Thursday, August 1, 2013

በኮሚሽኑ መርማሪ ቡድን የምርመራ ሒደት ላይ ፍርድ ቤት ጥያቄ አቀረበ‹‹አቶ መላኩ ፈንታ የተሻለ ዕውቀትና ተሰሚነት አላቸው ተብሎ ይገመታል››

የኮሚሽኑ መርማሪ ቡድን

በከባድ የሙስና ወንጀል ተጠርጥረው በቁጥጥር ሥር በሚገኙት የኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ከፍተኛ ሹማምንት፣ ኃላፊዎች፣ ሠራተኞች፣ ነጋዴዎችና ግለሰቦች ላይ የሚደረገው ምርመራ እንዳልተጠናቀቀ በመግለጽ፣ ለስምንተኛ ጊዜ ተጨማሪ የ14 ቀናት እንዲፈቀድለት ለፍርድ ቤት ጥያቄ ባቀረበው የፌዴራል የሥነ ምግባርና የፀረ ሙስና ኮሚሽን መርማሪ ቡድን ላይ ፍርድ ቤቱ ጥያቄ አቀረበ፡፡

የኮሚሽኑ መርማሪ ቡድን ያቀረበውን ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ ጥያቄ ተከትሎ በምርመራ ሒደቱ ላይ ጥያቄ ያቀረበው፣ የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ሁለተኛ የወንጀል ችሎት ሐምሌ 22 ቀን 2005 ዓ.ም. የቀረበለትን የእነ አቶ መላኩ ፈንታና የእነ አቶ ገብረዋህድ ወልደጊዮርጊስ የምርመራ መዝገብን አይቶ ነው፡፡

መርማሪ ቡድኑ ባለፉት አሥር ቀናት በተጠርጣሪዎቹ ዙሪያ ያከናወናቸውን የሰዎች ምስክሮችን ቃል መቀበል (የ27 ሰዎች ቃል) መቀበሉን፣ የሰነድ ማስረጃዎችን መሰብሰቡን፣ የተወሰኑ ኩባንያዎችን የኦዲት ምርመራ ውጤት መቀበሉን፣ በመስክ የምርመራ ሥራ ከተሰማሩ የቡድኑ አጋሮች የምስክሮችን ቃልና የሰነድ ማስረጃዎችን መሰብሰቡን ለፍርድ ቤቱ አስረድቷል፡፡

የእያንዳንዱን ተመርማሪ የተሳትፎ ሁኔታ በመግለጽ ያከናወነውን የምርመራ ሒደት ከገለጸ በኋላ፣ ቡድኑ የቀረውን ምርመራም አስታውቋል፡፡ የቀሩትን የምርመራ ሒደቶች እንደገለጸው፣ በቦሌ ኤርፖርት በኮንትሮባንድ ሲገቡ የተያዙና የተለቀቁ ዕቃዎች፣ በፍራንኮ ቫሉታ በሕገወጥ መንገድ ስለገባ ሲሚንቶ፣ ኦዲት ያልተደረጉ ግን በመደረግ ላይ ያሉ ድርጅቶች፣ የታክስ ማጭበርበርና ዝቅ አድርጎ መገመት፣ ከጥቆማ አበል ጋር በተያያዘ፣ በቃሊቲ ጉምሩክ በሕገወጥ መንገድ የገቡ ዕቃዎች፣ ከሚሌ፣ ከድሬዳዋና ከሌሎች ቅርንጫፍ መሥሪያ ቤቶች ሰነዶችን ማሰባሰብና የምስክሮችን ቃል መቀበል (የ26 ምስክሮች ቃል) እንደሚቀረው በማብራራት ተጨማሪ የ14 ቀናት ጊዜ እንዲፈቀድለት ጠይቋል፡፡

ፍርድ ቤቱ ለመርማሪ ቡድኑ ያቀረበው ጥያቄ፣ ‹‹የኦዲት ሥራው በመጠናቀቅ ላይ እንደነበር ገልጻችኋል፡፡ ምን ላይ ደረሰ? ቀሩን ያላችኋቸውን ምስክሮች ቃል ለምን እስካሁን አልተቀበላችሁም? የመስክ የምርመራ ሥራ መጠናቀቁን ገልጻችሁ ነበር፡፡ አሁን ደግሞ እንደ አዲስ አቅርባችኋል፡፡ ምን ማለት ነው? የኦዲት ሥራ እስከ ሐምሌ 30 ቀን 2005 ዓ.ም. ድረስ እንደምታጠናቅቁ ገልጻችሁ ነበር፣ አሁን ደግሞ ለኦዲት ሥራ ማስረጃ እያሰባሰባችሁ መሆኑን ያሳያል፣ ምን ማለት ነው? የሰነድ ማስረጃ ለኦዲት ሥራ መሠረታዊና አስፈላጊ መሆኑ ግልጽ ነው፡፡ ኦዲት መርማሪዎቹ የሚፈልጉትን አቅርባችሁ ነው ሥራ የጀመሩት፡፡ በመሰብሰብ ላይ ነን ማለት ምን ማለት ነው?›› የሚል ነበር፡፡ ፍርድ ቤቱ ጥያቄውን ያነሳው የተጠርጣሪዎች ጠበቆች ተጨማሪ ጊዜ መጠየቁንና እንደ አዲስ የማስረጃ ሰነድ መሰብሰብ እንደሚቀረው መርማሪ ቡድኑ ያቀረበውን ጥያቄ በከፍተኛ ሁኔታ በመቃወማቸው ነው፡፡

መርማሪ ቡድኑ ከፍርድ ቤቱ ለቀረበለት ጥያቄ በሰጠው ምላሽ፣ ‹‹የኦዲት ሥራ የሚሠራው በአንድ መሥሪያ ቤት ተሰብስቦ በተቀመጠ ሰነድ ብቻ አይደለም፤›› ሲል፣ ፍርድ ቤቱ አስቁሞት ‹‹ፍርድ ቤቱ ይኼንን ያውቃል፤ ይረዳል፤ ለቀረበው ጥያቄ ብቻ ምላሽ ስጡ፤›› በማለት ሲያስቆመው ቡድኑ በጥያቄዎቹ ላይ ምላሽ መስጠቱን ቀጠለ፡፡

ቀሪ ሥራዎች አሉኝ ካላቸው ውስጥ በተከለከለ የፍራንኮ ቫሉታ ፈቃድ ሲሚንቶ ማስገባትን በሚመለከት፣ ካለፉት ስድስት ቀጠሮዎች ለየት ያለ ነገር መርማሪ ቡድኑ አቅርቧል፡፡ የነፃና ባሰፋ ትሬዲንግ ኩባንያዎች ባለቤት አቶ ነጋ ገብረ እግዚአብሔር በዋናነት የተጠረጠሩበት በተከለከለ የፍራንኮ ቫሉታ ፈቃድ ሲሚንቶ በማስገባታቸው የተመሠረተባቸው ክስ እንዲቋረጥ መደረጉን በሚመለከት፣ በስድስት ቀጠሮዎች ላይ የሰነድ ማሰባሰብ እንደቀረው መርማሪ ቡድኑ የገለጸ መሆኑ ቢታወስም፣ ሐምሌ 22 ቀን 2005 ዓ.ም. ያቀረበውና ቀሪ ምርመራ እንዳለው የገለጸው ቡድኑ፣ ሲሚንቶው ወደ አገር ውስጥ የገባው ለአዲስ አበባ ቤቶች ልማት ኮንስትራክሽን ጽሕፈት ቤት ቢሆንም፣ ሲሚንቶው ለጽሕፈት ቤቱ ሳይደርስ በሌላ ቦታ ለሽያጭ መዋሉን የሚያሳይ ሰነድ ለማግኘት ከጽሕፈት ቤቱ ጋር እየተነጋገረ መሆኑን አስረድቷል፡፡ 

የኦዲት ምርመራን በሚመለከት በፊት ካላቸው ሦስት ድርጅቶች በተጨማሪ ሁለት ድርጅቶች መኖራቸውን የገለጸው መርማሪ ቡድኑ፣ ኦዲተሮቹ እንደነገሩት ከሆነ እስከ ሐምሌ 30 ቀን 2005 ዓ.ም. ኦዲት ተደርጎ ሊጠናቀቅ እንደሚችል በመግለጽ፣ ሁኔታውን ከባለሙያዎቹ ለማረጋገጥ ፍርድ ቤቱ ኦዲተሮቹን ጠርቶ ሊያነጋግራቸው እንደሚችል ሐሳብ አቅርቧል፡፡ ሥራውን ከፍተኛ የሰው ኃይል በመመደብ ተረባርቦ እየሠራ መሆኑንም ቡድኑ ተናግሯል፡፡ የመስክ ሥራ ቢጠናቀቅም ከዋና መዝገብ ጋር ሲወራረስ የጎደለ ነገር በመኖሩ፣ ቀሪዎቹን ማስረጃዎች ለማምጣት መርማሪ ቡድን ወደ ሚሌ፣ ድሬዳዋና ሌሎች ቦታዎች መላኩንም አክሏል፡፡

የተጠርጣሪዎቹ ጠበቆች በጊዜ ቀጠሮው መራዘም ምክንያት የተሰላቹ በሚመስል ሁኔታ፣ ‹‹ምርመራው መቼ ነው የሚጠናቀቀው?›› በማለት ጠይቀው፣ ቢፒአር መሠራቱን ፍርድ ቤት፣ ፌዴራል ፖሊስ፣ አዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽንና ማረሚያ ቤት አራቱ መሥሪያ ቤቶች በጋራ የተፈራረሙበት የምርመራ ጊዜ መወሰኑን ተናግረዋል፡፡ በመሆኑም ዝቅተኛ፣ መካከለኛና ከፍተኛ ተብሎ የምርመራ ጊዜ መቀመጡን ያስረዱት የአቶ እሸቱ ወልደ ሰማያት ጠበቃ፣ ከፍተኛው ሦስት ወራት መሆኑን በመጠቆም ደንበኛቸው ሦስት ወራት እየሞላቸው በመሆኑ ፍርድ ቤቱ ትዕዛዝ እንዲሰጥበት አሳስበዋል፡፡

ሁሉም ጠበቆች መርማሪ ቡድኑ የጠየቀውን ተጨማሪ የ14 ቀናት ጊዜ ተቃውመው፣ ደንበኞቻቸው ከእስር እንዲፈቱ ወይም የዋስትና መብታቸው ተጠብቆ በውጭ ሆነው ጉዳያቸውን እንዲከታተሉ ጠይቀዋል፡፡ የአቶ መላኩ ፈንታ ጠበቃ ባቀረቡት ተቃውሞ፣ አቶ መላኩ አሁን ባለሥልጣን አለመሆናቸውንና በቦታቸው ላይ ሌላ ሰው መሾሙን በመግለጽ፣ ሥልጣናቸውን በመመካት የሚያባብሉት፣ የሚያስፈራሩት ወይም የሚደብቁት ሰነድ እንደሌለ በመግለጽ፣ የዋስትና መብታቸው ተፈቅዶ እንዲፈቱ ጠይቀዋል፡፡

መርማሪ ቡድኑ ሁሉም ጠበቆች ያነሱትን የዋስትናና የይፈቱልንን ጥያቄ በመቃወምና ውድቅ እንዲደረግለት አመልክቶ፣ አቶ መላኩን በሚመለከት ባቀረበው ተቃውሞ፣ ‹‹አቶ መላኩ የተሻለ ዕውቀትና ተሰሚነት አላቸው ተብሎ ይታሰባል፤›› ካለ በኋላ፣ ቢወጡ በምስክሮችና በቀሪ ሰነድ አሰባሰብ ላይ ተፅዕኖ እንደሚፈጥሩ በማስረዳት፣ የዋስትና መብታቸው ውድቅ እንዲደረግ ጠይቋል፡፡ ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ እንዲፈቀድለት በድጋሚ ጠይቋል፡፡

የግራ ቀኙን ክርክር ያደመጠው የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ሁለተኛ የወንጀል ችሎት፣ ተጠርጣሪዎቹ ያቀረቡትን የመፈታትና የዋስትና ጥያቄ በማለፍ፣ መርማሪ ቡድኑ ከጠየቀው 14 ቀናት አሥሩን በመፍቀድ፣ ለነሐሴ 2 ቀን 2005 ዓ.ም. ቀጠሮ በመስጠት የዕለቱን ችሎት አብቅቷል፡፡ 

በሌላ የምርመራ መዝገብ ማለትም በእነ መሐመድ ኢሳ (6 ሰዎች) እና እነ ባሕሩ አብርሃ፣ እንዲሁም ይስሀቅ እንድሪስ (የመልካሙ እንድሪስ ወንድም) እና ሲሳይ ተሰማ (የአሸብር ተሰማ ወንድም) ሐምሌ 23 ቀን 2005 ዓ.ም. ቀርበው፣ በተጠርጣሪዎቹ ላይ መርማሪ ቡድኑ ያከናወናቸውንና የቀሩትን የምርመራ ሥራዎች ለችሎቱ ካቀረበ በኋላ፣ የ14 ቀናት ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ ጠይቆባቸዋል፡፡

ተጠርጣሪዎቹም የመርማሪ ቡድኑን ጥያቄ በመቃወም የዋስትና መብታቸው እንዲከበርላቸው ጠይቀዋል፡፡ ግራ ቀኙን ያዳመጠው ፍርድ ቤት፣ የተጠርጣሪዎቹን የዋስትና መብት ጥያቄ በማለፍ ለመርማሪ ቡድኑ በእነ መሐመድ ኢሳ መዝገብና ባህሩ አብርሃ መዝገብ የተጠየቀውን የ14 ቀናት በማለፍ ስምንት ተጨማሪ ቀናት ፈቅዷል፡፡ እንዲሁም በይስሀቅ እንድሪስና ሲሳይ ተሰማ ላይ የስድስት ቀናት ተጨማሪ ጊዜ ፈቅዷል፡፡ 

No comments:

Post a Comment