Monday, August 19, 2013

ለአቶ መለስ ሙት አመት መታሰቢያ የመንግስት ሰራተኞች በግድ እንዲገኙ ታዘዙ

ነሃሴ ፲፫(አስራ ሦስት)ቀን ፳፻፭ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-  የቀድሞ ጠ/ሚኒስትር አቶ መለስ ዜናዊ ሙት ዓመት በነገው ዕለት በአዲስ አበባ ጉለሌ ዕጽዋት ማዕከል በልዩ ልዩ
ፕሮግራም ታስቦ እንደሚውል ለማወቅ የታቸለ ሲሆን፣ በዛሬው እለት ደግሞ  የተለያዩ የመንግስት ሰራተኞች ምሽትና ነገ  ሻማ በማብራት እንዲዘክሩት ታዘዋል።

አንዳንድ የመንግስት ሰራተኞች  ኢቲቪ አቶ መለስ ዜናዊ ከተናገራቸው ንግግሮች መካከል እያለ ሲያቀርብ መሰንበቱ እንዳሰለቻቸው ተናግረው፣ የፓርቲው ካድሬዎች በየመስሪያ ቤቱ የሚገኙ ሰራተኞች በግድ ተገኝተው እንዲዘክራቸው ማስፈራሪያ አዘል ቅስቀሳ በማካሄድ ላይ መሆናቸውን ገልጸዋል።

ነሃሴ 7 ቀን 2005 ዓ.ም በአዲስአበባ የመለስ ዜናዊ የአረንገዴ ልማት ማዕከል የመሰረት ድንጋይ  በአድዋ
ፓርክ የተጣለ ሲሆን የዚህን ፕሮጀክት ወጪ የአዲስአበባ ከተማ አስተዳዳር ለመሸፈን ቃል መግባቱን መዘገባችን ይታወቃል።
ከሃያት ሆስፒታል ፊት ለፊት ማረፊያውን የሚያደርገው ማዕከሉ ከ100 ሄክታር በላይ ስፋት ሲኖረው ፥  በተለያዩ
የአረንጓዴ ዕፅዋት በመሸፈን በውስጥ ትላልቅ የመዝናኛ ስፍራዎችን ያካትታል ተብሏል።

ባለፉት 15 ቀናት የአዲስአበባና የክልል ከተሞች ነዋሪዎች እና የመንግስት ሰራተኞች ዕለቱን ለማሰብ የችግኝ
ተከላ ማካሄዳቸው የሚታወስ ሲሆን መንግስትም በዚህ አጋጣሚ የመለስን ሌጋሲ ለማስቀጠል የገባውን ቃል ዳግም
ያደሰበት አጋጣሚ መሆኑን በመንግስት መገናኛ ብዙሃን ሲናገር ከርሟል።

አቶ መለስ ዜናዊ ታምመው በሕክምና ሲረዱ መቆየታቸው በከፍተኛ ሚስጢር ተይዞ ከቆየ በኃላ ነሃሴ 14 ቀን 2004
ዓ.ም መሞታቸውን መንግስት በይፋ ማመኑ የሚታወስ ነው፡፡

ገዢው ፓርቲ የአቶ መለስን ሞት ለፖለቲካ ድጋፍ ማስገኛ እየተጠቀመበት ነው በሚል ሲተች ቆይቷል። አቶ መለስ በኢኮኖሚው ዘርፍ መጠነኛ ለውጥ እንዳመጡ ቢነገርላቸውም፣ የኢትዮጵያን ህዝብ አንድነት በማዳከም፣ አገሪቱን ወደብ አልባ በማድረግና የሰብአዊ መብቶችን በመጣስ ይወቀሳሉ። በህይወት በነበሩበት ጊዜ በተለይም ኢፈርት የተባለ የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ ተቆጣጥሮ ዬያዘ የንግድ ኩባንያ እንዲቋቋም በማድረግ አንድን ብሄር ብቻ ለመጥቀም ተንቀሳቅሰዋል እየተባሉ በተቃዋሚዎቻቸው ይተቹ ነበር።

ባለቤታቸው ወ/ሮ አዜብ መስፍን የመለስን ፋውንዴሽን በበላይነት እየመሩ ይገኛሉ።

No comments:

Post a Comment