የእስክንድር መልዕክት!
Oktober 03.2013
የእስክንድር መልዕክት!
ትናንትና ሰብሰብ ብለን ወደ ቃሊቲ አምርተን ነበር፡፡ አንዱአለምንና ርዕዮትን መጠየቅ ባይፈቀድልንም እስክንድር መጠየቅ ችለናል፡፡
በእርግጥ እስክንድርን እንደ እስረኛ አይደለም የጠየቅነው፡፡ እስክንድር ምኑም እስረኛ አይመስልም፡፡ እርሱ ራሱ በእንግድነት የተቀበለን ነው የሚመስለው፡፡ እሱን ለመጠየቅ ሄደን ተጽናንተን የመጣነው እኛው ነን፡፡ ስለ አገራችን መጻኢ እድል፣ የትግሉ ምስቅልቅል፣ የህዝብ መከራ፣ የፖለቲካ ሀይሎች ድክመት …..ስለ በርካታ ነገሮች ስንማር ውለን ነው የተመለስነው፡፡
በስተመጨረሻ ስንሰነባበት ደግሞ የሚያወቁኝን ሁሉ ሰላም በሉልኝ ብሎናል፡፡ መቼም ፌስ ቡከኛ ሆኑ እስክንድርን የማያውቅ የለምና የእስክንድርን የከበረ ሰላምታ ተቀበሉት፡፡
ሌላም መልዕክት አስተላልፏል፡፡ ‹‹ፌስ ቡክ ላይ ያላችሁን እንቅስቃሴ ማጠናከር ይገባችኋል፡፡ ፌስ ቡክ እንዲሁ ማህበራዊ ድህረ ገጽ ሲባል ለለውጥ ምንም ፋይዳ የሌለው ሊመስል ይችላል፡፡ ሆኖም የአሁኑ ዘመን ትግል አንድ አጋር ሆኗልና በሚገባ ተጠቀሙበት፡፡›› የእስክንድር መልዕክት ነው፡፡
ግብጽን በምሳሌነት የሚያወሳው እስክንድር ‹‹የሙስሊም ወንድማማኞች ፌስ ቡክ መጠቀም ባይችልም ፌስ ቡከኞችን የግብጽ ወጣቶች ተጠቅሞ ሙባረክን አሸንፏል፡፡ ሙስሊም ወንድማማኞች ራሱ አምባገነን ለመሆን ሲቃጣውም ፌስ ቡክን ጠንቅቀው በሚያውቁት ግብጻዊያን ወጣቶች አይኑ እያየ በዚህ በተናቀው ድህረ ገጽ አውርደውታል፡፡›› ሲል የፌስ ቡክን ጠቀሜታ በአጽንኦት አስታውሶናል፡፡
የእስክንድርን ጥልቅ ትንተና መስማት የምትፈልጉ ሁሉ ወደ ቃሊቲ ጎራ ብትሉ ተጽናንታችሁ እና በርትታችሁ ትመለሳለችሁ፡፡ እናም እስክንድርን አግኙት፡፡ በተራችሁም መልዕክት አስተላልፉልን፡፡
No comments:
Post a Comment