Wednesday, October 23, 2013

የመከላከያው ሹመትና መዘዙ

October 23/2013

 የሰሞኑና የቀደሙት የመከላከያ አድሎአዊ ሹመቶች ከማሳሰብ በላይ እየሆኑ ነው:: ይህ ተደጋጋሚ ተግባር የህገ መንግስቱን አንቀጽ 12:1 ፣62:4፣87:1ና5 እንደዚሁም አንቀጽ 88:2ን በጽኑ ይጥሳል:: በተለይም በአንቀጽ 87:1 ላይ የተቀመጠውንና በመከላከያ ሰራዊቱ ተዋጽኦ ላይ ፍትሃዊ ውክልና እንዲኖር የሚጠይቀውን ግብ ሙሉ በሙሉ ይሽራል:: አጠቃላይ የማንኛውም ህገ መንግስት መንፈስ የሆነውን ፍትሀዊና በአንድ ማህበረሰብ ሊኖር የሚገባውን የነጻነት፣ እኩልነትና ወንድማማችነትን የማስፈንና የማበረታታት ተግባርን ያኮላሻል:: በህሊና ተጠያቂነትም ላይ ይሳለቃል::
ትልቁና ስልታዊ (ስስተሚክ) ሙስና ይህ ነው:: 400,000 ብር የቤት ኪራይ ለግርማ ወ/ጊዮርጊስ ቤት ተከፋለ አልተከፈለ ኢትዮጵያ በርካታ ጉድ ችላለች:: ትችላለችም! በተደጋጋሚ የምንሰማው በመካላከያ ሹመት ግን ከህወሐት አይን አውጣነት ያለፈ ነው::የምርም ስድብ ነው:: ንቀት ነው:: እንዲህ ያሉ አብሮ መኖርን የሚጋፉና ኢፍትሀዊ አሰራሮች መቆም አለባቸው:: ማንኛውም ለትክክለኛ ሰላም፣ አብሮ መኖርና ፍትህ የሚያስጨንቀው ኢትዮጵያዊ ነኝ የሚል ይህ ይመለከተዋል:: ጥቂቶች ይጠቀሙ ዘንድ እንዲህ አይነት ግፍ ሲፈጸም እያዩ ዝም ማለት ተገቢ አይደለም:: አይሆንም::
የሀገሪቱ መከላከያ እንደግብ የተቀመጠለትን የብሔር ብሔረሰብ ተዋጽኦነት በአስቸኳይ ሊፈጽም የግድ ነው:: አለያ ይህ ሀገር ቅኝ ግዛት እየሆነ ነው:: በቅኝ ግዛት ያለ ህዝብ ነጻ መውጣቱ ግድ ይላል! የሕወሀት ሰዎች መሾም የለባቸውም የሚል የለም:: ህወሐት ከአንድ ብሔር የመጡ ሰዎች የመሰረቱት ድርጅት ነው::ድርጅቱ የኢህኣዴግ ባለውለታ ነው:: የሀገሪቱ ባለውለታነት ከነበረውም ጨርሶታል:: ቀሪ ሂሳቦዎ እየተባለ ያለበት ሁኔታ ነው ያለው:: ያም ሆኖ እንደ አንድ አባል መሳተፍ እንጂ ከሁሉ ብሄር እንደሆነ ሁሉ ሁሉንም የተቋሙን የስልጣን እርከኖች ሹመቶች መቆጣጣር አይበጅም::
ይህ የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ነው:: ኢትዮጵያም መከላከያ ሰራዊቱም የብዙ ብሔሮችና ብሔረሰቦች ሀገርና ተቋም ናቸው:: ስለሆነም ብዙ ጊዜ በምክንያትነት የሚቀርበው የልምድ: የዕውቀት ማነስ ወዘተ እንኳን ከ22 ዓመት በኋላ ቀድሞም ምክንያትነቱ አይታመንምና ማብቃት አለበት:: እስካሁንም ይህን ለማድረግ እውነተኛ ጥረት አልተደረገም ምናልባት በተቃራኒው እንጂ::
ይህ አድሎአዊ አሰራር አሁን ባለው ሁኔታ ከልክ አልፏል:: በአስቸኳይም ሊገታና ማስተካከያ መወጠን አለበት:: ይህ ካልሆነ አገሪቱን ይጠብቃል ተብሎ የተዋቀረ ተቛም በአወቃቀሩ ኢፍትሃዊነትና በህወሐት ማን-አለብኝነት ምክንያት አገሪቱን ለማፍረስ የተጋረጠ አደጋ ሆኖ ይቀጥላል:: ስለዚህ የህወሐትና የማዕከላዊው መንግስት ባለስልጣናት በተለይ በመከላከያው ተቋም የብሔር ተዋጽኦ ላይ ጠንካራ የሆነ ክለሳ ተደርጎ በሚቀጥሉት አምስት አመታት የሚቆይ ፕሮግራም ካልነደፉና በአስቸኳይ በስራ ላይ ካላዋሉ ሀገሪቱን ወደ ከፋ አደጋ በማዝቀጥ እንደሚያፈራርሷት ግልጽ ነው::
ፖለቲካ የማህበረሰቡ ስልጣንና ሀብት በትክክል እንዲከፋፈል ፍትሃዊ መፍትሔ ማምጣት ነው ግቡ:: በየጊዜው የምናየው የሀገራችን ፖለቲካ ግን በፍጥነት አድሎአዊነቱ እየጨመረና በርካታ የተወከሉ የመሰላቸውን ብሄሮችንና ግለሰቦችን በማግለል ስራው ተጠምዷል::ይህ ከሶማሊያም የባሰ አደጋ አለው ነው መልክቴ! መንገዳችሁ ለእኛም ለናንተም አይበጅምና ህሊና ያላችሁና የኢትዮጵያ መኖር የሚጠቅማችሁ የህወሐት አባላት እንድትሰሙ እመክራለሁ::

No comments:

Post a Comment