Thursday, April 25, 2013

በቤቶች ጉዳይ አቶ ሀይለማርያም የሰጡት መልስ የፓርላማ አባላቱን አስቆጣ

ሚያዚያ ፲፯ (አስራ ሰባት) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-ጠ/ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ትላንት የመንግስታቸውን የ2005 በጀት ዓመት የስምንት ወራት ሪፖርት ባቀረቡበት ወቅት ...ከፓርላማ አባላት ከቀረቡላቸው ጥያቄዎች መካከል የ40 በ 60 የተባለው የቤቶች ልማት ፕሮጀክትን አስመልክቶ የሰጡት ምላሽ ባልተለመደ መልክ የኢህአዴግ የፓርላማ አባላትን ጉምጉምታ አስከተለ፡፡

40 በ 60 የሚባለው የቤት ልማት ፕሮግራም ሕዝቡ በአንድ በኩል ቆጥቦ የቤት ባለቤት እንደሚሆን እየተነገረ በሌላ በኩል መቶ በመቶ የመክፈል አቅም ላላቸው ሰዎች ቅድሚያ ይሰጣል የመባሉን ጉዳይ ተጠይቀው በሰጡት ምላሽ መቶ በመቶ ለሚከፍሉ ቅድሚያ እንደሚሰጥ ማረጋገጣቸው የፓርላማ አባላቱን ጉምጉምታ አስከትሏል፡፡

 መንግስት 20 በ80 በሚባለው የኮንዶምኒየም ቤቶች የልማት ፕሮግራሙ ባለፉት ስምንት ዓመታት ጊዜያት ውስጥ ከ350 ሺ በላይ ቤት ፈላጊ በተመዘገበበት በአዲስአበባ ከተማ ብቻ 100ሺ ያህል ቤቶችን መገንባቱን አስታውሰዋል፡፡ የቤት ፍላጎቱን ለማርካት ተጨማሪ 40 በ60 በሚባል ፕሮግራም መካከለኛ ገቢ ያላቸውን የህብረተሰብ ክፍሎች ለመድረስ፣10 በ90 በሚባለው ፕሮግራም ደግሞ ዝቅተኛ ገቢ ያላቸውን የህብረተሰብ ክፍሎች የቤት ባለቤት ለማድረግ መታቀዱንና በ10 በ90 ፕሮግራም 35 ሺ ፣በ40 በ60 ወደ 10ሺ ያህል ቤቶች በአዲስአበባ ግንባታቸው መጀመሩንና በቅርቡም የቤት ፈላጊዎች ምዝገባ እንደሚካሄድ ጠቅሰዋል፡፡

 አቶ ኃ/ማርያም አያይዘውም 40 በ60 የሚባለው ፕሮግራም መካከለኛ ገቢ ያላቸውን የህብረተሰብ ክፍሎች የሚመለከት በመሆኑ መቶ በመቶ ክፍያ ለሚፈጽሙ ቅድሚያ እንደሚሰጥ ማረጋገጫ መስጠታቸው በኢህአዴግ አባላት የተሞላውን ፓርላማ
ጉምጉምታ አስነስቷል።

ለፓርላማ ቅርበት ያላቸው ምንጮች አባላቱ ያልጎመጎሙበትን ምክንያት ተጠይቀው በሰጡት ምላሽ ቀደም ሲልም ፕሮግራሙን በተመለከተ ለፓርላማው ሪፖርት በቀረበበት ወቅት 40 በ60 የሚባለው ፕሮግራም መካከለኛ ገቢ ያለውን በተለይም በወርሃዊ ደመወዝ የሚተዳደረውን የህብረተሰብ ክፍል ይጠቅማል መባሉንና ነገርግን ለባለአንድ ክፍል መኝታ
ቤት 857 ብር፣ለባለሁለት መኝታ ቤት 1 ሺ 337 ብር፣ ለባለሶስት ምኝታ ቤት ደግሞ 2 ሺ133 ብር ለአምስት ተከታታይ ዓመታት በየወሩ መቆጠብ እንዳለበት መታቀዱ የመካከኛ ገቢ ያለውን የህብረተሰብ ክፍል አቅም ያገናዘበ አይደለም የሚል ቅሬታ በአባላቱ
ዘንድ በቅሬታ መልክ ተደጋግሞ ይነሳ እንደነበረ አስታውሰዋል፡፡

በኢትዮጵያ ተጨባጭ ሁኔታ መካከለኛ ገቢ አለው የሚባለው በተለይም የመንግስት ሰራተኞች አማካይ ወርሃዊ መካከለኛ ገቢ ከ2 ሺ 500 ብር እንደማይበልጥ ምንጫችን ጠቅሶ ከዚህ ደመወዝ ላይ ዝቅተኛውን በወር 857 ብር መቆጠብ እንዴት ይቻላል ሲል ይጠይቃል፡፡ በዚህ ምክንያት የ40 በ60 የቤት ልማት ፕሮግራም ከፍተኛ ገቢ ያላቸው የህብረተሰብ ክፍሎች የሚጠቅም ነው የሚል ድምዳሜ መኖሩን ምንጫችን አስታውሶ የአቶ ኃይለማርያም ምላሽ ይህን በግልጽ ማረጋገጡ የፓርላማ አባላቱን እንዲያልጎመጉሙ ምክንያት ሆኗል ብሏል፡፡
የ40 በ60 ዓይነት የቤት ልማት ፕሮግራሞች ዓይነተኛ ዓላማ ቁጠባን ማበረታታት ነበር ያለው ምንጫችን አፈጻጸሙ ግን በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ቤት ፈላጊዎች ተመዝግበው እንዲቆጥቡ የሚያበረታታ አልሆነም ሲል ያስረዳል፡፡
በተያያዘ ዜና ጠ/ሚ ኃይለማርያም የዋጋ ንረቱ ወደ 7 ነጥብ 6 በመቶ ወርዶአል፣እየተረጋጋ ነው ያሉት ግን በተግባር ያልተቀረፈውን የኑሮ ውድነት ችግር ለመቅረፍ ከውጪ አገር ሸቀጦችን ገዝቶ በተመጣጣኝ ዋጋ የሚያከፋፍል መንግስታዊ የሆነ ግዙፍ ኢንተርፕራይዝ በመቋቋም ላይ መሆኑን ፍንጭ ሰጥተዋል፡፡
ምንጮቻንን ስለጉዳዩ እንደገለጹት በጠቅላይ ሚኒስትር ቢሮ አማካይነት በተደረገው ጥናት ለውጪ ኩባንያዎች ዝግ የሆነውን የሸቀጦች ችርቻሮ ንግድ ስራ ለመፍቀድ ወይ ሌሎች አማራጮችን ለማየት መሞከሩን ጠቅሶአል፡፡ ነገር ግን ትልልቆቹ ኩባንያዎች በሸቀጦች የችርቻሮ ንግድ እንዲሰማሩ ቢደረግ የአገር ውስጥ አስመጪዎች በአጭር ጊዜያት ውስጥ
ከገበያ ውጪ በማድረግ መንግስት ሊቆጣጠረው የማይችለው ገበያ ሊፈጠር ይችላል የሚል ግምት በመወሰዱ በመንግስት ቁጥጥር ስር ሆኖ ዋጋ የማረጋጋትና አነስተኛ ዋጋ ካላቸው ገበያዎች ሸቀጦችን በመግዛት በተመጣጣኝ ዋጋ የሚያቀርብ ኢንተርፕራይዝ እንዲቋቋም ውሳኔ ላይ ተደርሶአል፡፡

ይህም ሆኖ ግን መንግስት በገበያ ውስጥ ያለውን ድርሻ እየቀነሰ ከመምጣት ይልቅ በየሰበብ አስባቡ የግሉን ዘርፍ ስራዎች ሁሉ ተክቶ ለመስራት የሚያደርገው ጥረት እምብዛም ውጤት እንደማያመጣ ባለፉት ዓመታት በተመሳሳይ ስራ ላይ የቆዩትንና የሙስኞች መቀፍቀፊያ የሆኑትን የሸቀጦች ጅምላ ንግድና አስመጪ ድርጅት (ጅንአድ) እና የእህል ንግድ
ድርጅትን በምሳሌነት የጠቀሱ አስተያየት ሰጪዎች የመንግስትን ዕቅድ አጣጥለውታል፡፡

አስተያየት ሰጪዎች አያይዘውም መንግስት የዋጋ ንረትን የሚያባብሱት የግብርና ምርቶች መሆናቸው እየታወቀ ከውጪ የሚገቡ የፋብሪካ ምርቶች ናቸው በሚል በጠ/ሚኒስትሩ የቀረበው ሪፖርት ተጨባጭነት የጎደለው ነው ሲሉ ነቅፈውታል፡፡

ከግብርና ምርቶች መካከል አብዛኛው ሕዝብ የዕለት ምግብ የሆነው የጤፍ ምርት በአሁኑ ሰዓትም የመረጋጋት ሳይሆን የመጨመር አዝማሚያ እያሳየ መጥቶ አንድ ኩንታል ጤፍ ከ 2,000 ብር በላይ የሚጠየቅበት የሐብታሞች ምግብ ብቻ ወደመሆን መሸጋገሩን በተመለከተ በሪፖርታቸው ሳይጠቀስ መታለፉ አሳዛኝ ነው ብለውታል፡፡

አቶ ኃይለማርያም ከተሾሙ በኋላ የመጀመሪያቸው በሆነው የፓርላማ የከዚህ በፊት ውሎ ላይ የጤፍ ዋጋን መወደድ አስመልክቶ ሕብረተሰቡ የጤፍ ምርትን ከተለያዩ ሰብሎች ጋር በመደባለቅ መጠቀም ቢለምድ ዋጋው ሊረጋጋ እንደሚችል አስተያየት መስጠታቸውን ተከትሎ ለከፋ ትችት ተጋልጠው ከርመዋል፡፡ጠ/ሚኒስትሩን ለትችት የዳረጋቸው ከጥንት ጀምሮ በገጠር አካባቢዎች ሳይቀር በተለምዶ ጤፍን ከማሽላ፣ጤፍን ከበቆሎና ከመሳሰሉ እህሎች ጋር በመደባለቅ መመገብ ለኢትዮጽያዊያን አዲስ ባህል አለመሆኑ እንደነበርም ይታወሳል፡፡

No comments:

Post a Comment