Monday, November 25, 2013

“ኦሮሞዎች ኢትዮጵያውያን አይደለንም”የሚለውን መፈክር ማሰማት- ምን ማለት ነው?

November 25/2013

እኛ ኦሮሞዎች ኢትዮጵያውያን አይደለንም”የሚሉ ኦሮሞዎች እንዳሉ አውቃለሁ። ይህን አቋም የሚያራምዱት ከአጠቃላይ የኦሮሞ ህዝብ ውስጥ ምን ያህል ፐርሰንቱን እንደሚወክሉ ግን መረጃው የለኝም። በፖለቲካ ፓርቲ ደረጃ አንድኛው የኦነግ ክንፍ ከኢትዮጵያ የተለየችን ኦሮሚያ የመፍጠር ዓለማ ሰንቆ ሲንቀሳቀስ፤ ሌለኛው ደግሞ “መፍትሔው ሁላችንም በእኩልነትና በፍትህ የምንኖርባትን ኢትዮጵያ እውን ማድረግ ነው” ብሎ ማወጁን ከሁለት ዓመት በፊት ሰምቻለሁ። ይህ ብቻ ሳይሆን በነ ፕሮፌሰር መረራ የሚመራው ኦብኮ( ልብ በሉ ኦብኮ በ 1997ቱ ምርጫ ወቅት ከቅንጂት ቀጥሎ በተናጠል በርካታ የፓርላማ መቀመጫዎችን ያሸነፈና በኦሮሞ ህዝብ ንድ ተቀባይነቱን ያስመሰከረ ፓርቲ ነው) ፣ በአቶ ቡልቻ ደመቅሳ የተመሰረተው ኦፌዲንና ሌሎችም የኦሮሞ ፓርቲዎች- ከነባሩ ኦነግ የተለየ አቋም እንደሚያራምዱ እና ዲሞክራሲ፣ ፍትህና እኩልነት በሰፈነባት ኢትዮጵያ ውስጥ የ ኦሮሞን ህዝብ መብትና ጥቅም ከማረጋገጥ ውጪ ሌላ የተሻለ አማራጭ እንደሌለ አውጀው እየተንቀሳቀሱ ነው። በ ያ ላይ ጥርስ የሌለው አንበሳ የሆነው የኢህአዴጉ- ኦህዴድም አለ። በኢትዮጵያ ጉዳይ ከ ኦነግ የተለየ አቋም የሚያራምዱት እኚህ ሁሉ ፓርቲዎች ይነስም ይብሳም የየራሳቸው ደጋፊዎች አሏቸው።

ከዚህ አንፃር ከታች በቪዲዮው የሚታዩት ሰልፈኞች እንደ ኦነግነታቸው፦”ሳዑዲ ዐረቢያ የኦሮሞ ህዝብን መግደል አቁሚ!”የሚል መፈክር ማሰማት መብታቸው ነው። “ኦሮሞዎችኢትዮጵያውያን አይደለንም!” የሚለው ግን የተሣሳተ እንዲሁም ከሞራልን ከህሊና አኳያ ተገቢ ያልሆነ ነው።

አዎ! ሰልፈኞቹ፦”እኛ ኢትዮጵያውያን አይደለንም” ማለት ይችላሉ። በነፕሮፌሰር መረራ ፣ በነ ኦቦ ቡልቻ ደመቅሳ እና በሌሎችም በርካታ ኦሮሞዎች ጉዳይ ግን ህዝበ ውሳኔ ማሳለፍ አይችሉም። በየትኛው ውክልናቸው ነው ስለ አጠቃላዩ የ ኦሮሞ ህዝብ ውሳኔ የሚያሳልፉት በኢትዮጵያዊነታቸው የማይደራደሩ ብቻ ሳይሆን ኢትዮጵያዊነታቸውን ጥያቄ ምልክት ውስጥ የማያስገቡ እልፍ ኦሮሞዎችን ባቀፈች አገር ላይ ፦”ኦሮሞዎች ኢትዮጵያውያን አይደለንም!” ብሎ ያለ ውክልና ማወጅ አይቻልም። “እኛ የኦነግ አባላት ኢትዮጵያዊ አይደለንም!”ማለት ግን መብት ነው። ይቻላል።

ሌላው ያሳነኝ ነገር የዚህ ሰልፍ ዓላማ በሳዑዲ በስደተኞች ላይ እየተፈፀመ ያለው ስቃይና ግድያ እንዲቆም ለመጠየቅ ነው። ይህ ከሆነ እንደ ኦነግ አስተሣሰብስ ቢሆን ፦“ሳዑዲ ዐረቢያ የኦሮሞ ህዝብን መግደል አቁሚ!” የሚለው አይበቃም ነበር ወይ? “ በዝህ አስከፊ ሁኔታና ሁሉም ስለሁሉም እየጮኸ ባለበት ወቅት “ኦሮሞዎች ኢትዮጵያውያን አይደለንም”የሚለውን መፈክር ማሰማት- ምን ማለት ነው? ‘ሳዑዲ ኢትዮጵያውያንን መምታት ትችየለሽ’ ማለት አይመስልም ወይ? አረ እየተስተዋለ!
Dereje Habtewold

No comments:

Post a Comment