Tuesday, December 3, 2013

ወያኔን አትንኩ የሳውዲ መንግስትን ተቃወሙ፣ ከመረቁ አቅርቡልኝ ከሥጋው ጾመኛ ነኝ

December 3, 2013
አዜብ ጌታቸው

ማቆሚያ ያጣው የክህደት – እርከን

የሳውዲ መንግስት በወገኖቻችን ላይ የፈጸመው ግፍና ኢ.ሰባዊ ተግባራት በመላው አለም የሚገኘውን ኢትዮጵያዊ ሁሉ አስቆጥቷል! አስቆጭቷል!።

ይህ በወገኖቻችን ላይ የተፈጸመው ግፍና በደል ብሄራዊ ውርደት እንጂ ተራ-ወንጀል አይደለም፡: ብሄራዊ ውርደት ደግሞ የደም- እዳ ነው!። በደም ሥሮቹ ዋሻ ኢትዮጵያዊ ደም የሚሹለከለክበት ዜጋ ሁሉ ይህን የደም-እዳ ሊጋራ ተፈጥሮ ግድ ይለዋል። ግድ የማይለው ካለ፦ እሱ አንድም ከተፈጥሮ እዝ ውጭ ነው። አልያም ኢትዮጵያዊ አይደለም። ከተፈጥሮ እዝ ውጭ የሆነ ፍጡር ሊኖር እንደማይችል ከግንዛቤ በማስገባት፤ ለግዜው ኢትዮጵያዊ አይደለም የሚለውን ይዘን እንጓዝ።

በህውሃት አስኳልነት የሚንቀሳቀሰው የወያኔ መንግስት እንደ መንግስት ላለፉት 22 ዓመታት በተለያዩ ግዚያት የሃገርን ህልውና የሚቧጥጡ ፤ የሕዝብን ደህንነት አደጋ ላይ የሚጥሉ፤ እንደ ግለሰብም የግለሰብ መብትን የገሰሱ እጅግ በርካታ ጥፋቶችን በጥናት ሲያከናውን ቆይቷል። የወያኔ መንግስት በህዝብ ላይ ቂም የሚይዝ ጉደኛ መንግስት ነው። የወያኔ መንግስት የሚያስተዳድረውን አገርና ሕዝብ የሚጠላ! ከዚህ በፊት በሃገራት ታሪክ ያልታየ ወደፊትም ሊታይ የማይችል የአለማችን ብርቅዬ  መንግስት ነው።

ወያኔ ይህን አደረገ ሲባል ሁሌ እንደነቃለን /SURPRISE/። ከዚህ በላይ ምንም አይነት ክህደት ሊፈጽሙ አይችሉም ብለን ስንደመድም እነሱ ግን የክህደታቸውን ደረጃ ከፍ አድርገው ያስደንቁናል/SURPRISE/
ድንበር ቆርሰው ለጎርቤት አገር ሰጥተው አስደነቁን/ SURPRISE/። ከዚህ በላይ ምን ሊመጣ ነው? ከዚህ በላይስ ምን ሊያደርጉ ይችላሉ? ብለን የድንበር መሬት ቆርሶ ለባዕድ መስጠት ማለት ከክህደቶች ሁሉ የከፋ የክህደት ጣራ ነው ስንል ደመደምን። ወያኔ ደግሞ የለም ይህ የመጨረሻው ክህደት አይደለም ። የድንበር መሬቱ ሲገርማችሁ እትብታችሁ የተቀበረበትን የመሃል አገር መሬታችሁንም ለውጭ ኢንቨስተር እንሸጣለን። እናንተንም አፈናቅለን ከነልጆቻችችሁ ጎዳና  እንጥላለን አሉና ስንቱን ጎጆ አፍርሰው ስንቱን አባ-ወራ ለጎዳና አዳሪነት ዳርገው አስደነቁን /SURPRISE/።

ቀጠሉም፦ የክህደት እርከናቸውን ብቻ ሳይሆን አድማሱንም አሰፉት። ከዓለማዊ (በህዝብና በሃገር ላይ ከሚፈጽሙት) ክህደት ወደ መንፈሳዊ ክህደት ተሸጋገሩ። የሃገር ቅርስ እያላችሁ የምትመጻደቁበትን ገዳም አርሰን ሸንኮራ እንዘራለን አሉ፡፡ የሙስሊሙን ወገን እውነተኛ መንፈሳዊ መሪዎች አባረው አብዮታዊ ዲሞክራት መሪዎችን አስቀመጡ።

መንፈሳዊው ክህደት ግን እንደ ዓለማዊው ክህደት እዳው ገብስ አልሆነላቸውም። መናንያኑ በሱባኤና በጸሎት ለአንድዬ ፋክስ ላኩ፤ ሼኮቹም በሰላት አላህን ምን እስክንሆን ነው የምትጠብቀው? አሉ። አንድዬ/አላህ ከብርሃን ፍጥነት በቀደም መልስ ሰጠ፡፤ ከሸንኮራውም ሆነ ከስኳሩ ቀድሞ “የህውሃቱ አንድዬ”ይሟሟ ዘንድ ማዘዣ ጻፈ!።ያም ግን የክህደታቸው እርከን መጨረሻ አልሆነም።

አሁን በቅርቡ ደግሞ የሳውዲ አረቢያ መንግስት በወገኖቻችን ላይ ግፍና በደል በፈጸመበት ቅጽበት  “የሳውዲ መንግስት ስደተኞቹን ማባረር መብቱ ነው” በማለት የክህደት እርከናቸውን ከፍ አድርገው አስደነቁን።/SURPRISE/
ነገ ደግሞ ከዚህ የባሰ ምን አይነት ክህደት ፈጽመው እንደሚያስደንቁን ማሰብም መገመትም የሚከብድ ይመስለኛል። እውነት! እውነት! እላችኋለሁ! እነሱ ግን እኛ ለማሰብና ለመገመት እንኳ የሚያዳግተንን ቀጣዩን የክህደት እርከን በማንጠብቀው ፍጥነት በተግባር ፈጽመው ዳግም ያስደንቁናል።

ይህ ሂደት ደግሞ እነሱ እስካልጠፉ ካልጠፉ ወይም ኢትዮጵያ የምትባል ሃገር እስካልጠፋች ቀጣይ ነው። የኛ ጫንቃ መሸከሙ ይክበደው እንጂ የነሱ የክህደት እርከን ከፍ እያለ መሄዱ አይቀርም።ፕሮፌሰር መስፍን የክህደት ቁልቁለት ያሉትን ልብ ይሏል።ለእኔ ግን የክህደት ዳግት …እየሆነ ነው።

ወደ ሁለተኛው የጽሁፌ ክፍል ልግባ፡ በሣውዲ አረቢያ በሚገኙ ወገኖቻን ላይ የተፈጸመው ግፍና አረመኔያዊ ተግባር ያስቆጣው በተለያዩ አገራት የሚገኝ ኢትዮጵያዊ በሚገኝበት ሃገር የሳውዲ ኤንባሲ እየተገኘ ተቃውሞውን በምሬት ገልጿል። በኔ እይታ ይህ በመላው አለም የሚገኘው ኢትዮጵያዊ ያሰማው ተቃውሞ ከዚህ በፊት በየትኛውም አገር ዜጋ በዚህ መጠንና ርብርብ የተደረገ አይመስለኝም። የምዕራቡ አለም ታላላቅ ሚዲያዎች ለጉዳዩ በቂ ሽፋን ሰጥተውት ቢሆን ኖሮ የኢትዮጵያዊያኑ ተቃውሞ ምን ያህል የአለማችን መነጋገሪያ ሆኖ በሰነበተ ነበር። ያም ሆነ ይህ በቂ ሽፋን ተሰጠውም አልተሰጠው የኢትዮጵያኑ ድምጽ ከፍ ብሎ ተሰምቷል።ውጤትም አስገኝቷል።

የሳውዲን መንግስት በመቃወም ረገድ ኢትዮጵያዊው ሁሉ አንድ ሆኖ ቆሟል። ለምን ቢባል ብሄራዊ ውርደት ነውና ! ብሄራዊ ውርደት ደግሞ ከላይ ለመግለጽ እንደሞከርኩት የደም እዳ በመሆኑ ኢትዮጵያዊ  ሁሉ ስሜቱ ሊነካ ግድ ብሏል።
ይህ ብሄራዊ ውርደት ያስቆጨው አብዛኛው ኢትዮጵያዊ ቁጣውን በሳውዲ መንግስት ላይ ብቻ አልገደበም። የአረብና የምዕራባዊያን ሎሌነቱን በተደጋጋሚ ባረጋገጠው የወያኔ መንግስት ላይ ጭምር እንጂ።ለምን ካልን? ይህ ብሄራዊ ውርደት እንዲፈጸም ምክንያት የሆነው ሃገርና ሕዝብ ጠሉ የወያኔ መንግስት በመሆኑ የሚል ነው መልሱ።

በተለያዩ ጸሃፍትና ሚዲያዎች ሲገለጽ የነበረውን መደጋጋም ባይሆንብኝ በሳውዲ የሚገኙ የበርካታ ሃገራት ዜጎች በሳውዲ መንግስት የተሰጠው የ7 ወር ግዜ ሳይጠናቀቅ ዜጎቻቸውን ወደ ሃገራቸው በመመለስ ከዚህ መሰሉ ችግር ታድገዋቸዋል። የወያኔ ባለስልጣናት ግን በተቃራኒው የኢትዮጵያዊያኑን ህገ-ወጥነት በመመስከር የተፈጸመውን ግፍ የተጋነነ እያሉ ሰነበቱ። በመሆኑም የኢትዮጵያኑ ቁጣ ከሳውዲ ባላነሰ በወያኔ መንግስት ላይ በረታ።ይህ ብቻ አይደለም፤ ሰማያዊ ፓርቲ በአዲስ አበባ ሳውዲ ኤንባሲ የጠራውን የተቃውሞ ሰልፍ የአጋዚ ታጣቂዎች በዘግናኝ ቅጥቀጣ በመበተን የወያኔ መንግስት በሳውዲ የተፈጸመብን ግፍ ተባባሪ መሆኑን አረጋገጠ። ይህም ደግሞ ኢትዮጵያዊያኑ በወያኔ መንግስት ላይ የሚያሰሙትን ቁጣ አጠናከረው።

ይህ በእንዲህ እያለ ተቃዋሚውን ኢትዮጵያዊ የተቀላቀሉ የወያኔ ካድሬዎችና ቅልቦች የሳውዲን መንግስት እንጂ ወያኔን መቃወም ትክክል አይደለም። ወያኔን አትንኩ ሳውዲን ብቻ ተቃወሙ በማለት ከመረቁ አቅርቡልኝ ከሥጋው ጾመኛ ነኝ ሲሉ እንደሰነበቱም ተመልክተናል።

እንደኔ እንደኔ እነዚህ ወገኖች የሳውዲ መንግስትን ለምን እንደሚቃወሙም የገባቸው አይደሉም። የማድረግ እንጂ የማሰብ ሃላፊነት ስላልተሰጣቸው አንዳንዴ የሚያደርጉትና የሚናገሩት ነገር ሲቃረን እንኳ አያስተውሉም።

ይህ ብሄራዊ ውርደት አለም አቀፍ መልክ መያዙ ወይም በውጭ መንግስት መፈጸሙ እንጂ ልዩ ያደረገው፤ የወያኔ  መንግስት በሃገር ውስጥ ባለው ዜጋና በሃገሪቷ ላይ ተደጋጋሚ ሃገርና ህዝብ አዋራጅ ተግባር ፈጽሟል።
እነዚህ የወያኔ ቅልቦች፦ በደል፤ ግፍና ግድያ ድንበር ዘለል እስካልሆነ ድረስ በሃገር ውስጥ በተፈጸመ ግድያና ክህደት ላይ ተቃውሞ ሊቀርብበት አይገባም እያሉ እንደሆነ የተረዱ አልመሰለኝም።

እነዚህ የወያኔ ቅልቦች፦ የሚያገባን ከሪያድና ከጅዳ የተባረረው ኢትዮጵያዊ ጉዳይ እንጂ  ከጉራ ፋርዳ በግዴታ የተፈናቀለው ኢትዮጵያዊ ጉዳይ የኛ ጉዳይ አይደለም እያሉ እንደሆነ የገባቸው አይመስለኝም።
እነዚህ የወያኔ ቅልቦች፦ የሚያንገበግበን በሪያድ ጎረምሶች የተደፈሩት እህቶቻችን ጉዳይ እንጂ በወያኔ ታጣቂዎች የተደፈሩት የተቃዋሚ ድርጅት አባላት ጉዳይ አያገባንም። ይህም ሲያንሳቸው ነው እያሉ እንደሆነ ያወቁ አልመሰለኝም። ለነገሩ የተሰጣቸው ሃላፊነት የማድረግ እንጂ የማሰብ አይደለምና ሊረዱም፤ ሊገባቸውም ሆነ ሊያውቁም አይችሉም።

ለነኚህ ወገኖች ላመላክት የምሻው (ማንበብ ከተፈቀደላቸው) የሳውዲ መንግስት እነሱ አትንኩብን ከሚሉት ከወያኔ መንግስት ምን ያህል የተሻለ መሆኑን ነው።
  • በመጀመሪያ ደረጃ እኛ በሳውዲ መንግስት ላይ የተቆጣነው ወገኖቻችንን ከሳውዲ እንዲወጡ በማዘዙ አይደለም። የሳውዲ መንግስት ያንን ማድረጉ መብቱ ነው።  ቁጣና ተቃዉሟችን ትእዛዙን በአግባቡና ሰባዊ በሆነ መልክ ባለመፈጸሙ ነው፡፡ እንደሰማነው ደግሞ የሳውዲ መንግስት ስደተኞችን የሚያስወጣው ለዜጎቹ ስራ ዕድል ለመክፈት ነው፡፤ በአንጻሩ የወያኔ መንግስት ዜጎቹን ወልደው ከብደው ከኖሩበት ሃገር የሚያፈናቅለው ለውጭ ሃብታሞች የስራ ዕድል ለመስጠት ነው። ልብ ካላቸሁ ልዩነቱን ልብ በሉ ።የሳውዲ መንግስት ለዜጎቹ ሲል ስደተኛን አባረረ።ወያኔ ለውጭ ባለሃብት ሲል ዜጎቹን አፈናቀለ አሰደደ።

  • ሴቶቻችን ላይ የመድፈር ወንጀል የፈጸሙት የሳውዲ ጎረምሶች እንጂ የሳውዲ መንግስት ፖሊሶችና ታጣቂዎች አይደሉም። ሃገር ውስጥ ባሉ በተቃዋሚ ድርጅት አባላት ላይ የመድፈር ወንጀል የሚፈጽሙት ግን መንግስት  ደሞዝ የሚከፍላቸው የስርአቱ አካሎች ናቸው።  ! ተደብቃችሁም ቢሆን ይህንንም አስቡ።
በቅርቡ ተክሌ የተባሉ አንድ ጸሃፊ ከወደ ካናዳ “…ሰልፋችንን ልንቀማ …” በሚል ርዕስ ለንባብ ያቀረቡት ጽሁፍም ይህንኑ የወያኔ ቅልቦች “የወያኔ መንግስት አይነካብን” ግርግር በስፋት ተመልክቷል። አቶ ተክሌ ስጋት አላቸው። ሰልፋንም ይቀሙናል የሚል።በርግጥም አንዳንድ ቦታ ተስክቶላቸዋል ተብሏል።ስኬት በምን እንደሚለካ ግልጽ ባይሆንም…በበኩሌ የአቶ ተክሌን ስጋት እጋራለሁም አልጋራምም።

የአቶ ተክሌን ስጋት እጋራለሁ

የወያኔ መንግስት ዲያስፖራውን ለመበተን ከፍተኛ ባጀት መድቦ በተለይ ወጣቶችን በልዩ ልዩ ጥቅማጥቅም በመደለል ወደ ሃገር ቤት ጠርቶ ስልጠና ሰጥቶ ሊያሰማራ መሆኑን ከሰማሁበት ቅጽበት ጀምሮ ይህ መንግስት እድሜው ካላጠረ መጪው ግዜ አስፈሪ መሆኑ ታይቶኛል።የኢትዮጵያዊነትን እሴቶች በአግባቡ ለመረዳት እድሉና አጋጣሚው (exposure) ያልነበረው በውጭው አለም ያደገ ትውልድ የወያኔ መንግስት እነኚህን እሴቶች ለማጥፋት የሚሄድበትን መንገድና ተንኮል እንዲረዳ አይጠበቅበትም። መኖሩን ስለማያውቀው ነገር መጥፋት ሊያውቅ አይችልምና።ይህን ክፍል እንደ አውቆ አጥፊዎቹ ጎልማሳና አዛውንት የወያኔ ቅልቦች ልንኮንነውም ሆነ በጥፋተኝነት ልንጠይቀውም ይከብደናል።

የወያኔ መንግስት እንኳን በውጭው አለም ለሚገኝ ወጣት ትውልድ ቀርቶ በሃገር የሚገኘውንም ወጣት በግሎባ ላይዜሽን ጥራዝ ነጠቅ ፍልስፍና በውጭው አለም ባህል፤ ሙዚቃ፤ አልባሳት፤ ፊልሞችና በመሳሰሉት ግሳንግሶች እያጠመደው እንደሆነ እያየነው ነው።በመሆኑም በተለይ በወጣቶቻችን ላይ ከፍተኛ ትኩረት መስጠት ይገባናል እላለሁ። በወጣቶች ጀርባ የሚንቀሳቀሱ ተባዮችን በማጋለጥ ወጣቱን ማንነቱን የማያውቅ ዜጋ ከመሆን ልንታደገው ይገባል። ይህ ወያኔን ከመቃወም እንቅስቃሴ ባላነሰ በትኩረት ሊሰራበት የሚገባ ተግባር ነው።የአቶ ተክሌን ስጋት የምጋራውም በዚህ ምክንያት ነው።

የአቶ ተክሌን ስጋት አልጋራም

የአቶ ተክሌን ስጋት የማልጋራው ደግሞ በአንድና አንድ ምክንያት ብቻ ነው። የወያኔ መንግስት ምንም እንኳ ከፍተኛ በጀት መድቦ ከዚህ ቀደም በነበረበት የጥንካሬ መሰረት ላይ ተመልሶ ለመቀመጥ እየተንደፋደፈ መሆኑ እውነት ቢሆንም ከውስጡ በተከሰቱና ከውጭም ባሉ ችግሮች እንደ አንጋሬ ተወጥሮ የሚገኝበት ወቅት ነው። በሚከተላቸው የተሣቱና የሃገሪቷን አቅም ያላገናዛቡ ፖሊሲዎች ምክንያት የተከሰተው የኑሮ ውድነት ከአጋዚ ሰራዊት ሰደፍ በበለጠ ህዝቡን እየደቆሰው ነው። ሙስሊሙ፤ ክርስቲያኑ፤ ገበሬው፤ የዩኒቨርሲቲ ተማሪው፤ መምህራኑ፤ ሰራዊቱ ….ሁሉም ውስጥ ቁስል አለ።ሁሉም ፍትኑን መድሃኒት ይሻል። መደሃኒቱ ደግሞ ወያኔን ማስወገድ ነው። ወያኔ እንደ መንግስት ደግፈው ያቆሙትን ምሶሶዎች አጥቷል፡፤ ከዚህ አንጻር የወያኔ ደጋፊዎች እንኳን የኛን ሰልፍ ለመንጠቅ ቀርቶ ራሳቸውም ከወያኔ ጓዳ ጓዛቸውን ጠቅልለው እብስ የሚሉበት ግዜ ሩቅ የሚሆን አይመስለኝም።

በዚህ ወቅታዊ ሁኔታ ላይ ተመርኩዤ የአቶ ተክሌን ስጋት  ስቃኘው ከኛ ይልቅ ወይኔ ነው መስጋት ያለበት ባይ ነኝ።

ይህን ስል ግን እጃችንን አጣጥፈን እየተመለከትን ወያኔ እንደ ባሉን ከሰማይ ወርዶ እግራችን ስር ፈንድቶ ይጠፋል በሚል ግብዝነት አይደለም። እንዲያውም ከመቼውም ግዜ በበለጠና በተለየ መልክ መንቀሳቀስና መስራትን የሚጠይቅ የታሪክ አጋጣሚ ላይ እንደምንገኝ አጽንኦት ሰጥቼ መግለጽ እሻለሁ።ምክንያቴም፦ የወያኔ መንግስት ከፍተኛው ስጋት የዲያስፖራው እንቅስቃሴ መሆኑ ግልጽ ነው። በመሆኑም የሚጨብጠው የሚይዘው ያጣው የወያኔ መንግስት ከፍተኛ በጀት የመደበበት ዲያስፖራውን የማዳከም የመበተን ከተቻለም የመቆጣጠር ፕሮጀክት በርካታ ወገኖችን ሊያነሆልል ስለሚችል ይህን እድል እንዳያገኝ በተደራጀ መልክ ልንቀሳቀስ ይገባልና ነው።

ምን ማድረግ ይገባናል?

ከዚህ በፊት የነበረው የተቃውሞ እንቅስቃሴ በዘፈቀደ የሚከናወን፤ በአብዛኛው የወያኔ መንግስት ለሚፈጽመው ኢሰባዊና ኢ.ዲሞክራሲያዊ ተግባራት የተቃውሞ ምላሽ መስጠትን ብቻ ያለመ ነው። አለፍ ሲልም የወያኔ የግፍ በትር ያረፈባቸውን ተጎጂ ዜጎች በገንዘብና በሞራል መርዳት ነው። አልያም በተቃዋሚነት ቆመው የሚታገሉ የተደራጁ ወገኖችን መርዳት ነው።  ይህ ብቻ ደግሞ የወያኔን መንግስት አውርዶ የምንናፍቀውን ዲሞክራሲያዊ ስርአት ለመገንባት የሚደረገውን ትግል ከግብ አያደርስም።

ከዚህ በኋላ በውጭው አለም ያለው የወያኔን መንግስት ብሄራዊ ጥፋት ለማስቆም የሚታገል ኢትዮጵያዊ ሁሉ! ሕዝባዊና አካባቢያዊ ድርጅት መፍጠር ይገባዋል፡፤ይህ ህዝባዊ ድርጅት ፡ ኢትዮጵያን እንታደግ የሚል አንድና ግልጽ አላማን ያማከለ የየትኛውም የፖለቲካ ድርጅትን ፕሮግራምና አቋም በተለይ የማይቀበል ወይም በተለይ የማይነቅፍ የፖለቲካ ድርጅት አባል የሆነው ያልሆነው በጸረ ወያኔ አቋሙ ብቻ ተመዝኖ የሚቀላቀልበት ሆኖ ተጠሪነቱም በዛው በተቋቋመበት ሃገር ላለው ኢትዮጵያዊ ብቻ የሆነ አደረጃጀት መከተል ይገባል።

እስካሁን ትግላችንን የጎዳው እርስ በርስ መጠራጠርና አልያም ግዴለሽነት በመሆኑ ይህ አዲስ አደረጃጀት ከምንም ነገር በፊት ቅድሚያ ሊሰጠው የሚገባው ፍጹም በሆነ መቀራረብና መተማመን ላይ የተመሰረተ አባላት ሊያከብሩት የሚገባ የዲሲፒሊንና የአሰራር ደንብ  አውጥቶ ተግባራዊ ማድረግ ነው።
ይህ ህዝባዊ ድርጅት አደረጃጀቱ እንደ እድርና ማህበር ሁሉ ሕዝባዊ መልክ ኖሮት እንቅስቃሴው ግን እንደ ፖለቲካ ድርጅት ልዩ ልዩ ንኡሳን ኮሚቴዎች የያዘ ሊሆን ይችላል።

ለምሳሌም የመረጃ  ክፍል፤ የዲሲፒሊንና ሥነ ስርአት ክፍል፤ የመድረክ ዝግጅት ክፍል፤ የፋይናንስ ክፍል፤ የአባላት ምልመላ ክፍልና ሌሎችም እንደአካባቢው ሁኔታ ሊኖሩ የሚገባቸው ክፍሎችን ማካተት ይችላል።

የመረጃ ክፍሉ፤  በአባላት መካከል የነቃ የመረጃ ልውውጥ የሚደረግበትን መንገድ እያመቻቸ በአካባቢው ያሉ የወያኔ ጀሌዎችን  ለይቶ በማወቅ የሚያደርጉትን እንቅስቃሴ ተከታትሎ የማጋለጥ ሚና ይጫወታል።

የዲሲፒሊን ክፍሉም በአባላት ቸልተኝነት የሚፈጠሩ ስህተትና ጥፋቶችን በአግባቡ በማረም የህዝባዊ ድርጅቱን ውስጠ ደንብ ተግባራዊነት ያረጋግጣል። መተማመን እንዲሰፍንና አባላት ለህገ ደንቡ ተገዢ እንዲሆኑ ያደርጋል።
የቅስቀሳና መድረክ ዝግጅት ክፍሉም የወቅቱ ሁኔታን አስመልክቶ ልዩ ልዩ መድረኮችን በማዘጋጀትና በማመቻቸት የአባላትን ሁለንተናዊ ግንዛቤ የሚያበለጽጉ ስራዎችን ይሰራል።ሌሎቹም ንዑሳን ክፍሎች እንደዛው የተሰጣቸውን ሃላፊነት ይመራሉ።
አደረጃጀቱ በተለይ በህቡ ቢሆን ጠቀሜታው የጎላ ይሆናል። ምክንያቱም በወያኔ ጀሌዎች የሚደረግን እንቅስቃሴ ለማክሸፍም ሆነ በየአካባቢው የሚኖሩ እንደ ቸርች ኢትዮጵያ ኮሚኒቲ የስፖርት ኮሚቴ የወጣቶች ኮሚቴ ፤ የሴቶች ኮሚቴ፤ የመሳሰሉትን ተቋማት ድምጽ ሳይሰማ ያለ ችግር መቆጣጠር ያስችለናል።

ይህ እንግዲህ ቀጣይ እንቅስቃሴያችንን በመንደፍ ረገድ እንደ መነሻ የቀረበ ሃሳብ ሲሆን፡፤ በጽሁፌ ላመላክተው የፈለኩት አብይ ጉዳይ ግን ከዚህ ቀደም ስናደርገው የነበረው የትርፍ ግዜ የዘፈቀደ “ሲያመች ብቻ” አይነት እንቅስቃሴ የትም እንደማያደርሰንና በአፋጣኝም ተቀራርበን ተማምነንና ተግተን የምንሰራበትን መንገድና ዘዴ መፈለግ እንዳለብን ነው። ይህን ማድረግ ካልቻልን የወያኔን ዘላለማዊ መንግስትነት የኛንም ዘላለማዊ ተቃዋሚነት ተቀብለን ሲገሉ እያለቀስን፤ ሲያስሩ እንዲፈቱ እየጠየቅን፤ ሲያፈናቅሉ ተፈናቃዩን እየረዳን፤ …. የራሳችንንም የሀገራችንንም መጨረሻ መጠበቅ ነው……
azebgeta@gmail.com

No comments:

Post a Comment