ሐምሌ 13 ቀን 2005 ዓ.ም
«ነጻነትን ማንም አይሰጥህም። እኩልነትና ፍትህንም ማንም አይሰጥምህ። ሰው ከሆንክ፣ አንተዉ እራስህ ተቀበለው» ነበር ያሉት፣ የሰብአዊ መብት ተሟጋች ማልኮም ኤክስ። ነጻነትና ሰላም፣ ዴሞክራሲና ፍትህ፣ እኩልነትና መልካም አስተዳደር፣ ሌሎች የሚሰጡን ሳይሆን፣ ፈጣሪ በቸርነቱ የለገሰን፣ ደፍረንና ፈቅደን የምንቀበላቸው፣ የኛዉ የሆኑ በረከቶች ናቸው።
ነገር ግን ለአመታት መብታችንና ነጻነታችን፣ በጥቂቶች ተገፎ፣ ሁላችንም በየጓዳችን ስንናደድ፣ ስናማርር፣ ስናዝን፣ ስንራገም፣ ልባችን ሲደማ፣ «እንደዉ ምን ይሻላል? » እየተባባልን ስናወራ ቆይተናል። ለዜጎቿ ሁሉ እኩል የሆነች፣ ሕግ የበላይ የሆነባት፣ ፍትህ የሰፈነባት፣ ሕዝቡ ለመሪዎች ሳይሆን መሪዎች ለሕዝብ የሚንበረክኩባት፣ ዴሞክራሲያዊት ኢትዮጵያን ለማየት ትልቅ ጉጉት አለን።
ማልኮም ኤክስ እንዳሉት፣ ፍትህንና እኩልነትን እንዲያመጡልን፣ ሌሎችን መጠበቅ የለብንም። እያንዳንዳችን መንቀሳቀስ ይኖርብናል። በአገር ቤት፣ በጎንደርና በደሴ እንደታየው፣ ከፍተኛ፣ ሰላማዊ፣ የሰለጠነ የፍቅር ፖለቲካ ላይ ያተኮረ፣ እንቅስቅሴ እየተደረገ ነዉ። እንቅስቅሴዎቹ በባህር ዳር፣ በፍቼ፣ በጂንካ፣ በአርባ ምንጭ፣ በአዳማ፣ በመቀሌ፣ በወላይታ ሶዳ፣ በጋምቤላ በአሶሳ .. እያለ ይቀጥላል። በአገሪቷ ክልሎች ሁሉ ያለው ሕዝቡ መብቱንና ነጻነቱን እንዲያስከብር ቅስቀሳ ይደረጋል። ለምን ? የምንፈልጋት ኢትዮጵያ ልትመጣ የምትችለው እኛን ጨምሮ ሕዝቡ ቀን ሲል ብቻ በመሆኑ።
በዉጭ አገር ያለነዉ ፣ አገር ቤት ያለው ሕዝብ አካል ነን። «ምን ተደረገ?» እያልን የምንከታተል ብቻ ሳይሆን፣ የሚደረጉት እንቅስቃሴዎች አካል መሆን መቻል አለብን። እምነት ያለን በጸሎታችን፣ ገንዘብ ያለን በገንዘባችን፣ ጠቃሚ፣ ትግሉን ወደፊት ሊያስኬዱ የሚችሉ ምክሮችና አስተያየቶች ያሉን፣ ሃሳቦቻችን በማቅረብ፣ ትልቅ አስተዋጽኦ ማድረግ እንችላለን። ይገባናልም።
የአንድነት ፓርቲ የሚሊዮኖች ድምጽ ለነጻነት ግብረ ኃይል፣ ለሕዝብ ይፋ ያደረገዉን የሶስት ወራት እንቅስቃሴ ለመደገፍና ለማገዝ፣ በዳያስፖራ የሚሊየኖች ድምጽ ለነጻነት ግብረ ኃይል ተቋቁሟል። ግብረ ኃይሉ የተለያዩ መርሃ ግብሮችን አውጥቶ፣ ዳያስፖራዉ እንዴት ሊረዳ፣ ሊደግፍና የሚሊዮኖች አንዱ ሊሆን እንደሚችል መረጃዎች የሚያቀርብና አቅጣቻዎችን የሚያሳይ ይሆናል። በዉጭ አገር የሚገኙ ሬዲዮች፣ ቴሌቭዥኖች ፣ ድህረ ገጾች፣ የሲቪክ ማህብራትና በዉጭ ያሉ የፖለቲካ ድርጅቶች ሁሉ ድጋፋቸዉን እንዲሰጡንም በአክብሮት ጥሪ እናቀርባለን።
በኢትዮጵያ ወገኖቻችን ትልቅ ዋጋ እየከፈሉ ነዉ። በዉጭ አገር ያለን ኢትዮጵያውያን፣ ከዚህ በፊት ብዙ ለአገራችን ደክመናል። አሁን ወሳኝ ወቅት ላይ እንዳለን ተረድተን፣ ከዚህ በፊት ካደረግነዉ በላይ ለማድረግ እንነሳ። ትላንት ወድቀን ቆስለን ሊሆን ይችላል። የትላንቱ ጠበሳ ወደፊት እንዳንሄድ ሊያግደን ግን አይገባም። ከወደቅንበትና ከተኛንበት ተነስተን፣ ከቆምንበት ተንቀሳቅሰን፣ ወደፊት በመሄድ መቻል አለብን።
ከሚሊዮኖች አንዱ እንሁን ! በዚህ ወቅት እኛ ካልተባበረን ማን ? ? ዛሬ ካልሆነ መቼ ?
No comments:
Post a Comment