Thursday, September 26, 2013

ሰላማዊ ሰልፍ የማድረግ መብትን ሊገድብ ይችላል የተባለ መመሪያወጣ

protest 2
September 26 /2013

ከቅርብ ወራት ወዲህ ተቃዋሚ ፓርቲዎች የአደባባይ የተቃውሞ ሰልፍ መጥራት መጀመራቸውን ተከትሎ በኢትዮጽያ ሕገመንግስት አንቀጽ 30 መሰረት የመሰብሰብ፣ ሰላማዊ ሰልፍ የማድረግ ነጻነትና አቤቱታ የማቅረብ መብትን ሊገድብ ይችላል የተባለ አዲስ መመሪያ የአዲስአበባ ከተማ አስተዳደር ማውጣቱ ተሰማ። አዲሱ መመሪያ ሰላማዊ ሰልፍ የማይደረግባቸው አካባቢዎችንና ጊዜያትን ለይቶ ያስቀምጣል።

 በዚሁ መሠረት በሃይማኖት ተቋማት፣ ሰፊ ህዝብ በሚገበያይባቸው የገበያ ቦታዎችና ህብረተሰቡ በብዛትና በስፋት በሚንቀሳቅስባቸው የስራ ቀናት እንዲሁም በስራ መግቢያና መውጫ ስዓታት ሰላማዊ ሰልፍ ማድረግ እንደማይፈቀድ ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው አካላት ገልፀዋል።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደርም ህገ መንግስቱ ላይ የሰፈሩትንና ሰላማዊ ሰልፍ በማድረግናበመሰብሰብ መብት ላይ ያተኮሩትን ሀሳቦች በዝርዘር ማየቱ አስፈላጊ በመሆኑ፤ ህገ መንግስቱን በአግባቡለመተግበር የሚያስችል መመሪያ ማዘጋጀቱን ገልጿል።
 በውስጡም ህጉን በዝርዝር ለማስፈፀም የሚያስችሉ መመሪያዎችን ያካተተ ነው ተብሏል።
ሰላማዊ ሰልፉን የጠራው አካል ያሉበትን ሃላፊነቶችና  የፀጥታ አካላትን ሚና ምን እንደሆነ በዝርዝር ያስቀመጠ መሆኑ ታውቋል።
የመመሪያው ተልዕኮ በህገ መንግስቱ አንቀፅ 30  ላይ የተቀመጠውን ድንጋጌ ማስፈፀምእንደመሆኑ ሁሉም ዜጋ በቅርቡ እንዲያውቅ ይደረጋል ብለዋል።
በዚሁ አንቀፅ ንዑስ ቁጥር 1 ላይ የሰፈረው ድንጋጌ ደግሞ ማንኛውም ሰው ከሌሎች ጋርበመሆን መሳሪያ ሳይዝ ሰላማዊ ሰልፍ ማድረግ እንዳለበት ያስቀምጣል።

ከቤት ውጪ የሚደረጉ ስብሰባዎችና ሰለማዊ ስልፎች በህዝብ እንቅስቃሴ ላይ ችግርእንዳይፈጥሩ ለማድረግና ሰላምን፣ ዲሞክራሲያዊ መብቶችንና የህዝብን የሞራል ሁኔታ እንዳይጥሱአግባብነት ያላቸው ስርአቶች ሊደነገጉ እንደሚችሉ በህገ መንግስቱ ላይ ተቀምጧል። 

የሰላማዊ ሰልፍና የፖለቲካ ስብሰባ አዋጅ ቁጥር 31/83 ኢህአዴግ ወደሥልጣን እንደመጣከወጡ አዋጆች አንዱና ቀዳሚው ነው:: ይህንኑ መብት የሚያረጋግጥ ተጨማሪ ድንጋጌ በ 1987 አ.ምበአዋጅ ቁጥር 1/87 በጸደቀው ህገ መንግስት አንቀጽ 30 ስር ተቀምጧል:: በዚህ ሕግ መሰረት ሰላማዊሰልፍ ለማድረግ የሚፈልግ አካል ከ 48 ሰአት በፊት በአቅራቢያው ለሚገኘው የመስተዳድር አካልማሳወቅ እንዳለበት መስተዳድሩ ደግሞ የሰልፈኛውን ደህንነት የሚጠብቅ የጸጥታ ሀይል የመመደብ ግዴታየተጣለባቸው ሲሆን ሰልፉን በታቀደበት ቀን ለማካሄድ የማያስችል በቂ ምክንያት በተገኘ ጊዜመስተዳድሩ ይህንኑ በመግለጽ ስብሰባው ለሌላ ጊዜ እንዲተላለፍ ኀሳብ ማቅረብ እንደሚችል በአዋጁተመልክቷል:: በሰላማዊ መንገድ ተሰብስቦ ተቃውሞን መግለጽ ህገ መንግስታዊና ሰብአዊ መብት በመሆኑይህንን መብት የሚንድ መመሪያ የአዲስአበባ አስተዳደርም ሆነ የፌዴራሉ ም/ቤት የማውጣት በህገመንግስቱ የተሰጣቸው መብት እንደሌለ አንዳንድ የሕግ ባለሙያዎች አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

አንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ ይህ መመሪያ መውጣቱን ከአዲስአበባ ፖሊስ መረጃ ካገኘ በኋላ የፖሊስ ከፍተኛ አመራሮችንና የአዲስአበባ አስተዳደር ኃላፊዎችን በጉዳዩ ላይ ለማነጋገር ሞክሮ እንዳልተሳካለት በይፋ መግለጹን በተለይ በግሉ መገናኛ ብዙሃን መዘገቡ ይታወሳል። የፓርቲው አመራሮች መመሪያ የወጣው የተቃዋሚዎችን በተደጋጋሚ ሰልፍ ለመውጣት የመጀመሩትን ጥረት ለማፈን ነው ማለታቸው ይታወሳል።

በጉዳዩ ላይ አስተያየት የጠየቅናቸው አንዳንድ የተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች መመሪያ ወጥቷል መባሉን ከመስማት ውጪ ኮፒው ስላልደረሳቸው አስተያየት ለመስጠት እንደሚቸገሩ ተናግረዋል። ሆኖም በአንዳንድ መገናኛ ብዙሃን ያነበቡትና የሰሙት ዓይነት መመሪያ ወጥቶ ከሆነ ሕገመንግስታዊ መብትን የሚገድብ መሆኑ የሚያጠራጥር አይደለም ብለዋል።
  


No comments:

Post a Comment