Sunday, December 22, 2013

100 ኢትዮጵያዊያን ኢሚግሬሽን እስር ቤት በር ላይ ወድቀዋል፡፡በግሩም ተ/ሀይማኖት

December 22/2013

 አንዲት ኢትዮጵዊን አንድ ሀበሻ አሳሰራት ብለው ነገሩኝ፡፡ ያ አሳሰረ የተበለውን ሰው ፈልጌ ለማናገር መፍትሄ ለማግኘት እንጂ እስር ቤት ሄጄ እሷን ማየት አላሰብኩም፡፡ ምክንያቴ ከእስር የምትወጣበትን መንገድ መፈለግ ነበር፡፡ በመሀል ልጅቱን ለመጠየቅ ወደ እስር ቤት ከሄዱት መካከል ነብዩ ተስፋዬ የሚባለው ልጅ ደወለልኝ፡፡ 
‹‹..እስር ቤት ጊቢ በር ላይ ተኝተዋል፡፡ እስኪ አንዱን አናግረው አለኝ…›› ሞባይል ስልኩን አቀበለው፡፡ ‹‹…ወንድሜ ልብሳችንን ነጥቀው አቃጠሉት፣ ከዚህ በር ላይ ሂዱ ብለው አባረሩን ርቦናል ጠምቶናል…ከነጋ አልበላንም እርቦናል….›› መስማት አልቻልኩም፡፡ ሰሞኑን ባደረብኝ በጤና ችግር ምክንያት አርብ እለት ሄጄ ላያቸው ባለመቻሌ ውስጤን ጸጸት ሸነቆጠው፡፡ ግን ወድጄ አልነበረም፡፡ መንገድ ላይ ቢያመኝ ብዬ በመፍራት ሄለን ገ/እግዚአብሄርን አስከትዬ በቀጥታ በኮንትራት ታክሲ ወደ ኢሚግሬሽን እስር ቤት አመራሁ፡፡ ስደርሰ ባየሁት ነገር ከሚገባው በላይ አዘንኩ፡፡ አነባሁም፡፡ በምን አይነት አለመታደል ነው የተሰነግነው? ምን አይነት እርግማ ነው ያለቀቀን..ምን አይነት ተስፋ ማጣት ነው አሁንም ሳዑዲ አረቢያ ለመሄድ ባህር እያሻገረን ያለው ሁኔታ?፡፡ ምን አይነት መጨካከን ነው እንደካባ የደረብነው፡፡ እነዚህን ልጆች እያየ አልፎ ገብቶ ሌላ ኢትዮጵያዊት ያሳሰረው አለማየሁ አንጀቱ እንዴት ቻለው ስል ራሴን ጠየኩ፡፡ ግን ምላሹ በእየአንዳንዳችን ማንነት ውስጥ የጠፋ እኛነት ሆኖ ነው የታየኝ፡፡

አንጀታቸው እጥፍ ያለ፣ በርሃብ የከሱና የጠቋቆሩ፣ የሚለብሱት የሌላቸው 102 ልጆች እስር ቤት ገብተው ወደ ሀገራቸው ለመመለስ ፈልገው እሰሩን ቢሉም ጭራሽ ፖሊስ ከቦታው እንዲሄዱ አባረራቸው፡፡ ነፍሳቸውን ለማዳን ሮጡ፡፡ ጥለውት የሮጡትን ልብስ እና በእንደ ብርድ ልብስ የሚጠቀሙበትን ከሰው ያገኙትን ልብስ ሰብስበው ፖሊሶቹ አቃጠሉባቸው፡፡ በዛ አጥንትን በሚሰብር ብርድ እንዲሁ ራቁታቸውን አድረው ጦም ውለው ነው እንግዲህ እኔ የደረስኩት፡፡ ምንስ ባደርግ የተሰመማኝ ሀዘን ከውስጤ ይወጣል፡፡ አማራጭ የለኝም፡፡ ዞሬ የሄድኩበት እና ቆሞ የሚጠብቀኝ ታክሲ ውስጥ ገባሁ፡፡ ሄለን እና ነጅብ በመለቀው ቪዲዬ ላይ ታዩዋቸዋላችሁ እነሱን ይዤ ለ100 ሰው ምግብ ላገኝ የምችልበትን አካባቢ እና ሆቴል ፍለጋ ዳከርኩ፡፡ ተመስገን አግኝቼ መቶ ፉል አዘዝን፡፡ ኩብዝ የሚባለውን ቂጣ ነገር 300 ያህል ገዛሁ፡፡ ይህን ሁሉ የማደርገው ከዚህ ቀድሞ በግሌ ለማደርገው እስረኞችን የማብላት፣ የማልበስ እና የሚያስፈልጓቸውን ነገሮች ማቅረብ እንቅስቃሴ እንዲረዳኝ ብለው ጥቂት ሰዎች ከላኩልኝ የተወሰነውን ከትላንት ወዲያ አርብ ለእስረኞቹ አዘጋጅቼ ልሄድበት ባስቀምጠውም በጤና ችግር ምክንያት አርብ እለት ወደነሱ መሄድ ባለመቻሌ የቀረ ነበር፡፡ ለነገሩ ከስዊድን የኢትዮጵያዊያ ሬድዬ ጋዜጠኞች በኩልም የደረሰኝ ስለነበር ዛሬ እሁድ ታህሳስ 13 ምሳ የማብላት ዝግጅት አዘጋጀሁበት፡፡

No comments:

Post a Comment