Saturday, September 14, 2013

እኔ ባልፍም እንኩዋን ሺህ ርዕዮቶች ስላሉ በርቱ አትደናገጡ “

September 14, 2013
by  Sekedar alemu
Reeyot-Alemu
* የርዕዮት ደህንነት አደጋ ላይ መሆኑን እንድታዉቁት ስል ነዉ ይህንን በብዙ ሀዘን ዉስጥ ሆኜ የጻፍኩላችሁ
ትላንትና እንደሁል ጊዜዉ ስንቅ ይዤላት ወደ ቃሊቲ ሔድኩ በር ላይ ያለዉ ፖሊስ “የርዕዮት እህት ነሽ አይደል እሱዋን መጠየቅ አትችይም በአስተዳደር በኩል ሔደሽ ጠይቂ” አለኝ፡፡ እንዳዘዘኝ በአስተዳደር በር በኩል ሔድኩ ወደ ዉስጥ በስንት ትግል ከስለሺ (የርዕዮት እጮኛ) ጋር ገባን፡፡

ከብዙ ጥበቃ በሁዋላ በብዙ ፖሊሶች ታጅባ መጣች ፊትዋ ተለዋዉጦ ስለነበር ምን እንደሆነች ስጠይቃት ከእናት፡ አባት እና ንስሃ አባት ዉጪ ማንም ሊጠይቃት እንደማይችል እና የእነሱን ስም እንድትሰጥ እንደተጠየቀች እና አሚናዘር የሚትባል የሴቶች ክፍል ሀላፊ አልጋዋ ድረስ በመምጣት እንደሰደበቻትና እንደዛተችባት እየነገረችኝ እያለ አሚናዘር የተባለችዉ ሃላፊ ወደኛ በመምጣት ርዕዮትን በማመናጨቅና በመስደብ ከኛ ልትወስዳት ስትሞክር ለምን እንደሆነ ስጠይቃት “ከዛሬ ወዲህ ዐይኑዋን አታዩትም ማንም እኔን ሊያዝ አይችልም የእናንተ ጋዜጣና ሚዲያ ምን እንደሚያመጣ እናያለን ” በማለት ርዕዮትን በማዋከብ እና በመጎተት እየሰደቡ ወሰዱዋት፡፡ ምድር ላይያሉ ሰቅጣጭ እና ለህሊና የሚከብዱ ስድቦችን አወረዱብን በዚህ መሀል ርዕዮት ድምጹዋን ከፍ አርጋ “የማልጨርሰዉን ነገር አልጀምርም እኔን ለማንበርከክ እና ለማሸማቀቅ ክሆነ መቼም አላረገዉም ትገይኝም ከሆነ ነይ ተኩሺ ” ስትል ጎትተዉ ወሰዱዋት፡፡ እኛንም ከጊቢዉ አዋክበዉ አስወጡን፡፡

ዛሬ በዐል ስለሆነ ምን አልባት ሊያስገቡን ይችላሉ ብለን ነበር ሁላችንም ወደ ቃሊቲ የሔድነዉ፡፡ የሆነዉ ግን በጣም አሳዛኝ ነበር፡፡ በር ላይ ደርሰን ስንጠይቅ (ቤተሰቦችዋና ጓደኞችዋ) አሚናዘር ላስፈቅድ ብላ በር ላይ ያለችዉ ፖሊስ ወደ ዉሰጥ ገባች ትንሽ ቆየት ብላ ተመለሰችና አባትና እናት ብቻ ነዉ የሚገቡት ያልችዉ አሚናዘር ብላ እኔና ስለሺ ጓደኞችዋንም ጨምሮ መግባት እንደማንችል ተነገረን የዚን ጊዜ አባታችን “የእነሱን ህገወጥ ስራ እንደማይተባበር እና እኛ ተከልክለን እሱ እንደማይገባ ነገራቸዉ” እናታችን እንድትገባና ሁኔታዋን አይታ እንድትነግረን የያዝነዉን ምግብ ይዛ ገባች፡፡ በጣም በሀዘን የያዘችዉን ምግብ ይዛ ተመለሰች ምነዉ ስንላት ርዕዮት የርሃብ አድማ እንዳደረገች እና ቤተሰብ የማይገባላት ከሆነ አድማዉን እንደምትቀጥል እንደነገረቻት እናም በጣም ያስደነገጠንን ዜና ነገረችን “አጠገቡዋ ኮ/ል ሐይማኖት (የ ገብሩዋድ ባለቤት) እንዳመጡዋትና የርዕዮትን አልጋ በማስጠጋት እሱዋነ ከጎንዋ አድረገዋት እሱዋም ሙሉ ለሊት እየሰደበቻትና እየዛተች እንዳሳደረቻት ህይወትዋ አደጋ ላይ መሆኑን አንድ ነገር ቢፈጠር በህመም እንዳልሆነ እንድታዉቁት እኔ ባልፍም እንኩዋን ሺህ ርዕዮቶች ስላሉ በርቱ አትደናገጡ” የሚል መልእክት ነገረችን፡፡

አስረዉ ሲያበቁ እንኳን ምነዉ ቢተዋት? በዚህ ከቀጠለ እህቴን ነገ ለማግኘቴ ምን ያህል እርግጠኛ እንደምሆን አላዉቅም!!!!!
ሉሉዬ የሚታልፊበት መከራሽን አምላክ ይይልሽ!!!!

* ይህ ጽሁፍ በተለያዩ የፌስ ቡክ አድራሻዎች የተስተናገደ አሳዛኝ ማስታወሻ ነው። ጽሁፉን በዋናነት ያተመ ትክክለኛ ምንጭ ካለ ለማረም ዝግጁ ነን። ጽሁፉን እንድናስተናግድ ለላክልን ደንበኛችን እናመሰግናለን። ርዕየትና ሌሎች ውድ ወገኖቻችንን እናስባቸው!!
 
Sources:-  Daniel Haregawi Timeline(FB)

No comments: