Saturday, November 2, 2013

ለእንጀራየ ብዬ !!!

November 2,2013

በሬ ሆይ በሬ ሆይ፤
ሞኙ በሬ ሆይ፤
ሳሩና አየህና ገደሉን ሳታይ፤
እልም ካለው ገደል ወደክብን ወይ።
ዛሬ ዛሬ “ለእንጀራየ ብየ ወይንኩ ለመኖር” የሚሉ አካሎች ቁጥር እና የአስተሳሰባቸው ሁኔታ አሳሳቢ ደረጃ ላይ ደርሷል።በተለይም ህግን እናስከብራለን ብለው የቆሙ አካሎች “ለእንጀራየ ብዬ ምንም ይሁን ምን የታዘዝኩትን ሳላቅማማ እፈጽማለሁ” የማለታቸው ነገር ከአሳሳቢ በላይም ነው።እነዚህ አካላት ዛሬ መረቅ የበዛበትን ወጥ በእንጀራ ለመጉርስ ሲሉ ነገና ተነገ ወዲያ የሚሆነውን ማየት ተስኗቸዋል። ዛሬ በያዙት ጠመንጃ ንጹሃን ዜጎችን ገድለው የሚበሉት እንጀራ ነገ ከማይወጡበት ገደል ውስጥ ሊከታቸው እንደሚችል ቆም ብለው ማሳብ ይኖርባቸዋል።
የህግ አስፈፃሚ አካላት ከእንጀራቸው በላይ የሚኖሩለት ትልቅ ቁምነገር ቢኖር የህግ የበላይነትን ማስከበር ነው። እነዚህ አካላት ከማንኛውም ተራ ዜጋ ተለይተው ህግን ለማስከበር ቃለ ማሃላ ፈፅመዋል። ይህን ቃለ መሃላ ሲፈጽሙ ዳኛው እና ተመልካቹ ሂሊናቸው ከፍ ሲል አምላክ ካላቸው አምላካቸው እንዲሁም ህዝብ ነው። ከዚህ ቃለ መሃላ በኋላ ህግ አስከባሪዎች በዋናነት የሚኖሩለትም ሆነ የሚሞቱለት ቁም ነገር እንጀራ ሳይሆን የህግ የበላይነት ነው። የምንኖርለትም ሆነ የምንሞትለት ዋናው ቁም ነገር የህግ የበላይነት እንጂ እንጀራ አይደለም ብለው የሚቆሙ የህግ አስከባሪዎች ባሉበት አገር ህግ ተከብሮ ዜጎች በሠላም ተረጋግተው ለመኖር እድሉን ያገኛሉ። ይህ ግን በኢትዮጵያችን እየሆነ አይደለም።
በኢትዮጵያችን የህግ አስከባሪዎች የሚኖሩለትም ሆነ የሚሞቱለት ዋናው ቁም ነገር “እንጀራዬ!” የሚባል ነገር ከሆነ ሃያ ሁለት ዓመት ሆነው።ህወሃት አገሪቷን ከተቆጣጠረ ዘመን ጀምሮ ኢትዮጵያችንን ድርና ማግ ሆነው እንደ አገር ሊያቆሟት የሚችሉ ዋና ዋና ክሮችን ሲበጣጥስ መኖሩ ከማንም የተሰወረ አይደለም። እየተበጣጠሱ ካሉ ክሮች መካከልም እውነትና ፍትህ ይገኙበታል። የህግ አስከባሪ አካላት ከፍትህና ከእውነት ይልቅ ለሚበላና ለሚጠጣ ከንቱ ነገር የበለጠ ትኩረት የሚሰጡ ሆነው እንዲያስቡ የተደረጉ ይመስላል። በዚህ በህወሃት ዘመን ህግን አስከብራለሁ ብሎ የማለ አካል “ለእንጅራ” ብሎ መሃላውን ያፈርስና ፍትህን ያጎድላል። ”ለእንጀራ”ብሎ በሃሰት ይከሰል ዳኛውም ያለ በቂ ማስረጃ ለእንጀራ ብሎ በሃሰት የእድሜ ልክ እስራት ይፈርዳል። በዚህም ዜጎች ይጎዳሉ ቤተሰብም ይፈርሳል።
ለእንጀራ ብሎ የገዛ ወገኑን የሚገድል ትውልድ መፈጠሩ አገሪቷን በእጅጉ የሚጎዳ ቢሆንም ህወሃቶች እንዲህ ያሉ ትውልዶችን መፍጠር በመቻላቸው ተሳክቶልናል ይላሉ ።በአንዲት አገር ውስጥ ፍትህ እና እውነት ከሚበላ ምናምን ነገር አንሳ ከተገኘች ያቺ አገር እንደ ባቢሎን ግንቦች ወድቃ ከመበታተን የሚጠብቃት ምንም ዓይነት ዋስትና የላትም።ኢትዮጵያ እንዲያ ነች። ኢትዮጵያ ውስጥ ነገን ተስፋ አድርጎ እና ተረጋግቶ ለመኖር የሚቻልበት ሁኔታ የለም። እንዲህም በመሆኑ ከሊቅ እስከ ደቂቅ የሚሰደድባት አገር ሁና የዓለምን ትኩረት ለመሳብ በቅታለች። ኢትዮጵያችን ከቄስ እስከ ዩንቨርስቲ ፕሮፌሰር፤ ከተማሪ እስከ ገበሬ፤ ከበረንዳ አዳሪው አንቱ እስከ ተባለ ባለ ሙያ ሁሉም በአንድ ላይ የሚሰደዱባት አገር ሁናለች።
ይሄ ለኢትዮጵያዊያን ትልቅ ውርደት ነው።ዘረኞቹ ህወሃቶችና በዙሪያው የተሰባሰቡ ዴማጎጎች ግን ይሄን ውረደት ለመረዳት አልቻሉም።
ለእንጀራው ብሎ ኢ-ፍትሃዊ ደርጊትን የሚፈጽም የህግ አስከባሪ አቅመ ቢስ ወገኖቹን ለስደት ይዳርጋል። ይሄ ሁኔታም አገርን ያፈርሳል እንጂ አይገነባም። በፈረሰ አገር ላይ ደግሞ ለእጀራ ተብሎ የሚሠራ ሥራ አይኖርም። አሁን በኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ ህግ አስከባሪዎች “እኔ ምን ላድርግ ለእንጀራዬ ብዬ ነው ህገ ወጥ ድርጊት የምፈጽመው” ሲሉ አለማፈራቸው በእጅጉ ያስገርማል። ምን ዓይነት ዘመን ላይ ደረስን ብለንም እንድንጠይቅ እንገደዳለን። እነዚህ ህግ አስከባሪዎች “ለእንጀራየ ስል ፍትህን አጓደልኩ” ማለታቸው በሌላ መልኩ ሲታይ “ለእንጅራየ ስል አገሪቷ እንድትፈርስ እኔም የበኩሌን ሚና ተጫወትኩ” ማለታቸው መሆኑን መገንዘብ እንዳለባቸው ልናሳስባቸው እንወዳለን።
አንድ ህግ በማስከበር ወይንም ደግሞ የአገርን ደህንነት እጠብቃለው ብሎ የቆመ ዜጋ የገዛ ወገኑን በትእዛዝ የሚገድል ከሆነ ከያዘው ብረት በምን እንደሚለይ ራሱን መጠየቅ አለበት። በምንም ዓይነት መለኪያ “አለቃየ ስላዘዘኝ ሰውን ገድያለሁ” ማለት ከፍርድ ነፃ የሚያደርግ አይሆንም።በኢትዮጵያ ውስጥ አገራችሁንና ዜጎቻችሁን ከጥቃት ለመከላከል ቃል ኪዳን ገብታችሁ ስታበቁ የገዛ ወገኖቻችሁን በማስጨነቅ ላይ ያላችሁ የህግ አስከባሪ አካላት ቆም ብላችሁ እንድታስቡ እንመክራችኋለን። የፈጠራችሁ አምላክ ከተሸከማችሁት ብረት ለይቶ ሰው የሚያደርጋችሁን ፈራጅ ሂሊና የሰጣችሁ መሆኑንም ማስታወስ ይኖርባችኋል።
እናንተ ለእንጀራ ብላችሁ በገዛ ወገኖቻችሁ ላይ ኢ-ፍትሃዊ የሆነ ድርጊት ስትፈጽሙ ዜጎች በህግ ላይ እምነት እንዳይኖራችሁ እያደረጋችሁ መሆኑን ልትገነዘቡ ይገባል። በህግ ላይ እምነት ያጣ ዜጋ እጅግ የከፉ እርምጃዎችን ለመውሰድ የሚስችል አቅም ያለው መሆኑንም መረዳት አለባችሁ።
እስኪ “የህግ አስከባሪ” አባላትን እንዲህ ብለን እንጠይቃችሁ ፤
አንድ ወንድ ልጃችሁን ይማርልኝ ብላችሁ ተማሪ ቤት ሰዳችሁታል። ይሄ ብላቴና በትምህርቱ ጎብዞ ወላጆቹን የሚያስመሰግን ሁኗል። እናትም እሰይ ልጄ በርታልኝ እያለች ሃሴት ታደርጋለች። አባትም እንዲህ ነው እንጂ ልጅ እያለ በልጁ ጉብዝና የሚኮራ ሁኗል። ልጁም ከተማሪ ቤት እንደ ወጣ ፈጥኖ ቤቱ የሚደረስ የቤተሰቡ የዓይን ማረፊያ ነው። ከእለታት አንድ ቀን ይሄ ብላቴና በተለመደው ሠዓት አልደረሰም። ቢጠበቅ ቢጠበቅ ድምጹ የሚሰማ አልሆነም። የዓይኖ ማረፊያ የደስታዎ ምንጭ እና የኩራትዎ ምክንያት የሆነው ልጅዎ አሁንም አልመጣም። ነገሩ ያሳስብዎትና ፍለጋ ብለው ሲወጡ ከደጅ የቆመ አንድ ሰው የልጅዎን መገደል ያረድዎታል።የልጅዎ ገዳይ መንግስት የቀጠረው አነጣጥሮ ተኳሽ መሆኑንም ጨምሮ ይረዳሉ።
ልጅዎን ተኩሶ ጭንቅላቱን በርቅሶ የገደለው ህግ አስከባሪ ተብየም “እኔ ምን ላድርግ ለእንጀራየ ስል የታዘዝኩትን ፈፀምኩ” ማለቱንም ሰሙ።በዚህ ሁኔታ የሚኮሩበትን አንድያ ልጅዎን አጥተው ሃዘን ተቀምጠዋል። በዚህ ግዜ የመንግስቱ ጋዜጦች የእርስዎ ልጅ የተገደለው ባንክ ሊዘረፍ ሲል ነው ብለው ዜና ይዘው ብቅ አሉ። የዚያ የንጹህ ልጅዎ ታሪክ ላይም እውነት ያልሆነ ታሪክ ተጨምሮበት የብላቴናው ፍፃሜ ሆነ። እርስዎም በዚህ ተቆጥተው የልጅዎን ገዳይ ወደ ፍትህ ለማቅረብ ወደ ፍርድ ቤት ይሄዳሉ። እንዲህ በማድረግዎ መንግስት የአገሪቷን ሠላም ለማስጠበቅ የወሰደውን እርምጃ ተቃወሙ ተብለው እጆ ተይዞ ወህኒ ይወረወራሉ።
ኢትዮጵያ ውስጥ እንዲህ ያለ ግፉ ተፈፅሞ አይተናል።በዚህ ሁኔታ የዓይኖቻቸው ማረፊያ የሆኑ ልጆቻቸውን ያጡ ወላጆች ደጃቸውን ዘግተው የሚያዜሙት የሃዘን እንጉርጉሮ ሰማየ ሰማያቱን ሰንጥቆ እፈጣሪ ደጅ ደርሷል። ሌሎችም አገር አልባነት ተሰምቷቸው “ለመሆኑ ይህች አገር የማን ነች” እያሉ እየጠየቁ ነው። ህወሃቶች ለዚህ ሮሮና ጥያቄ በቂ መልስ የላቸውም። ወደፊትም አይኖራቸውም። እነርሱ አገራቸው ሆዳቸውና እየዘረፉ የሚያከማቹት የገንዘብ ብዛት እንጂ ኢትዮጵያ አይደለችም።
እንግዲህ ኢትዮጵያ ውስጥ ያላችሁ የፌዴራል ፖሊስ አባላትና የደህንነት ሠራተኞች ይሄ በደል የተፈፀመው በእናንተ ላይ ቢሆን “ለእንጀራየ ብዬ የታዘዝኩትን ፈፅሜያለሁ” ለሚል ህግ አስከባሪ እና እርሱን ለሚያዘው አካል መልሳችሁ ምን ይሆን ?
በመጨረሻም እንዲህ እንላለን። አንድ መንግስት መፍረስ የሚጀምረው ዜጎች እነዚህን ጥያቄዎች መጠየቅ ሲጀምሩ ነው።እነዚህ ጥያቄዎች ለአገር መፍረስ ምልክቶች ናቸው።ለዚህም ነው ኢትዮጵያ ከውዳቂ መንግስታት ተርታ ገብታ ልትቆጠር የበቃችሁ። ኢትዮጵያችንን ለመታደግ የህግ አስከባሪዎች ለህግ የበላይነት እንዲሰሩ እንመክራቸዋለን። ዋስትናችሁ የሚያዛችሁ የጨለማው ንጉስ ህውሃት ሳይሆን ዜጎች በህግ ፊት በእውነት በፍትህ እና በእኩልነት መዳኘት መቻላቸው ነው።ፍትህን ከህወሃት ለሚወረወርላችሁ ፍርፋሪ እንጀራ ብላችሁ ማጓደላችሁን የምትቀጥሉ ከሆነ ፍፃሜያችሁ ከመቸውም ግዜ የከፋ እንደሚሆን አትጠራጠሩ። ፍትህ ማለት እውነት ነች። እውነትም ፍትህ ነች። እነዚህን ሁለት ገፀ በረከቶችን ልሞተ ለእንጀራ ብላችሁ መርገጣችሁን ካላቆማችሁ የሰደታችሁ ዘመን የጠነክርባችኋል።
የጨለማው ንጉስ የህወሃት መሪዎች እንደሆኑ ሁሉን ትተው በዝሪፊያ ላይ ተጠምደዋል።የዘረፉትንም ይዘው የሚሰወሩበትን ሥፍራ እየፈለጉም ነው።እነዚህ ዘረኞች “ካለኛ ጀግና የለም” እያሉ የሚዘባበቱበትና ብዙሃኑን ተጭነው የሚኖሩበት ዘመን በቅርቡ እንደሚያበቃ ልናስታውሳቸው እንወዳለን። ያለምንም ጥርጥር ህውሃት ከህግ በታች የሚሆንበት ግዜ እየመጣ ነው። በዙሪውያውም የተሰባሰቡ ጉግማንጉጎች የጠዋት ፀሃይ እንዳየው ጤዛ መርገፋቸው አይቀርም። እኛም ለዚህ ግብ እየሰራን ነው።
የጨለማው ንጉስ ተወግዶ የነፃነት ጎህ በኢትዮጵያ ላይ ሲያበራ “ለእንጀራየ ስል ታዝዤ ንጹሃን ዜጎችን ገደልኩ” ማለት መልስ አይሆንም።የህግ አስከባሪዎች ሆይ ስሙ ! አልመሸም። አሁንም በቂ ግዜ አለ።ፍትህን፤ እኩልነትን እና ነፃነትን በኢትዮጵያ ለማንገስ በሚደረገው ትግል ውስጥ ተቀላቀሉ።ብትወድቁ የሚያነሳችሁ፤ መሸሸጊያ ብትሹ መደበቂያ የሚሆናችሁ ህዝብ እንጂ ዘረኞቹና ዘራፊዎቹ ህውሃቶች አይደሉም። እነሱማ እንደ ሸንኮራ መጥጠው ይተፏችኋል እንጂ መድህን አይሆኗችሁምና አሁኑኑ ከህዛባዊ ትግሉ ግን እንድትቆሙ ደግመን ጥሪያችንን እናቀርባለን።
ድል ለኢትዮጵያ ህዝብ

No comments:

Post a Comment