Wednesday, June 12, 2013

ኢትዮጵያና ግብጽ የቃላት ጦርነት መወራወር ጀምረዋል።

<<ማናቸውንም እርምጃ ለመውሰድ በሩ ክፍት ነው>>ግብጽ

<<በቀረርቶ ተደናግጠን ለሰከንድ የግድብ ግንባታውን አናቆምም>>-ኢትዮጵያ

በሁለቱ አገሮች መካከል መተነኳኮሱ እየባሰ የመጣው ዘንድሮ ግንቦት 20 ቀን የተከበረውን የገዥውን ፓርቲ በኣል ምክንያት በማድረግ ኢትዮጵያ ፦” የአባይ ወንዝን የተፋሰስ አቅጣጫ አስቀየስኩ” ብላ ማወጇን ተከትሎ ነው።
ይህን ተከትሎ በተለይ የግብጽ መንግስት -ከተቃዋሚዎቹ ጋር በመሆን በኢትዮጵያ ላይ እስከ ወታደራዊ ጥቃት ድረስ የሚደርስ እርምጃ ለመውሰድ የመከሩበት ስብሰባ በይፋ ታየ፤

 ይሁንና የግብጽ መንግስት-ከተቃዋሚዎቹ ጋር በመሆን ኢትዮጵያ ላይ ለመውሰድ ስለታሰበው እርምጃ ሲመክሩበት የነበረው ስብሰባ በቀጥታ የቴሌቪዥን ስርጭት መተላለፉ፤ግብጽ -ኢትዮጵያን ለማስፈራራት መፈለጓን የሚያሳይ ተራ ጨዋታ ነው በሚል ብዙዎች ትኩረት ሳይሰጡት ቆይተዋል
ይህ በ እንዲህ እንዳለ ትናንት የግብጹ ፕሬዚዳንት መሀመድ ሙርሲ ፦ኢትዮጵያ በምትሠራው ግድብ ሳቢያ ወደ ግብጽ ከሚፈሰው የ አባይ ወንዝ የጠብታ ያህል ከቀነሰ አገራቸው ግብጽ ማናቸውንም እርምጃዎች ኢትዮጵያ ላይ ለመውሰድ ዝግጁነቱ እንዳላት አስታውቀዋል።

 ከ ኢትዮጵያ ጋር ጦርነት እንደማይፈልጉ፤ ግድቡን ለማስቆም የሚያደርጉት ጥረት ካልተሳካ ግን ሁሉንም አማራጭ እርምጃዎች ለመውሰድ እንደሚገደዱ ነው ፕሬዚዳንቱ የተናገሩት።
ኢትዮጵያ - አቅጣጫውን የቀየረው የወንዙ ፍሰት ሀይል ካመነጨ በሁዋላ ተመልሶ በመደበኛው መስመር እንደሚፈስ እና በግብጽም ሆነ በሱዳን ላይ የሚፈጥረው ነገር እንደማይኖር ደጋግማ ብታሳውቅም፤ፕሬዚዳንት ሙርሲ ፈጽሞ የግብጽ የውሀ ደህንነት ሊነካ አይገባም! በማለት የ ኢትዮጵያን ምላሽ እንደማይቀበሉት አስታውቀዋል።
“የ አገሪቱ ፕሬዚዳንት እንደመሆኔ መጠን ሁሉንም እርምጃዎች ለመውሰዱ በሩ ክፍት መሆኑን አሳውቃለሁ” ነው ያሉት -ፕሬዚዳንት ሙርሲ።
በማያያዝም፦”ግብጽ የዓባይ ስጦታ ከሆነች፤ዓባይ የግብጽ ስጦታ ነው”ብለዋል-በስሜት ውስጥ ሆነው በቴሌቪዥን ባደረጉት ንግግር።
እንደ አንድ ታላቅ ህዝብ የግብፃውያን ህይወትና ኑሮ ከ ዓባይ ጋር የተያያዘ ነው ያሉት ፕሬዚዳንት ሙርሲ፤ ፍሰቱ በ አንዲት ጠብታ ከቀነሰ ያለን ቀሪ አማራጭ ደማችን ነው”ብለዋል።
የግብጽን ተደጋጋሚ ዛቻ ተከትሎ የ ትዮጵያ የውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር ዛሬ ባወጣው መግለጫ፦<<ኢትዮጵያ በቀረርቶ ተደናግጣ ለሰከንድ የግድብ ግንባታዋን አታቆምም>>ብሏል።

ኢትዮጵያ ከምንም በላይ ለትብብር ፣ ለወዳጅነትና ለጋራ ጥቅም ያላትንም ፅኑ እምነት በወቅቱ ግልፅ አድርጋለች ያለው የሚኒስቴሩ መግለጫ ፥ ይህ በእንዲህ እንዳለ ትናንት ብሄራዊ የናይል ጉባኤ በተሰኘው ስብሰባ ላይ የግብጽ ፕሬዚዳንት ፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ፣ ሚኒስትሮችና ሌሎችም በተገኙበት ታላቁን የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ አስመልክቶ አፍራሽ መልዕክቶች ተላልፈዋል ብላል ።
በዚህ ረገድ በግብፅም ሆነ በሌላ ማንኛውም ወገን የሚቀርብ የግድቡን ግንባታ የማዘግየት ወይም ከነአካቴው የማቋረጥ ነገር ፈፅሞ ተቀባይነት እንደማይኖረው የውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር ገልጿል ።

 ጦርነትና ሌሎች አፍራሽ ስልቶችን ስለመጠቀም የሚቀርቡት ሀሳቦች ያረጁና ያፈጁ ፣ የ21ኛውን ክፍለ ዘመን አስተሳሰብ የማይሸከሙ ፣ እና ጤናማ ያልሆኑ አስተሳሰቦች እንደሆኑ የገለጸው የውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር፤ ኢትዮጵያ በዚህ ቀረርቶ ተደናግጣ ግንባታውን ለሰኮንድም አታቆምም ብላል።

 ጉዳዩን በትኩረት እየተከታተሉ ያሉ የፖለቲካ ተንታኞች ግን ሁለቱ መንግስታት የቃላት ጦርነት ውስጥ የገቡት በውስጣዊ አስተዳደራቸው የተፈጠረባቸውን ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ቀውስ ለመጠምዘዝ እንደሆነ በስፋት አስተያየት ሢሰጡ ይደመጣሉ።

No comments:

Post a Comment