“ኢህአዴግን ምን እናድርገው? ንገሩን!”
አሜሪካ ከመቼውም ጊዜ በላይ ደንግጣለች። ኦባንግ እንዳሉት ለህዝባቸው “ሬት” ለምዕራባውያንና “ማር” (የቤት ቀጋ፤ የውጭ አልጋ) የነበሩት አምባገነን በድንገት እንደ ተነቀለ ቡሽ ተስፈንጥረው ከሲስተም መውጣታቸው አሜሪካንን አስጨንቋታል። በተለይም እሳቸው አፍነው የያዙት የስርዓቱ “ክፉ ጠረን” አሁን እነርሱ (አሜሪካውያኑ) ደጅ የደረሰ ያህል መፍትሄ ለመፈለግ የወሰኑ ይመስላሉ። አውቀውና ፈቅደው ሲታለሉ የቆዩበትን ጊዜ አስልተው መንገዳቸውን የማስተካከል ስራ የጀመሩት ዛሬ አይደለም። አንዳንድ ምንጮች እንደሚሉት ከመለስ ሞት በኋላ አሜሪካ በምስራቅ አፍሪካ ላይ ሚዛኗን ሊያስታት የሚችል ውድቀት የሚደርስባት ኢትዮጵያ ላይ ያላትን አቋም ማስተካከል ሲያቅታት ብቻ እንደሆነ ይናገራሉ።
“… ሆን ተብሎ በተቀነባበረ እቅድ ህወሃት አዲስ አበባን እንዲቆጣጠር የተወሰነው ውሳኔ አሳዛኝና ከቶውንም ሊታመን የማይችል ነው። የሰከረ ርዕዮት ዓለም የሚከተሉ፣ በብሄርና በጎሳ ፖለቲካ ላይ የተተከሉ ጠባብ ቡድኖች፣ በስታሊናዊ መርህ የተጠመቁ፣ እንኳንስ 50 ሚሊዮን ህዝብ ያላት አገር ቤተሰብን የመምራትና የማስተዳደር ተሞክሮ የሌላቸው፣ አገርን መምራትን የሚያክል ታላቅ ሃላፊነት ማሸከም ለኔ ከአእምሮ በላይ ነው …” የዛሬ 22ዓመት ኮሎኔል ጎሹ ወልዴ ከተናገሩት፡፡
“አሜሪካኖች ነጻ እንድታወጡን አንጠይቃችሁም። የኢትዮጵያ ህዝብ እንዴት ነጻ እንደሚወጣ ያውቃል። እናንተ ግን በነጻነት መንገዳችን ላይ ዕንቅፋት አትሁኑብን፤ (የነጻነት መንገዱን አትዝጉብን)። ከመንገዱ ላይ ገለል በሉ … እስካሁን ያልተሞከረ መንገድ አለ … እሱም እርቅ ነው … ከመንግሥትም ሆነ ከተቃዋሚው በኩል ዓመኔታ የሚጣልባቸው አሉ … ” አቶ ኦባንግ ሜቶ፡፡
“የሚታየኝ ጦርነት ነው፣ የርስ በርስ ግጭት ነው። የርስ በርስ ግጭት በኢትዮጵያ የመነሳቱ ጉዳይ የማይቀር ነው። አገሪቱ ላለፉት 21 ዓመታት በተጓዘችበት መንገድ አትቀጥልም። … ሕዝብ በጭቆና አገዛዝ እየተገዛ ዝም ብሎ የማይኖርበት ደረጃ ላይ ደርሷል … ዝም ብሎ ግን አይቀመጥም … ይፈነዳል … ይህን እንድትገነዘቡ እፈልጋለሁ” ዶ/ር ብርሃኑ ነጋ፡፡
አቶ መለስ “አሮጋንት /እብሪተኛ/፤ የፈለገውን ነገር በፈለገው ጊዜ የሚያደርግ ሰው … እንደነበር አዲስ አበባ ሄጄ ባነጋገርኩበት ወቅት አረጋግጫለሁ” ክሪስ ስሚዝ፡፡
“እድሜ ልካችሁን አትገዙም ብለን መክረናቸዋል” ዶናልድ ያማሞቶ፡፡
የምክክሩ መድረክ
“ኢትዮጵያ ድኅረ መለስ፤ የዴሞክራሲና ሰብዓዊ መብቶች የወደፊት ዕጣ በኢትዮጵያ” በሚል ርዕስ፤ ከኢትዮጵያ ሁለት ተናጋሪዎች ዶ/ር ብርሃኑ ነጋ እና አቶ ኦባንግ ሜቶ፤ በኢትዮጵያ የአሜሪካን አምባሳደር የነበሩትና በአሁኑ ወቅት በአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚ/ር የአፍሪካ ጉዳዮች ተጠባባቂ ጸሐፊ ዶናልድ ያማሞቶ፣ የአሜሪካ የዓለምአቀፍ የልማት ተራድዖ የአፍሪካ ቢሮ ረዳት አስተዳዳሪ ኤሪል ጋስት፤ የማይክል አንሳሪ የአፍሪካ ተቋም ዳይሬክተር ዶ/ር ፒተር ፓሃም እንዲሁም በአምነስቲ ኢንተርናሽናል የመንግሥት ጉዳዮች ዋና ዳይሬክተር አዶቴ አክዌ የተጋበዙበት የምክክር ሸንጎ ላይ የቀረቡት ሃሳቦች በርካታ ጉዳዮችን የዳሰሱ ነበሩ። ሰብሳቢው በአሜሪካ የተወካዮች ምክርቤት በአፍሪካ፣ በዓለምአቀፍ ጤናና ሰብዓዊ መብቶች እንዲሁም ዓለምአቀፋዊ ድርጅቶች ንዑስኮሚቴ ሰብሳቢ ክሪስቶፈር ስሚዝ ደግሞ ኢህአዴግ ከፍተኛ ገንዘብ አፍስሶ ያኮላሽው ኤችአር2003 የኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብት ረቂቅ ህግ ከሟቹ ዶናልድ ፔይን ጋር በማዘጋጀት በምክርቤት ለማስወሰን ያስቻሉ ነበሩ።
የአዲሲቷ ኢትዮጵያ የጋራ ንቅናቄ (አኢጋን) ዋና ዳይሬክተር አቶ ኦባንግ ሜቶ፣ እንዲሁም በበክኔል ዩኒቨርሲቲ የኢኮኖሚክስ ተባባሪ ፕሮፌሰር የሆኑት የግንቦት 7 ሊቀ መንበር ዶ/ር ብርሃኑ ነጋ እንደ እምነታቸው ንግግር አድርገዋል። ለተጠየቁት ጥያቄ ምላሽ ሰጥተዋል። በምክክር ሸንጎው ላይ ከተጋበዙት መካካል ኢህአዴግ በቀጥታ ባለመወከሉ “ያለመመጣጠን (ያለመወከል)” ችግር አልነበረም፡፡ ኢህአዴግም ተገኝቶ ቢሆን ኖር ሊናገረው ከሚችለው በላይ ተናጋሪና ተከራካሪ ስለነበረው የኢህአዴግ መኖር አስፈላጊ አልነበረም የሚል አስተያየት ስብሰባውን በአካል ተገኝተው ከታዘቡና በቀጥታ ስርጭት ከተከታተሉ ወገኖች ተደምጧል።
ያም ሆኖ ግን ምክክሩ ከመካሄዱ ቀደም ብሎ በአሜሪካ የኢትዮጵያ ኤምባሲ የበላይ ሰው ክሪስ ስሚዝ ቢሮ በመገኘት አሉ የሚሏቸውን መከራከሪያዎች አቅርበው ነበር። የጎልጉል ምንጮች ለማረጋገጥ እንደቻሉት ኢህአዴግ ምክክሩን ተከትሎ ኤች አር 2003 ረቂቅ ሕግ እንዳይጸድቅ የተጠቀመበትን መንገድ ገና ካሁኑ በድጋሚ ጀምሯል።
ለኢትዮጵያውያን ሁሉ እያደር የእግር እሳት ሆኖ ያለፈውን የ1997 ምርጫ ተከትሎ ወደ ኢትዮጵያ በማምራት ከኢህአዴግ መሪ አቶ መለስ ጋር በርካታ ዲፕሎማቶች ተነጋግረዋል። አንዱ ከኒውጀርሲ ጠቅላይግዛት የአሜሪካ ም/ቤት ተወካይ ክሪስ ስሚዝ ነበሩ።
“ኢትዮጵያ ከመለስ በኋላ” በሚል የተዘጋጀውን የምክክር ሸንጎ በመሪነታቸው ሲከፍቱ አቶ መለስን “አሮጋንት /እብሪተኛ/፤ የፈለገውን ነገር በፈለገው ጊዜ የሚያደርግ ሰው …” በማለት ነበር የገለጹዋቸው። የርሳቸው ገለጻ ታዲያ ከሁለት ዓስርተ ዓመታት በፊት ኢህአዴግ እንዲነግስ ሲወሰን ከቃል በላይ እሳት እየተፉ ንግግር ያደረጉትን ኢትዮጵያዊ አስታወሰ – የቀድሞው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ኮ/ሎ ጎሹ ወልዴ!
“… ሆን ተብሎ በተቀነባበረ እቅድ ህወሃት አዲስ አበባን እንዲቆጣጠር የተወሰነው ውሳኔ አሳዛኝና ከቶውንም ሊታመን የማይችል ነው። የሰከረ ርዕዮት ዓለም የሚከተሉ፣ በብሄርና በጎሳ ፖለቲካ ላይ የተተከሉ ጠባብ ቡድኖች፣ በስታሊናዊ መርህ የተጠመቁ፣ እንኳንስ 50 ሚሊዮን ህዝብ ያላት አገር ቤተሰብን የመምራትና የማስተዳደር ተሞክሮ የሌላቸው፣ አገርን መምራትን የሚያክል ታላቅ ሃላፊነት ማሸከም ለኔ ከአእምሮ በላይ ነው …” ኮሎኔል ጎሹ ወልዴ የትንቢት ያህል፤ ሳግ እየተናነቃቸው የኢትዮጵያን ተላልፎ መሰጠት በዚሁ በሰኔ ወር ከ22ዓመት በፊት አስረግጠው በማስረጃና በማስጠንቀቂያ በመቃወመ፣ በማሳሰብ፣ እንደማይሆን በመምከር፣ አድሮ እንደሚያቃጥል በማስጠንቀቅ፣ ላቀረቡት ንግግር የክሪስ ስሚዝ ገለጻ በማረጋገጫነት የሚቆም እውነት ይሆናል።
አሜሪካ ራስዋ ቀብታና ባርካ በትረ ሹመት የሰጠቻቸውን ሰዎች ከ22ዓመት በኋላ መልሳ “ገምግሙልኝ” ማለቷ አስገራሚ የሚሆንባቸው ጥቂት አይደሉም። ሰብሳቢው በመግቢያቸው የተናገሩት የኢትዮጵያ መንግስት ወቅታዊ መገለጫ፣ ቀደም ሲል ሚ/ር ያማሞቶን በመጥቀስ ዊኪሊክስ ይፋ ያደረጋቸውን መረጃዎች ለተከታተሉ “አሜሪካኖቹ ምን የማያውቁት ነገር አለና ነው የሚጠይቁት ያሰኛል” በሚል የሚገረሙ በርካታዎች ናቸው።
ለዚህ ይመስላል የአዲሲቷ ኢትዮጵያ የጋራ ንቅናቄ ዋና ዳይሬክተር አቶ ኦባንግ ሜቶ ታሪካዊውን የኮሎኔል ጎሹ “ትንቢትና የኢትዮጵያ ህዝብን የሚወክል የምልጃ መቃተት” በማስታወስ ቀዳሚ የሆኑት። አስከትለውም “አሜሪካኖች ነጻ እንድታወጡን አንጠይቃችሁም። የኢትዮጵያ ህዝብ እንዴት ነጻ እንደሚወጣ ያውቃል። እናንተ ግን በነጻነት መንገዱን ላይ ዕንቅፋት አትሁኑበት። (ከመንገዱ ላይ ገለል በሉ)” የሚል መልክት አስተላለፉ።
የጋራ ንቅናቄው መሪ በድርጅታቸው መርህ ላይ ተመሥርተው በሰጡት የምስክርነት ቃል “ህወሓት እስካሁን በነጻአውጪ ስም አገር እየመራ እንደሆነ፤ መለስ ለህዝባቸው “ሬት” ለምዕራባውያንና “ማር” (የቤት ቀጋ፤ የውጭ አልጋ) ዓይነት መሪ እንደነበሩና የኢትዮጵያ ሕዝብ ላለፉት 22ዓመታት በመከራ ውስጥ ያለና የዛሬ 8ዓመት በዚሁ ቦታ ላይ ያማሞቶ ኢትዮጵያ በአቋራጭ መንገድ (ክሮስሮድ) ላይ እንደምትገኝ” መናገሩ አቶ ኦባንግ ካስታወሱ በኋላ “መቼ ነው መንገዱን የምናቋርጠው? ከስምንት ዓመት በኋላ አሁም አንሻገርም ወይ፤ አናቋርጠውም ወይ” በማለት ተሰብሳቢውን ያስደመመ ለሰብሳቢዎቹ ግልጽ ጥያቄ ጠይቀዋል፡፡
አቶ ኦባንግ ሲቀጥሉም “ኢትዮጵያውያን የምንጠይቀው በጣም ቀላል ጥያቄ ነው፤ አሜሪካኖች የሚመኩበትን ሰብዓዊ መብት እኛ ተነፍገናል፤ የራሳችን ክሪስ ስሚዝ ይኑሩን ብቻ ነው የምንለው” ካሉ በኋላ በኃይለሥላሴም ሆነ በመንግሥቱ ጊዜ ኢትዮጵያውያን ዕድላቸውን እንደተነፈጉ አስታውሰዋል፡፡ በወቅቱም በዚሁ ም/ቤት የዛሬ 22ዓመት በወርሃ ሰኔ ኮ/ሎ ጎሹ ወልዴ የዛሬዋን ኢትዮጵያን መተንበያቸውን አቶ ኦባንግ በንግግራቸው አስታውሰዋል፡፡ አሁንም የኢትዮጵያውያንን ቁርጠኛ አቋም ምን እንደሆነ ለአሜሪካውያኑ ግልጽ አድርገዋል “አሜሪካ እንድታድነን አይደለም የምንጠይቀው፤ ራሳችንን ማዳን እንችላለን፤ በነጻነት መንገዳችን ላይ ግን ዕንቅፋት አትሁኑብን፤ ራሳችንን ነጻ እናወጣለን፤ ኦባማ ለፕሬዚዳንትነት ሲወዳደር በርካታ ኢትዮጵያውያን ከሚያገኙት ጥቂት ደመወዝ ለምርጫው ዘመቻ ረድተው ነበር፤ ከኦባማ ግን የሰማነው ነገር እስካሁን ምንም የለም፤ ነጻነታችንን እየለመንን አይደለም፤ ራሳችንን ነጻ እናወጣለን” በማለት የበርካታ ኢትዮጵያውያንን የነጻነት መንፈስ የቀሰቀሰ ንግግር አድርገዋል፡፡
በመጨረሻም አሜሪካ ለኢትዮጵያ መንግሥት የዴሞክራሲ ለውጥ 300 ሚሊዮን ዶላር ዕርዳታ ሰጥቻለሁ እንደሚል ከጠቀሱ በኋላ “ይህ ሁሉ ገንዘብ የት ነው የገባው፤ የት ነው የሄደው” በማለት ኢህአዴግ ከቀበሌ ጀምሮ እስከላይ ሥልጣኑን እንደተቆጣጠረ፤ ሙስሊሙ መሪውን እንምረጥ ሲል አሸባሪ ተብሎ እንደሚፈረጅ ነገር ግን እኛ ኢትዮጵያውያን ከሙስሊም ወገኖቻችን ጋር አገርና መሬት ብቻ ሳይሆን የምንጋራው በደም የተሳሰርን መሆናችን አስረግጠው ተናግረዋል፡፡ አንድ ጊዜም እንኳን ጦርነት ሰብከውም ሆነ መሳሪያ አንስተው የማያውቁ መሆናቸውን የተናገሩት ኦባንግ፤ በኢትዮጵያ መንግሥት “አሸባሪ” መባላቸውን በመናገር የኢህአዴግን አሸባሪነት አጋልጠዋል፡፡ እስካሁን በአገራችን ላይ የፈሰሰው ደም በቂ እንደሆነ የጠቆሙት የጋራ ንቅናቄው መሪ፤ በኤድስና ምግብ በማጣት የረደሰብን ዕልቂት በቂ እንደሆነና ከእንግዲህ ወዲህ መጋደል እንደሌለብን ሆኖም ከኢህዴግም ሆነ ከተቃዋሚ በኩል አመኔታ የሚጣልባቸው ሰዎች ስላሉ እስካሁን ያልተሞከረውን የዕርቅ መንገድ (ሥራ) በኢትዮጵያ መከናወን እንዳለበት አቶ ኦባንግ ሜቶ በሚመሩት ድርጅት መርህና በሚታገሉለት የማዕዘን ሃሳብ ላይ ተተርሰው ሃሳባቸውን አጠቃልለዋል፡፡
በምክክር ሸንጎው ላይ የተገኙት የግንቦት 7 ሊቀመንበር ዶ/ር ብርሃኑ ነጋ በበኩላቸው የንግግራቸውና የማሳሰቢያቸው ማሳረጊያ ሊባል የሚችል መልዕክት አስተላልፈዋል። ዶ/ር ብርሃኑ “አስተውሉ፣ ልብ ብላችሁ ተገንዘቡ” በማለት ያሳሰቡት ዛሬ ኢትዮጵያን የሚወዱ ሁሉ የሚጠበቡበት፣ እንዲከሰት የማይፈልጉትን የመጨረሻው ስጋት ነው።
በምክሩ ላይ በቀዳሚነት ምልከታቸውን ያብራሩት ዶ/ር ብርሀኑ ኢህአዴግ የዘረጋው የአፈና ስርዓት ያስመረረው ህዝብ፣ ኢህአዴግ ሆን ብሎ የሚያንኮታኩታቸው የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ ሆን ብሎ የሚተናኮለው ህዝብ፣ ያለው ብቸኛ አማራጭ ብረት ማንሳት ብቻ እንደሆነ አመልክተዋል። በቅርቡ የኢህአዴግ የአፈና ስርዓት ፈተና እንደሚገጥመው ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ አለመረጋጋት ቀጣናውን በሙሉ እንደሚረብሽና የአሜሪካንን ጥቅም በእጅጉ እንደሚጎዳ ዶ/ር ብርሃኑ በግልጽ በማስረዳት አሜሪካ ገንዘቧን በተገቢው ቦታ ላይ ማዋል እንዳለባት ምክር ሰጥተዋል፡፡ በአሁኑ ጊዜ የተቃዋሚ ኃይሎች አማራጭ ከማጣት የተነሳ ብረት ማንሳታቸውን የጠቆሙት የግንቦት 7 ሊቀመንበር፤ ሕዝብ ዝም ብሎ በአስከፊ አገዛዝ ሥር እየኖረ እንደማይቀጥል አስጠንቅቀዋል፡፡ በመሆኑም አማራጭ ሲጠፋ ባገኘው መንገድ ሁሉ መብቱን ወደማስጠበቅ እንደሚገፋና በአሁኑ ወቅትም የተቃዋሚ ኃይሎች በመተባበር በኢህአዴግ ላይ ጥቃት መሰንዘር የሚስችላቸውን ብቃትና ኅብረት እንደፈጠሩ ጠቁመዋል፡፡ ይህ ሊሆን የቻለውም ኢህአዴግ በምንም መልኩ የማይሰማና በሰላማዊ መንገድ ሥልጣን ለማስረከብ የማይችል መሆኑን በተለይ በ1997 ምርጫ ካስታወቀ ወዲህ በግልጽ የሚከተለው መርህ በራሱ ማስረጃ እንደሆነ ዶ/ር ብርሃኑ በጥያቄ መልክ ለቀረበላቸው ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡
የኢህአዴግ የደምሥር የውጭ ዕርዳታ እንሆነ የተናገሩት የግንቦት 7 መሪ አሜሪካ ከአውሮጳውያን ጋር በመተባበርና ለእያንዳንዱ የተሃድሶ ዕርምጃ ቀነ ገደብ በመሥጠት በተሰጠው ገደብ ውስጥ እስረኞች ካልተፈቱ፤ የምርጫ ኮሚሽን ካልተቀየረ፤ ወዘተ በማለት ዕርዳታው እንደሚቆም በማስጠንቀቅ አሜሪካውያኑ ለኢህአዴግ መመሪያ ቢሰጡ ለገንዘብ ሲል ኢህአዴግ ሊታዘዝ እንደሚችል አስረድተዋል፡፡
በመጨረሻም በድጋሚ የሰብሳቢውን ስም በመጥራት ትኩረት የጠየቁት ዶ/ር ብርሃኑ “የሚታየኝ ጦርነት ነው፣ የርስ በርስ ግጭት ነው። የርስ በርስ ግጭት በኢትዮጵያ የመነሳቱ ጉዳይ ነው። አገሪቱ ላለፉት 21 ዓመታት በተጓዘችበት መንገድ አትቀጥልም። ይህን እንድትገነዘቡ እፈልጋለሁ” ብለዋል።
ከክሪስ አንደበት
ሰብሳቢው ክሪስ ስሚዝ በምክርቤት ስብሰባ ላይ ድምጽ መስጠት በሚገባቸው ረቂቅ ህጎች ላይ ሲሳተፉ ስለነበር ምክከሩ የጀመረው ከታቀደው ሰዓት 1፡30 ያህል ዘግይቶ በመሆኑ ይቅርታ በመጠየቅ ነበር መንበራቸው ላይ ተሰይመው ንግግር ጀመሩት። የምክክሩ ሊቀመንበር አቶ መለስ የዘረጉት አገዛዝ የሰብዓዊ መብት ረገጣ ልዩ ባህሪው እንደሆነ የተለያዩ ማስረጃዎችን በመጥቀስ ምክከሩን ከፈቱ። ምክክሩ በኢትዮጵያ ስላለው ወቅታዊ የሰብዓዊ መብቶችና የዴሞክራሲ ጉዳይ ላይ እንደሚያተኩርና የአሜሪካ መንግሥት ምን ማድረግ እንዳለበት የሚያመላከት ምክር የሚካሄድበት እንደሆነ አስገነዘቡ።
ኢትዮጵያ እስላማዊ አሸባሪነትን በቀጣናው በመዋጋት የአሜሪካ ደጋፊ አገር ሆና መቆየቷን፣ ሆኖም ግን በተመሳሳይ መልኩ የኢትዮጵያ መንግሥት ለሚፈጽመው ተደጋጋሚ የሰብዓዊ መብቶች ረገጣ የአሜሪካ መንግሥት የኢትዮጵያን መንግሥት ተጠያቂ ማድረግ እስካሁን አለመቻሉን ሳይሸሽጉ ተናገሩ።
የፖለቲካ ድርጅቶች በነጻነት መንቀሳቀስ አለመቻላቸውን፣ መንግስታዊ ባልሆኑ የግብረ ሰናይ ድርጅቶች (መያዶች) ላይ ጥብቅ ቁጥጥር እንደሚደረግ፣ ጋዘጠኞች እንደሚታሰሩ፣ በርካታ ዜጎች ከመሬታቸው እንደሚፈናቀሉ ወዘተ በመዘርዘር አስረዱ።
የአሜሪካ የዕርዳታ ድርጅት – ዩኤስኤይድ እንደሚለው ከሆነ ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር ግልጽ ግንኙነት ማድረግ ወደፊት የዴሞክራሲና የለውጥ ሂደቶችን ለማሳካት ይረዳል ተብሎ ቢታሰብም፣ በክሪስ ስሚዝ አመለካከት ግን እምነቱ ሊተገበር የሚችል ቢመስልም እስካሁን ምንም ፍሬ እንዳላመጣ ሳይሸሽጉ ተናግረዋል።
እንደ አምነስቲ ኢንተርናሽናል መረጃ መሠረት በኢትዮጵያ እየተካሄደ ያለው ስልታዊ አፈናና የሰብዓዊ መብቶች ረገጣ ለሌሎች አገራት መጥፎ ምሳሌ እየሆነ መሄዱን ሊቀመንበር ስሚዝ ጠቅሰዋል፡፡ ንጹሃን ዜጎች ስቃይ፣ ድብደባ እንደሚደርስባቸው፣ በኤሌክትሪክ እንደሚጠበሱና የግዳጅ ወሲብ እንደሚፈጸምባቸው፣ የአምነስቲ ሪፖርት መዘገቡን ክሪስ ስሚዝ በእማኝነት ተናግረዋል፡፡
ራሳቸው ክሪስ ስሚዝ በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ ረቂቅ ህግ አዘጋጅተው እንደነበርና በወቅቱ የነበረው የጆርጅ ቡሽ አስተዳደር ግን ኢትዮጵያን በአሸባሪነት ላይ ወዳጅ በማድረጉ ምክንያት በነበረው ቸልተኝነት የተነሳ ተፈጻሚ ሳይሆን መቅረቱን አስታውቀዋል። ሚ/ር ስሚዝ እነዚህን ጉልህ ህጸጾች በመጠቆም ምክክሩ ላይ ተናጋሪ እንዲሆኑ የተጋበዙትን ክፍሎች በየተራ በማስተዋወቅ ጋብዘዋል። ከንግግሩ በኋላም ጥያቄዎችን ጠይቀዋል። ሌሎች ተሳታፊዎችም ጥያቄ በመሰንዘር ማብራሪያ እንዲወስዱ ተደርጓል።
ያማማቶ ምን አሉ?
ያማሞቶ በመግቢያ ንግግራቸው መለስን አወድሰዋል። አፍሪካን በዓለም መድረክ ከፍ እንድትል ያደረጉ መሪ በማለት አመስግነው ኢትዮጵያ ተሰሚነቷ እንዲጨምር ያደረጉ፣ ተሟጋችና ጎበዝ ተናጋሪ እንደነበሩ መስክረዋል። ኢኮኖሚውን አሳድገዋል፣ ኢትዮጵያን በቀጣናውና በዓለም ታዋቂ አድርገዋል፣ በሶማሊያ ተሟጋች፣ በሱዳን አስታራቂ፣ በአፍሪካ የአየርንብረት ጉዳይ ደግሞ አንደበተ ርዕቱ አፈቀላጤ ነበሩ በማለት የኢትዮጵያ ቴሌቪዥንና ሬዲዮ ድርጅት ከሚደረድረው በላይ ቃል አከማችተው ምስጋና ቸረዋቸዋል።
ያማማቶ በማያያዝ እንደ አምባሳደርነታቸው በኢትዮጵያ ያለውን የፖለቲካ ምህዳር መጥበብ አስመልክቶ አቶ መለስን ማነጋገራቸውን ጠቁመዋል። በሰብዓዊ መብቱን መጓደል ዙሪያም በተመሳሳይ መነጋገራቸውን አክለዋል።
ካሊፎርኒያ ሎሳንጅለስ “ትንሿ ኢትዮጵያ” ወረዳ ተወካይ የምክርቤት አባል ሚስዝ ባስ፤ ያማሞቶን መስቀለኛ ጥያቄ አቅርበውላቸው ነበር። ጠያቂዋ “የኢህአዴግ መንግሥት ዋናው ችግር ምንድነው? ለምንድነው ይህንን ሁሉ መከራና አፈና የሚያካሂደው” በማለት የመገረም የሚመስል ጥያቄ ጠይቀዋል። ያማሞቶ እንደ መንተባተብ ሲሉ “ችግሩ ምንድ ነው?” በማለት ባስ በድጋሚ ጥያቄያቸውን ወረወሩ። “ችግሩ እንዳለ ነው” ሲሉ ደግመው መልስ የሰጡት ያማሞቶ “ጠቅላይ ሚ/ር ሃይለማርያም አፍሪካ ኅብረት ስብሰባ ላይ እንዳሉት ነው፣ የዴሞክራሲ እሴቶች አስፈላጊ ናቸው፣ መጥፎ ህጎች መወገድ አለባቸው፣ እንስራ፣ እንሞክር ብለዋል” አሉና መለሱ።
ኮንግሬስማን ሜዶውስ በኢትዮጵያ ኢህአዴግ ሁሉን ተቆጣጥሮዋል፤ እኛ አሜሪካኖች ምን ልናደርግ እንችላለን? እንዴት ነው ልናስተካክለው የምንችለው? የሚል ጥያቄ ለያማሞቶ ወረወሩ። ያማሞቶም “ከምርጫው በኋላ ደስተኞች አለመሆናችንን ተናግረናል፡፡ ከበስተጀርባና በፊትለፊት እየሰራን ያለነው ነገር አለ፡፡ ጊዜ የሚወስድ ነው፡፡ ለምሳሌ በሴቶች ላይ የሚደረግ የመብት ጉዳይ አለ እናም ይህንን ከዩስኤድ ጋር እየሰራን ነው” አሉ፡፡
ሜዶውስ የረኩ አይመስልም “እና ያለው ፍርሃት ምንድርነው?” ሲሉ በድጋሚ መልስ መፈለጋቸውን አመለከቱ። “ነግረናቸዋል ፣ ለዘላለም ልትገዙ አትችሉም። ስለዚህ የተቃዋሚውን ተሳትፎ ማበረታታት አለባችሁ ። እነዚህ ተቃዋሚዎች አንድ ቀን መንግሥት ይሆናሉ። ስለዚህ ዝግጅት መደረግ አለበት ብለናቸዋል” የሚል የደፈና መልስ ከያማሞቶ ተሰጠ።
ጋንት፤ የዩኤስ ኤይድ ረዳት ዳይሬክተር
የሴፍቲኔት ፕሮግራም እየተካሄደ መሆኑንና በአሁኑ ሰዓት ኢትዮጵያ እየተረጋጋች እንደሆነ፣ ከዚህም ጋር በማከል ኢኮኖሚው እያደገ እንደሆነ ልክ የኢህአዴግ ወኪል መስለው ተናገሩ። ሰብሳቢው ስሚዝ “ቶርቸር በየቦታው አለ እና ይህንን እንዴት ነው ለማስታረቅ ወይም ለማቆም የሚቻለው?” ሲሉ ማብራሪያ ጠየቁ። ሚ/ር ጋንት “አስቸጋሪ ነገር ነው። ቶርቸር እንዳለ እናውቃለን ግን ዋናው ሥራችን መልካም ነገሮችን ለማበረታታት ነው የምንሞክረው” የሚል ምላሽ ሰጡ።
በሚ/ር ጋንት ንግግር ላይ ተንተርሰው ተጨማሪ ጥያቄ ያቀረቡት ክሪስ ስሚዝ፣ ኢትዮጵያ ትምህርትን አስመልክቶ የሚሊኒየም ጎል ተሳክቷል ማለታቸውን ጠቅሰው “ጋንት ግን እኮ ጥራቱ በጣም የዘቀጠ እንደሆነ ነው ሪፖርቱ የሚያሳየው” ሲሉ ሞገቱዋቸው። የዩኤስ አይዲው ዳይሬክተር ጋንት “አዎ ችግር አለ ግን በርካታ መምህራን ተሰማርተዋል በትምህርቱ በኩል ዕድገት አለ” የሚል መልስ መመለሳቸው ለግንዛቤ ያህል የሚጠቀስ ሆኖ አግኝተነዋል።
ያማሞቶና ጋንት ያቀረቡትን ንግግርና ምስጋና ያደመጡ፣ በአካል ተገኝተው የተከታቱተሉ እንዳሉት በምክክሩ ላይ ኢህአዴግ ቢገኝም የሚጨምረው ምንም ነገር ሊኖር እንደማይችል አመልክተዋል።
ዳግም HR2003
የዛሬ አስር ዓመት፤ ኤች አር 2003 በምክር ቤት ደረጃ ከፍተኛ የሸንጎ (ኮንግሬስ) አባላትን ድጋፍ ካገኘ በኋላ የሕግ መወሰኛ ም/ቤት (ሴኔት) አጽድቆት በፕሬዚዳንቱ ተፈርሞ ፖሊሲ ሆኖ እንዲጸድቅ ባለመደረጉ ተቋማዊና አስተዳደራዊ ለውጥ ሊያመጡ የሚችሉ ጉዳዮች መከኑ። የህጉ መርቀቅና እንዲጸድቅ የተጀመረው እንቅስቃሴ ያስበረገገው ኢህአዴግ ጡረተኛ የሴኔት አባላት ከሚመሩት ዲኤልኤ ፓይፐር ከተባለ የጎትጓች (ሎቢ) ቡድን ጋር ከፍተኛ በጀት በጅቶ ታገለ። ባፈሰሰላቸው መጠን ጎትጓቾቹ ባልደረቦቻቸውን ጠመዘዙና ህጉ አሜሪካ በኢትዮጵያ ላይ የምትከተለው አዲስ የዴሞክራሲና የሰብዓዊ መብት ህግ እንዳይሆን ተደረገ። ይህንኑ ህግ በማዘጋጀት ከሟቹ የምክርቤት አባል ዶናልድ ፔይን ጋር በወቅቱ ብዙ ደከሙት ክሪስ ስሚዝ የወቅቱን የቡሽ አስተዳደርን በንዝላልነት መድበው አሁን ይሀንኑ ህግ ተግባራዊ የሚደረግበትን አግባብ እንደሚገፉበት አመልክተዋል።
እንዴት እዚህ ተደረሰ?
የኢህአዴግን የአገዛዝ ዘመን ተቃዋሚዎችን አጃቢ አድረጎ የህግ ሽፋን በመስጠት የሚያራዝመው ዋና ተቋም ምርጫ ቦርድ፣ የፕሬስ ነጻነት፣ የመናገርና የመሰብሰብ ነጻነት፣ የህግ የበላይነት፣ ሕግን የማክበርና የማስከበር ሃላፊነት፤ ወዘተ በኢትዮጵያ ነጻ ከሆኑ ኢህአዴግ ከፊትለፊቱ ካለው ምርጫ የመዝለል አቅም እንደሌለው ይታመናል። ስለዚህም ለድርድር አያቀርባቸውም።
ኢህአዴግ ከጅምሩ በህዝብ የማይታመነውና እውቅና የሚነፈገው ራሱን በነጻ አውጪ (ህወሓት) የሰየመ መንግስት ስለሆነ ነው። ነጻ አውጪ እየተባለ አገር መምራቱ አቅዶ፤ ተልሞና መድረሻውን አስልቶ የሚጓዝ ስለመሆኑ ያሳብቅበታል። ለዚህም ይመስላል ስርዓቱ በሙስና የሸተተ፣ በግፍ የገለማ፣ የሚመራውን ህዝብ የሚገል፣ የሚያስር፣ የሚያሰቃ፣ መንግስት ሆኖ የሚሰርቅ፣ ብሔራዊ ክብርን የሚጠላ፣ ህብረትንና አንድነትን የሚጠየፍ፣ ጎሳና ጠባብ አመለካከት ላይ የተቀረጸ፣ በተራና በወረደ ተግባሩ ለመንግስትነት የማይመጥን መሆኑን የተረዱት አጋሮቹ አሁን ያመረሩበት ደረጃ ስለመዳረሳቸው ምልክቶች እንዳሉ አቶ ኦባንግ ሜቶ ለጎልጉል ተናግረዋል።
ይህ የምክክር ሸንጎ እንዴት ሊዘጋጅ ቻለ ለሚለው ጥያቄ በርካታ ጥረቶች መካሄዳቸውን በመግለጽ ዝርዝር ያላቀረቡት አቶ ኦባንግ ሐሙስ በተካሄደው ምክክር በመካከል ላይ ሚ/ር ስሚዝና ሌሎቹ ተወካዮች በምክርቤት ድምጽ መስጠት ስለነበረባቸው ምክክሩ ተቋርጦ እንደገና ሲጀመር ያልታዩበትን ምክንያት ተናግረዋል። ምክክሩ በተባለው ሰዓት ተጀምሮ ያልቃል የሚል እምነት ስለነበራቸው ሌላ ተደራራቢ የጉዞ መርሃግብር አመቻችተው እንደነበር አመልክተዋል።
“አሁን ስራ ላይ ነኝ” ያሉት አቶ ኦባንግ “እስራኤል አገር ለሁለት ከፍተኛ ጉዳዮች መጓዝ ነበረብኝ። አንዱ የወገኖቻችን ጉዳይ ነው። ሌላኛው ደግሞ የአገራችን ጉዳይ ነው። ከጉዞዬ በኋላ ማብራሪያ ለመስጠት እችላለሁ” በማለት ሁለተኛው ስብሰባ ሲካሄድ እርሳቸው ወደ እስራኤል ለሥራ እየተጓዙ እንደነበር አስታውቀዋል።
ምንጭ ጎልጉል (http://www.goolgule.com/)
No comments:
Post a Comment