Saturday, November 16, 2013

የወያኔ መንግስት ያጓጓዛቸው ስደተኞች ብዛት 107 ነው 35,000 ስደተኞች በስቃይ ላይ ይገኛሉ

 November 16/2013

መንግስት እስካሁን ወደ ሃገር ቤት የመለሰው በ3 ቀን 107 ዜጎችን ብቻ ነው፤ 35,000 ሰው ለማመላለስ ስንት ቀን ይፈጃል?

 የኢትዮጵያ መንግስት የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ በሳዑዲ አረቢያ የሚገኙ ኢትዮጵ ያውያንን የማስመለሱ ጥረት ተሳክቶ ዜጎችን እያስመለስን ነው ካሉ በኋላ ከትናንት በስቲያ ጀምሮ ወደ ሀገራቸው መመለስ እንደጀመሩ ቢናገሩም በሳዑዲ ያሉት ኢትዮጵያውያን ቁጥር እና እየተደረገ ያለው የማስመለስ ጥረት ግን በጣም ደካማና የችግሩን ዕድሜ በጣም የሚያራዝም ነው ተብሏል። ማስመለሱ የተጀመረ ዕለት 23፣ ከትናንት በሥቲያ ቀትር ላይ 34 ትናንት ማምሻውን ደግሞ 50 ኢትዮጵያውያን ብቻ የተመለሱ ሲሆን በድምሩ እስካሁን የተመለሱት ዜጎች 107 ብቻ ነው።
(የመንግስት ሚዲያዎች ወደ ሃገራቸው ተመለሱ ሲሉ ያሳዩዋቸው ኢትዮጵያውያን በአዲስ አበባ ኤርፖርት)
እንደ አምባሳደር ዲና ገለጻ፤ በሳዑዲ አረቢያ የሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ ወደ አገራቸው የሚመለሱ ዜጎችን እየመዘገበ ነው ቢሉም ኢምባሲው ግን ስልኩ የማይነሳ ከመሆኑም በላይ ቦንድ የገዛ፣ የተመረጠ ብሄር አባል የሆኑትን እየመረጠ ቅድሚያ እንደሚሰጥ ኢትዮጵያውያኑ ከሳዑዲ አረቢያ ለዘ-ሐበሻ ተናግረዋል። የውጭ ሚዲያዎች ወደ ሃገራቸው ለመመለስ እጅ የሰጡ ዜጎችን ቁጥር 25 ሺህ የሚያደርሱት ሲሆን በሳዑዲ የሚገኙ ወገኖች ግን 35 ሺህ እንሆናለን ይላሉ። እነዚሁ ዜጎች ወደ ሃገራችሁ ትመለሳላችሁ በሚል የታጉሩበት ሥፍራ ላይ ካለመጸዳጃ፣ ካለ ውሃ፣ ባልተመቻቸ መኝታ እየተሰቃዩ ሲሆን የኢትዮጵያ መንግስት በቀን ይህን ያህል ሰው ብቻ ማመላለሱ ችግሩን እንደሚያባብሰው ገልጸዋል።
    
“መንግስት በ3 ቀናት ውስጥ 107 ሰዎችን ብቻ ነው የመለሰው፤ ለኛ የተገለጸልን በቀን 400 ሰው እንልካለን የሚል ነበር” የሚሉት እነዚሁ ኢትዮጵያውያን በቀን 400 ሰው የሚያመላልሱ ከሆነ በ87 ቀን ይፈጃል ብለን ነበር፤ አሁን ግን በመንግስት ሚድያዎች እንደሚገለጸው 20 እና 30 ሰው ብቻ በቀን ወደ ሃገሩ የሚመለስ ከሆነ በዚህ አስቸጋሪ ሁኔታ ይህ ሁሉ ሺህ ሕዝብ መቼ እንደሚመለስ ግራ ገብቶናል ሲሉ በስቃይ ላይ ያሉት ወገኖች ለዘ-ሐበሻ ብሶታቸውን ገልጸዋል።
“ወገኖቻችን ሊደርሱልን ይገባል፤ ኢትዮጵያውያን ለቀይ መስቀል እና ለአይ ኦ ኤም ችግራችንን ሊያስረዱልን ይገባል” የሚሉት እነዚሁ ኢትዮጵያውያን ችግራችንን ስንገልጽ በኢትዮጵያ ኢምባሲ “ማን ኑ አላችሁ?” እየተባልን እንዋረዳለን፤ አያከብሩንም ሲሉ ያማርራሉ።
በሳዑዲ ኢትዮጵያውያን እየደረሰባቸውን ያለው ስቃይ የተረዱ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ዛሬ እዛው አዲስ አበባ የሚገኘው የሳዑዲ አረቢያ ኢምባሲ ደጃፍ ሰላማዊ ሰልፍ ለማድረግ ተንቀሳቅሰው በመንግስት ወታደሮች መቀጥቀጣቸውና ብዙ ሰዎች መታሰራቸውም ዘ-ሐበሻ ዛሬ ጠዋት መዘገቧ ይታወሳል።
በሳዑዲ አረቢያ አሁንም ኢትዮጵያውያኑ በስቃይ ላይ እንዳሉ በስልክ የደረሱን መረጃዎች ይጠቁማሉ።
አሁንም ተጨማሪ መረጃ እንደደረሰን እናቀርባለን።

No comments:

Post a Comment