የአንድነት ፓርቲ አመራር አባላት፣ በጎንደርና በደሴ የሚያደርጉትን ቅስቀሳ ቀጥለዉበታል። በደሴ ወረቀቶች እየተበተኑ፣ ፔትሽኖችም እየተሞሉ ሲሆን፣ በመኪና ላይ በመሆንና በየሰፈሩ በመዘዋወር በላውድ ስፒከር የትግል ጥሪ እየተላለፈ ነዉ።
እንደዚያም ሆኖ ግን ገዢው ፓርቲ ኢሕአዴግ፣ ባህሪዉ ነዉና፣ አፍራሽ እርምጃዎችን ከመዉሰድ አልተቆጠበም። ላለፉት ሃያ አመታት እንዳደረገዉ፣ የሕዝብን መሰረታዊ የዴሞክራሲ ጥያቄዎችንና ሕገ መንግስታዊ መብቶች ለማፈን ደፋ ቀና እያለ ነዉ። አቶ ነብዩ ፣ የፍኖት ጋዜጣ ዋና ኤዲተር እንደገለጹት « መንግስታዊ ሽፍታነቱን ገፍቶበታል» ። ዛሬ ጠዋት ሐምሌ 3 ቀን በደሴ ከተማ የቅስቀሳ ተልእኳቸዉን ለመወጣት፣ ከአዲስ አበባ የተጓዙትን የአንድነት ፓርቲ ብሄራዊ ምክር ቤት ሰብሳቢ አቶ ዘካርያስ የማነብርሃንና የፍኖት ነጻነት ጋዜጠኛ የሆነዉን አቶ ወንደወሰን ክንፈን በማገት «እንደራደር» በማለት ላይ ይገኛል።
«አግተዉ እንደራደር የሚሉት ሽፍቶች ናቸው። መንግስት አግቶ እንደራደር ሲል ሽፍታነቱ በአደባባይ መረጋገጡ ነዉ» ያሉት አቶ ነብዩ «አንድነት የፓርቲዉ ጽ/ቤት እስኪዘጋና አባላቱ እሥር ቤቶችን እስኪሞሉ ሕዝባዊ ንቅናቄዉ ይቀጥላል» የሚል የጸና አቋም አባላቱና ደጋፊዎቹ እንዳላቸው አስረድተዋል። ፓርቲው ያነሳዉ ሕዝባዊ ጥያቄ በመሆኑ «የአንድነት አመራሮችና አባላት መስዋእት ቢሆኑም ሕዝቡ ትግሉን ከዳር እንደሚያደርሰው አንጠራጠርም» ሲሉም ትግሉ ወሳኝ ምእራፍ ላይ እንዳለ ሳይጠቁሙ አላለፉም።
የሰማያዊ ፓርቲ በቅርቡ በአዲስ አበባ በጠራው ፣ መኢአድና አንድነትም በደገፉት የሰላማዊ ሰልፍ፣ የአዲስ አበባ ሕዝብ በአገዛዙ ላይ ያለዉን ተቃዉሞ ማሰማቱ ይታወቃል። በወቅቱ ሰልፈኞቹ ባለፉባቸው መንገዶች ዙሪያ አንድ የተዘጋ ሱቅ እንዳለነበረ፣ አንድ ጠጠር እንዳልተወረወረና ፍጹም ሰላማዊ በሆነ መንገድ ሰልፉ እንደተጠናቀቀ የሚታወቅ ነዉ። የአንድነት ፓርቲ፣ በአንድ ጊዜ በደሴና በጎንደር ከተሞች የጠራቸው ሰላማዊ ሰልፎች ሕዝባዊ እንቅስቃሴዉ፣ አዲስ አበባ ብቻ የተወሰነ ሳይሆን፣ አገር አቀፍ መሆኑንም በግልጽ ያሳየ ነዉ።
ለሚደረጉት እንቅስቃሴዎች የሚያስፈልጉ ከፍተኛ ወጭዎችን አገር ቤት ያለው ድሃዉ ሕዝብ፣ በራሱ ተነሳሽነት በስፋት እየሸፈነዉ እንዳለ እየገለጹ ያሉት የአንድነት አመራር አባላት፣ ዳያስፖራዉ በአገሩ ጉዳይ ላይ እንግዳ ሆኖ፣ ተነጥሎ መቆም እንደሌለበት፣ ሁኔታዎችን በቅርበት እንዲከታታልና የድርሻዉንም ለመወጣት መዘጋጀት እንዳለበት አሳስበዋል።
No comments:
Post a Comment