Monday, December 16, 2013

አንድ ወጣት የመንግስት ሰራተኛ መንግስትን በመቃወም ራሱን አጠፋ

December 16/2013

በሲዳማ ዞን በአለታ ጩኮ ወረዳ የግብርና ፅ/ቤ ባለሙያ የሆነው ወጣት ነጋልኝ ፀጋዬ በሙያው ለአመታት ህብረተሰቡን ሲያገለግል ቢቆይም የመንግስትን አሰራር በተደጋጋሚ በመተቸቱ፣ ከመስርያ ቤቱ ኃላፊዎች ጋር በተለያዩ ግዜያት ግጭት ውስጥ ከመግባቱም በላይ የማስጠንቀቂያ ደብዳቤ ሳይቀር ደርሶት ነበር።

ወጣት ነጋኝ ፀጋዬ መንግስትን በግልፅ በመቃወም፤ መስተካከል ያለበትን ጉዳይ በግልፅ መናገር ልዩ ባህሪው እንደነበር የሚናገሩት ጓደኞቹ፣ በዚህ ባህሪው በተደጋጋሚ ለእስር ተዳርጎም ነበር። "መቼ ነው ነፃ የምንወጣው?' በማለት በተደጋጋሚ ጥያቄዎችን ሲያቀርብ እንደነበር የሚናገሩት ባልደረገቦቹ፣ ታህሳስ 4 ቀን 2006 ዓም አዋሳ አውሮፕላን ማረፍያ ሜዳ ላይ 20 ገፅ ያለው መንግስትን የሚቃወም ደብዳቤ ፅፎ የትምህርት ዶክመንቶቹን እንደታቀፈ እራሱን አጥፍቶ ተገኝቷል። 

በሰዓቱ ደርሰው ደብዳቤውን ያነበቡ ሰዎች እንደተናሩት ደብዳቤው
‹‹ እስከዛሬ ነፃ እወጣ ይሆን ብዬ ጠብቄ ነበር ግን ነፃ የምወጣበት መንገዱ እየጠበበ ነፃነቴ እየራቀኝ መጣ፣ ታዲያ ነፃ እንዲያወጣኝ በማን ተስፋ ላድርግ? 'በማንም … 'ለካ ነፃ መውጣት ይቻላል፣ እኔ ግን በቀላሉ እራሴን ነፃ ማውጣት እንደምችል ተረድቻው ፣ ስለዚህ እራሴን ከመራር ግፍ አላቅቄ በነፃነት ነፃነቴን አውጃለሁ፤ ስለዚህም ሞቴ ነፃነቴ ነው፡፡ ሳልገድል ፣ በሞቴ እራሴን ነፃ አወጣለው ››.. የሚል ይዘት አለው።

በግል ማስታወሻው ላይ ደግሞ ‹‹ በዚህች ሀገር ላይ ሶስተኛ አራተኛ አምስተኛ ዜጋ ሆኜ መኖሬ የሚያበቃው መቼ ነው ›› ኢትዮጵያ ነፃ መውጣት ባትችል እኔ ግን እራሴን በሞቴ ነፃ አወጣለሁ የሚል መልዕት" ሰፍሯል።
ወጣት ነጋልኝ ፀጋዬ የፃፈው 20 ገፅ የተቃውሞ ደብዳቤ በአሁን ሰዓት በአዋሳ ፖሊስ እጅ የሚገኝ ሲሆን ለቤተሰብ እና ለጓደኞቹ ደብዳቤውን ለመስጠት ፖሊስ ፈቃደኛ አልሆነም፡፡ ወጣቱ በ30 ዓመቱ ይህችን አለም የተሰናበተ ሲሆን ስርዓተ ቀብሩ በጌደኦ ዞን ዲላ ከተማ ዲላ ኢየሱስ ቤ/ክ ታህሳስ 5 ቀን 2006 ዓ.ም ተፈፅሟል፡፡

ወጣት ነጋልኝ በጉራጌ ዞን ልዩ ስሙ ሜልኮ ተብሎ ከሚጠራው መንደር በ1976 ዓ.ም የተወለደ ሲሆን ትምህርቱን በዲላ ከተማ እና በሀዋሳ ከተማ የተማረ መሆኑንም ከቤተሰቦቹ ለማረጋገጥ ተችሏል፡፡ ወጣቱ በወላይታ ሶዶ ግብርና ኮሌጅ በ1998ዓ.ም በማዕረግ ተመራቂ ስለመሆኑም የኮሌጁ ቆይታው ያሳያል።
ወጣት ነጋልኝ በሲዳማ ዞን በሎካ አባያ ወረዳ ለሁለት ዓመታት ከ1998 እስከ 2000 ዓ.ም ሲሰራ ከቆዬ በኋላ ወደ አለታ ጩኮ ወረዳ የተዛወረ ሲሆን፣ ህይወቱ እስካለፈበት ዕለት ድረስ በስራ ላይ እንደነበረ ከስራው ጎን ለጎንም በ agricultural business management ከያርድስቲክ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ የመጀመርያ ዲግሪውን ይዟል፡፡
ለሰዎች መብት ዘወትር የሚታገል በሃፊዎቹ ዘንዳ ጥያቄ በመጠየቅ እና ያላመነበትን ነገር በመከራከር ሃላፊዎቹን መልስ በማሳጣት የሚታወቅ እንደነበር የስራ ባልደረቦቹ ገልጸዋል።
ወጣት ነጋልኝ ፡ አልንና ዝም አልን በሚል ርእስ በጻፈው አጭር ግጥም እንዲህ ይላል
አልንና ዝም አልን
ሲሉ ሰማንና እኛም መልሰን አልን
ያሉትን አልንና መልሰን ዝም አልን
በዝምታ ውስጥ መልስ እንደላ ስላወቅን

No comments:

Post a Comment