቢታተም “ የተዋጣላቸው” ከሚባሉት የአገራችን መጽሀፎች ተርታ የመመደቡ እድል ከፍተኛ ነው። ዶ/ር መረራ የአገራችንን ህልውና እየተፈታተነ የመጣውን፣ በ1960ዎቹ ተዘርቶ በእነ አቶ መለስ ዜናዊ አገዛዝ ተኮትኮቶ ያደገውን የብሄር ፖለቲካ መነሻ ፣ ያመጣውን ግሳንግስ እና የግሳንግሱን ማራገፊያ መፍትሄ አስቀምጠዋል። መፍትሄ ብለው ያስቀመጡትም በመጽሀፉ የመጨረሻ ገጽ እንደሚከተለው ሰፍሯል፣ “ …ለታሪክም ለህዝብም አስቀምጬ (ማለፍ) የምፈልገው መሰረታዊ ነጥብ ፣ አብዛኛው የትግራይ ሊሂቃን “ ስልጣን ወይም ሞት” ብሎ ስልጣን ላይ የሙጥኝ እስካለ ድረስ ፣ አብዛኛው የአማራ ሊህቃን በአጼዎች ዘመን የነበረውን የበላይነትን መልሼ አገኛለሁ ብሎ የሚገፋውን የሕልም ፖለቲካ እስካልተወ ድረስ፣ ብዙሃኑ የኦሮሞ ሊህቃን ኦሮሚያን ለብቻ የማውጣቱን ሕልም እስካልተወ ድረስ ሀገራችን ከአደጋ ቀጠና የምትወጣ አይመስለኝም። በሌላ ቋንቋ ለነዚህ መሰረታዊ በሽታዎቻችን መድሃኒት እስካላገኘን ድረስ ኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላምም ሆነ ዲሞክራሲያዊ አስተዳደርን ፈጽሞ የምታገኝ አይመስለኝም።” ( ገጽ 264)። ምንም እንኳ “አብዛኛው” የሚለው ቃል አወዛጋቢ ሊሆን እንደሚችል ቢሰማኝም ፣ ዶ/ሩ ያቀረቡት የመፍትሄ ሃሳብ በትኩረት ሊታይ እንደሚገባው ሳላስታውስ አላልፍም፤ በተለይ” እነዚህ የሶስቱ ብሄሮች ሊህቃን ህልማቸውን እንዲተው ማድረግ የሚቻለው እንዴት ነው?” የሚለው ጥያቄ ለእኔ ቁልፍ ይመስለኛል። ዶ/ር መረራ በዚህ ዙሪያ የተብራራ መልስ ቢሰጡ ኖሮ መጽሃፋቸውን የበለጠ ሙሉ ማደረግ ይችሉ ነበር እላለሁ።

የኢንጂነር ሃይሉ መጽሀፍ የአገራችንን የፖለቲካ ችግር ከግለሰቦች ባህሪ ጋይ ያያዘው በመሆኑ ብዙም ክብደት የሚሰጠው ሆኖ አላገኘሁትም፤ ንድፈሃሳባዊ ትንተናዎች ይጎድሉታል፣ የተዓማኒነት ችግሮችም አሉበት( በተለይ ከቅንጅት መሪዎች ጋር ስለነበረው የሽምግልና ሂደትና ከዚያ በሁዋላ ስለተፈጠሩት ኩነቶች) ፤ ለተተኪው ትውልድ የሚሰጠው ትምህርት ስለመኖሩም በእጅጉ እጠራጠራለሁ፤ በእርግጥ ኢ/ር ሃይሉ ብዙ ውጣውረዶችን አልፈው እስካሁን በህይወት ለመቆየት መቻላቸው እድለኛ ሰው እንደሆኑ በመጽሃፋ ለማየት ችለናል፣ አገራቸውን የሚወዱ ሰው መሆናቸውንም አስገንዝቦናል። ኢ/ር ሃይሉ የዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳን መንገድ በመከተል መጽሀፉን በሌላ ሰው በማስጻፋቸው ስለጸሃፊነት ችሎታቸው አስተያየት ለመስጠት አያስችልም ።

የዶ/ር ብርሀኑ “ዲሞክራሲና ሁለንተናዊ ልማት በኢትዮጵያ” የሚለው ርዕስ ዘጊ ወይም ለማንበብ የማይጋብዝ ነው፤ በትምህርቱ አለም የዘለቁና የጥናትና ምርምር ወረቀቶችን ለማንበብ ፍላጎት ያላቸው ምሁራን ካልሆኑ በስተቀር፣ እንደ እኔ አይነቱ ተራ አንባቢ በርዕሱ ማልሎ መጽሀፉን ለማንበብ ስለመነሳሳቱ እጠራጠራለሁ። መጽሀፉ ውጫዊ ገጽታው ባያማልልም ውስጣዊ ይዘቱ ግን ድንቅ ነው። እንደምንም የጀመርኩትን መጽሀፍ እየተጨነቁና እየፈራሁ፣ እያዘንኩና ከራሴ ጋር እየተሟገትኩ፣ እግረ-መንገዴንም የጸፊውን እይታ፣ የትንታኔ እና የቋንቋ አጠቃቀም ችሎታ እያደነቁኩ ጨርሸዋለሁ። መጽሀፉን እንደጨረስኩ የተናደድኩበት ነገር ቢኖር ጻሃፊው የኢትዮጵያን ችግሮች እንዲያ አድርገው ካቀረቡ በሁዋላ መፍትሄውን በይደር በመተዋቸው ነው።

ከዚህ ቀደም የአገራችንን ሁለተናዊ ችግሮች ማለትም የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚ፣ የተፈጥሮና የህዝብ ብዛትን በአንድነት አጣምሮ፣ በአገራችን ህልውና ላይ የደቀኑትን ፈተናዎች ቅልብጭ አድርጎ ያሳየ ከገብረህይወት ባይከዳኝ “መንግስትና የህዝብ አስተዳደር” በሁዋላ የተጻፈ መጽሀፍ ስለመኖሩ እጠራጠራለሁ፤ ይህን ስል ሌሎች ድንቅ የፖለቲካ መጽሃፎች አልተጻፉም እያልኩ አይደለም፤ የዶ/ር ብርሃኑን መጽሀፍ ለየት የሚያደርገው የተለያዩ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ችግሮችን ለይተው በማውጣት እርስበርስ ያላቸውን ትስስር ከግሩም ትንተና ጋር ሁሉም ሊረዳውና ሊጠቀምበት በሚችለው መንገድ ማቅረባቸው ነው ። (የምጣኔ ሀብት ትምህርት ( economics) የማይገባው ሰው እንኳ ቢሆን፣ መጽሀፉን አንብቦ ስለአገራችን ኢኮኖሚ ለመረዳት አይሳነውም።) መጽሃፉ የባራክ ኦባማን The Audacity of Hope እንዳስታወሰኝ ብገልጽ ያጋነንኩ አይመስለኝም፣ አጋነኸዋል የምትሉኝ ካላችሁም ” አንብቡትና ሞግቱኝ።

የዚህ መጽሀፍ ትልቁ መልእክት፣ ለእኔ እንደገባኝ፣ “የአገራችን ችግር ዲሞክራሲያዊ ስርዓትን በመገንባት ይፈታል” የሚለው አስተሳሰብ እንደሚታሰበው ቀላል አለመሆኑንና ከአሁኑ መፍትሄ ካልተበጀለት በሁዋላ ላይ ይዞት የሚመጣው ችግር ቀላል አለመሆኑን ማሳየት ነው ። የብሄር ፖለቲካው በዲሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ ላይ የሚኖረው ተጽእኖ፣ በአገራችን ልማትን ለማምጣት የሚገጥሙ ፖለቲካዊና መዋቅራዊ ችግሮች፣ ከአካባቢ ውድመትና ከህዝብ ብዛት ጋር ተያይዞ በመጽሀፉ በዝርዝር ቀርቧል። በአሁኑ ጊዜ በአገራችን እየታየ ያለውን የገቢ አለመመጣጠንም 1500 ብር የሚያወጣውን የአንድ መለኪያ ውስኪ ግብዣ በምሳሌነት በማንሳት በደቡብ አፍሪካ እንደታየው በአገራችንም ለወደፊቱ ይዞ ሊመጣ የሚችለውን ጣጣ ጸሀፊው በደንብ አሳይተውናል።

መጽሀፉ የውጩ ፖለቲካ በአገራችን ፖለቲካ ላይ የሚያሳርፈውን ተጽዕኖ እንዲሁም የአለማቀፉ የንግድ ስርዓት በኢትዮጵያ እድገት ላይ ያለውን ተጽእኖ ቢያካትት ኖሮ የበለጠ ድንቅ ይሆን እንደነበር አስባለሁ ። ከዚያ በተረፈ ግን መፍትሄዎቹ በሌላ ክፍል እንደሚቀርቡ መገለጹ በመጽሀፉ ላይ በቂ ክርክር እንዳይነሳ ያደረገው ይመስለኛል። በመጽሀፉ በቀረቡት ችግሮች እና ትንተናዎች ላይ ተቃውሞ የሚኖረው ሰው ይኖራል ብየ አላስብም፣ ተቃውሞ የሚነሳው ችግሮችን ለመፍታት በሚቀርቡት የመፍትሄ ሀሳቦች ላይ እንደሚሆን በመገመት ቀጣዩ መጽሃፍ አወያይ ( አካራካሪ) ይሆናል እላለሁ።

ስለአገራቸው እንቅልፍ አጥተው የሚያድሩ ሁሉ መጽሀፉን እንዲያነቡት እመክራለሁ ( የዶ/ር መረራንም ጨምሮ)። በተለይ በሰላማዊው የትግል ሜዳ ለመፋለም የሚያስቡ ጀማሪም ሆኑ ነባር ፖለቲከኞች የብርሀኑን መጽሀፍ በማንበብና በምርጫ ክርክር ወቅት ይዞ በመቅረብ ( የመፍትሄው መጽሀፍ ቶሎ እንደሚደረስ በመገመት) ምርጫውን ሊያሸንፉ እንደሚችሉ አልጠራጠርም፤ ስልጣኑን ይረከባሉ ብዬ ባላስብም።

No comments:

Post a Comment