Wednesday, December 4, 2013

ዝምታችን በቃ!! የምናውቀው ብቻችን እጣ ፈንታችን ሰንጎነጫት ነው፡፡ በጣም እጅግ በጣም ከመሸ! ዝም ስንል እናልቃለን! ……

December 4/2013

‹‹መጀመሪያ በ‹‹አማራው›› ላይ መጡ ምንም አልተናገርኩም ምክንያቱም ‹‹አማራ›› አልነበርኩም፡፡ ቀጥለው ‹‹በኦሮሞ›› ላይ መጡ ምንም አላልኩም ምክንያቱም ‹‹ኦሮሞ›› አልነበርኩም፡፡ በመቀጠል ‹‹በሶማሊው፣ በጋምቤላው፣በትግሬው….ላይ መጡበት ምንም አልተናገርኩም ምክንያቱም ከአንዳቸውም አልነበርኩም ከዚህ በመቀጠል በሙስሊሙ ላይ መጡ አሁንም ምንም አላልኩም ምክንያቱም ሙስሊም አልነበርኩም በመቀጠል በክርስቲያኖቹ ላይ መጡ ምንም አልተናገርኩም ምክንያቱም ክርስቲያን አልነበርኩም በስተመጨረሻ በእኔ ላይ መጡብኝ አሁን ለእኔ የሚቆምልኝ ማንም አልቀረም፡፡ ብቻዬን ነኝ!››
ይህ በናዚዎች ስር የነበረው ህዝብ ታሪክ ነው፡፡ በአምባገነኖች ስር ያለና የነበረ ህዝብ ታሪክ ነው፡፡ የእኛው የኢትዮጵያውያን የወቅቱ ችግር ነው፡፡ኒይሞለር በአንደኛው የዓለም ጦርነት የተሳተፈና የናዚ ቀንደኛ ደጋፊ የነበር የፕሮቴስታንት ፓስተር ነበር፡፡ ጨፍጫፊው ናዚ ለጀርመናውያን እቆማለሁ ቢልም በሀሳብ የተለዩትን ጀርመናዊያን ላይ ግን ጠንካራ ብትሩን አሳርፎባቸዋል፡፡ እናም ኮሚኒስት፣ ሶሻሊስት፣ ቤተ እስራኤላዊያን፣ የሰራተኛ ማህበራት….ሌላም ሌላም ከናዚ አስተሳሰብ የሚቃረኑት በሙሉ በየተራ እርምጃ ተወሰደባቸው፡፡ በዛ ዘመን አንዱ ላይ እርምጃ ሲወሰድ ሌላው ዝም በማለቱ ናዚዎች የሚፈልጉትን ሁሉ በግፍ ጨፍጭፈዋል፣ አስረዋል፣ አሰቃይተዋል፡፡
በዚህ ወቅት የፕሮቴስታንቱ ፓስተር ማርቲን ኒይሞለር የሂትለርና የናዚ ደጋፊ ነበር፡፡ ምክንያቱም ኮሚኒስት፣ ሶሻሊስት፣ ቤተ እስራኤላዊያን፣ የሰራተኛ ማህበራት… የሚባሉት መካከል ብዙዎቹ ከፕሮቴስታንት ጋር የሚቃረኑ በመሆናቸው እንደ ጠላት አይቷቸዋል፡፡ ፓስተሩ ሂትለር ኮሚኒስቶቹን ሲያዝር፣ ሲገድል፣ ሲያግዝ ‹‹እግዚያብሄር አይወደውም፣ እነሱም ጀርመናውያን ናቸው፣ ይቅር ተባባሉ፣ ተቀራረቡ›› ከማለት ይልቅ እግዚያብሄር የማይወደውን እግፍ በአይኑ እያየ ዝምታን መረጠ፡፡
ናዚ ያልዳሰሰው የህብረተሰብ ክፍል፣ ካድሬ ለማድረግ ያልጣረው ጀርመናዊ፣ ከጎኑ ለማሰለፍ ያልሞከረው መሪ አልነበረምና በስተመጨረሻ ወደ እምነት ተቋማት ማምራቱ የግድ ነበር፡፡ እናም ፕሮቴትታንትም ቤተ ክርስቲያንም ከመጽሃፍ ቅዱስ ይልቅ የናዚን ‹‹ዶክትሪን›› እንድትቀበል ተገደደች፡፡ ልክ እንደኛው ‹‹አብዮታዊ ዴሞክራሲ›› ማለት ነው፡፡ ናዚን አድንቆ የገባውን ካድሬ ‹‹የእምነት አባት›› እነ ሂትለር እጃቸውን ዘርግተው ተቀበሉት፡፡ በእምነታችን ጣልቃ ሊገባብን አይገባም ያሉት ግን አይቀጡ ቅጣት ተቀጥተዋል፡፡
ማርቲን ኒይሞለር የናዚን ‹‹ዶክትሪን‹‹ አልቀበልም ካሉት ‹‹አባቶች‹‹ መካከል አንዱ ነበር፡፡ ናዚ ሲያሰቃያቸው ዝም ብሎ ያያቸው ቤተ እስራኤላዊያን፣ ኮሚኒስቶች፣ ሶሻሊስቶች፣ የንግዱ ማህበራት…..የደረሰባቸው እጣ ፈንታ አሁን እሱ ጋ ደርሳለች፡፡ ከሌሎቹ ጋር ባለመተባበሩ ብቻውን ቀረ፡፡ ናዚዎች አስረው ሲያሰቃዩት ኖረው የተፈታው ጥምር ጦሩ ከአሸነፈ በኋላ ነው፡፡ ሆኖም ይህ ፓስተር ከስቃዩ በኋላ በእጅጉ ተጸጽቷል፡፡ እ.ኤ.አ እስከ 1984 ድረስ ስለ ሰላም ሰብኳል፡፡ ይህ ሰው ከሚታወቅባቸው መካከል ዝምታ አንድ በአንድ እንደሚያስጨርስ በእስር ዘመኑ የተናገረውና መግቢያየ ላይ ወደ እኛው ሁኔታ አጠጋግቼ የጠቀስኩት ወርቃማ አባባል ነው፡፡ እሱ ቃል በቃል ያለው እንዲህ ነበር፡፡
‹‹First they came for the communists, and I didn't speak out because I wasn't a communist. Then they came for the socialists, and I didn't speak out because I wasn't a socialist. Then they came for the trade unionists, and I didn't speak out because I wasn't a trade unionist. Then they came for me and there was no one left to speak for me.››
ይህ አባባል ከሌላ ብሄር፣ እምነት ወይንም ሌላ ማንነት ውስጥ ነኝ ብሎ በሌሎች ላይ የሚደረጉትን ጥቃቶች በቸልታ ለሚያልፍ አሊያም ከላይ የተጠቀሱት ‹‹ማንነቶች›› ውስጥም ሆኖ ግድ ለማይሰጠው ሰው ሁሉ የሚያገለግል ነው፡፡ በሌሎች ላይ የሚደረግን በዝምታ ሲያልፍ ኖሮ በስተመጨረሻ አብሮት የሚቆም አጥቶ በብቸኝነት ለሚጨቆን ሁሉ የተነገረ ነው፡፡
በእኛ አገር በአንዱ ቋንቋ ተናጋሪ ላይ ችግር ሲደርስ ሌላኛው ዝምታን ይመርጣል፡፡በእምነትም ቢሆን ተመሳሳይ ነው፡፡ ሙስሊሙ ሲነካ፣ ኦርቶዶክሱ ስለ መርህ፣ ስለመብት አብሮ አይጮህም፡፡ ሙስሊሙ፣ ፕሮቴስታንቱምና ካቶሊኩም የሚያደርገው ተመሳሳይ ነው፡፡ በተቃዋሚዎቻችን ሰፈር ደግሞ ይብሳል፡፡
በአገራችን ከሚነገሩት አሉታዊ አባባሎች መካከል ዝምታን የሚያበረታቱት በግንባር ቀደምነት ተጠቃሽ ናቸው፡፡ ሌሎች በሚደርስባቸው ችግር ይቅርና በራሳችን ጉዳይ ዝምታን በመምረጥ ኢትዮጵያውያን ባህላችን አድርገነዋል፡፡ ዝምታ ወርቅ ነው፣ ዝም አይነቅዝም፣ ዝም ባለ አፍ ዝንብ አይገባበትም፣ ዝምን ማን ወሰደው፣ ብንናገር እናልቃለን…. እና በርካቶች ዝምታን የሚያበረታቱ ናቸው፡፡ ከመናገር ይልቅ ዝምታን የሚመርጠው ይህ ባህላችን ‹‹መቻል!›› የሚባል ቃልንም በምሳሌነት፣ በስምነትና በሌላም መልኩ በስፋት ይጠቀምበታል፡፡ ገዳይ ባህል!
የጀርመኑ ፓስተር የናዚ ቀንደኛ ደጋፊ ነበር፡፡ መጨረሻ ግን የሂትለር ዱላ ያመራው ወደሱው ነው፡፡ እንዲያውም ስቃዩን በወጉ የሚያይለት፣ ለዚህ ስቃዩ የሚቆረቆርለት አላገኘም፡፡ ደጋፊ፣ ካድሬ…..ም ቢሆን ስለ አንድ ብሄር፣ እምነት፣ ቋንቋ፣ ሙያ፣ አሊያም ስለ ራሱ ከዚህም ወረድ ሲል ፈርቶ ዝም ቢል የመጨረሻው መዓት እሱ ላይ ማረፉ የማይቀር ነው፡፡ የአሁኑን ጨምሮ ከገዥው ጋር የተሰለፉ ፖለቲከኞች፣ ካድሬዎች፣ ደጋፊዎችና ሌሎች አካላትም በስተመጨረሻ በትሩ ያረፈው እራሳቸው ላይ ነው፡፡
በቃ! የዝምታችን አባዜ ይህ ነው ትርፉ፡፡ ልክ እንደዚያ ቄስ፣ ልክ እንደኛ ፖለቲከኞች፣ ልክ እንደአገራችን የእምነት ተቋማት፣ እንደ ማህበራት፣ ምሁራን፣ ልክ የተለያዩ ቋንቋ ተናጋሪዎች የተለመደ ተግባር ዝምታ፣ ‹‹ምን አገባኝ!››፣ የፖለቲካ እሳትነት ብቻችን ያስበላናል፡፡ አስበልቶናልም፡፡ ማንም ስቃያችን ሳያይልን፣ ማንም ሳይጮህልን፣ ማንም ሳይቆምልን ያስፈጀናል፡፡ ያስጨርሰናል፡፡ ዝምታ ከወርቅ ይልቅ እንደሚያበሰብስ፣ እንደሚነቅዝና እንደሚያነቅዝ የምናውቀው ብቻችን እጣ ፈንታችን ሰንጎነጫት ነው፡፡ በጣም እጅግ በጣም ከመሸ!
ሚኒልክ ሳልሳዊ

No comments:

Post a Comment