Thursday, September 5, 2013

የአንድነት ፓርቲ የጠራው አዲስ አበባው ሰላማዊ ሰልፍ ከ33ቱ ፓርቲዎች ጋር በጥምረት ይደረጋል


አንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ ‹‹የሚልዮኖች ድምጽ ለነጻነት››በሚል መሪ ቃል የጀመረው ህዝባዊ ንቅናቄ መስከረም 5/2006 በአዲስ አበባ በሚደረግ ሰላማዊ ሰልፍ ይጠናቀቃል፡፡ፓርቲው በተለያዮ የአገሪቱ ክፍሎች ያደረጋቸውን ህዝባዊ ስብሰባዎችና ሰላማዊ ሰልፎች በአንክሮ ሲከታተሉ የቆዮት 33 ፓርቲዎች በአዲስ አበባ የሚደረገውን ሰላማዊ ሰልፍ በጋራ ለማድረግ ስምምነታቸውን በመግለጽ በዛሬው ዕለት በአንድነት ዋና ጽ/ቤት ለጋዜጠኞች መግለጫ ሰጥተዋል፡፡


33 ፓርቲዎችን በመወከል ንግግር ያደረጉት አቶ ሔርጫፉ አዴሎ ‹‹አንድነት በህዝባዊ ንቅናቄው ሲያነሳቸው የነበሩ ጥያቄዎች አንድነትን ብቻ የሚመለከቱ አይደሉም ፡፡እኛም የምንታገልላቸው እንዲመለሱ የምንፈልጋቸው ጥያቄዎች በመሆናቸው ትግሉን በአንድነት ለማደረግ ስምምነት ላይ ደርሰናል››ብለዋል፡፡

 የአንድነት የድርጅት ጉዳይ ሃላፊ የሆኑት አቶ ስዮም መንገሻ ‹‹አንድነት በአብሮነት የመስራት ስስት የለበትም፡፡እንኳን ከ33 ፓርቲዎች ጋር ይቅርና በኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት እንዲገነባ በሰላማዊ መንገድ ከሚታገል ፓርቲ ጋር በሙሉ ለመስራት በራችን ክፍት ነው፡፡››በማለት የፓርቲውን አቋም አንጸባርቀዋል፡፡

 አንድነት ፓርቲ በጎንደር፣በደሴ፣በአርባ ምንጭ፣በባሌ ሮቢ፣በወላይታ፣በፍቼና በሌሎች ከተሞች ባደረጋቸው ሰላማዊ ሰልፎችና ህዝባዊ ስብሰባዎች ያጋጠሙትን የመብት ረገጣዎቸ፣ኢ ህገ መንግስታዊ ጥሰቶች፣ድብደባዎችና ህገ ወጥ እስራቶች በጋዜጣዊ መግለጫው ላይ ይፋ አድርጓል፡፡በፍቼ ድብደባ የደረሰባቸው የፓርቲው ሁለት አባላት ነብዮ ባዘዘውና መሳይ ትኩ በአካል በመቅረብ ለጋጠኞች የደረሰባቸውን ድብደባ አስረድተዋል፡፡እጁ ላይ በድብደባው ምክንያት ስብራት የደረሰበት መሳይ በፋሻ የተጠቀለለ እጁን በማሳየት ‹‹ሁላችንም እናንተ ጋዜጠኞችም ባላችሁ መሳሪያ እስክሪብቶ እውነቱን በመጻፍ ይህንን አምባገነን ስርዓት መታገል ይጋችኋል››ብሏል፡፡

33 ፓርቲዎች በወርሃ መስከረም ቀጠሮ ስለያዙበት የአዲስ አበባ ሰላማዊ ሰልፍ ያወጡት መግለጫ የሚከተለው ነው፡፡

No comments: