Saturday, April 27, 2013

አርቲስት ጀማነሽ ሰለሞን ታሰረች


አርቲስት ጀማነሽ ሰለሞን ታሰረች
“የፍርድ ሂደቱ ሲጠናቀቅ ጋዜጣዊ መግለጫ እንሠጣለን” - ከጀማነሽ ጋር የታሰሩ አባት
በተለያዩ የመድረክ ቴያትሮች፣ በቴሌቪዥንና በሬዲዮ ድራማዎች በተለይም “ገመና” በተሰኘው ተከታታይ የቴሌቪዥን ድራማ የእናትነት ገፀ - ባህሪን ተላብሳ በመተወን የምትታወቀው አርቲስት ጀማነሽ ሰለሞን ታሰረች፡፡ አርቲስቷ ማክሰኞ ማታ ተይዛ አራት ኪሎ የሚገኝ ፖሊስ ጣቢያ ከታሰረች በኋላ ረቡዕ አመሻሽ ላይ ወደ ጉለሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ ዘጠኝ መዛወሯንና ከእርሷ ጋር ሌላ አንዲት ሴትና ሁለት ወንዶች መታሰራቸውን በስፍራው ተገኝተን አረጋግጠናል፡፡ አርቲስት ጀማነሽና አብረዋት የታሰሩት ግለሰቦች ሃሙስ እለት አፍንጮ በር መንገድ አዲስ አበባ ሬስቶራንት አካባቢ በሚገኝ የመጀመሪያ ደረጀ ፍርድ ቤት ቀርበው ጉዳያቸው የታየ ሲሆን የፊታችን በድጋሚ ፍርድ ቤት ይቀርባሉ፡፡
 
አርቲስቷንና አብረዋት የታሰሩትን ሰዎች ለመጠየቅ ወደ ስፍራው ከመጡ ግለሰቦች ለመረዳት እንደቻልነው፤ አርቲስቷና አብረዋት ያሉት ሰዎች የታሰሩት “ማህበረ ስላሴ ዘ ደቂቀ ኤልያስ” ከተባለው ማህበራቸውና ከሀይማኖት ጉዳይ ጋር በተያያዘ እንደሆነ ጠቁመው ዝርዝር መረጃ ከመስጠት ተቆጥበዋል፡፡ ከአርቲስቷ ጋር የታሰሩት አንድ የሃይማኖት አባት፤ ጉዳዩ በፍርድ ቤት የተያዘ በመሆኑ ከፍርድ ሂደቱ በኋላ ጋዜጣዊ መግለጫ እንደሚሰጡ፣ አሁን ምንም አይነት ዝርዝር መረጃ ለመስጠት ፈቃደኛ እንዳልሆኑ ነግረውናል፡፡ አርቲስት ጀማነሽን ሊጠይቋት የመጡ ሰዎችን ለማነጋገር ስትወጣ በተመለከትናት ጊዜ በፈገግታ የታጀበች ሲሆን ጠያቂዎቿ “እንዴት ነሽ ተመቸሽ?” ብለው ሲጠይቋት “እግዚአብሔር ያለበት ቦታ ሁሉ ምቹ ነው” ስትል ምላሽ ሰጥታለች፡፡ አርቲስቷ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ “ተዋህዶ” በሚል ሃይማኖት ውስጥ ተሣታፊ በመሆን አነጋጋሪ ሆና መቆየቷ የሚታወስ ነው፡፡
 
ወረዳ ዘጠኝ ፖሊስ ጣቢያ በተገኘን ጊዜ የሃይማኖቱ ተከታዮች የሚለብሱት የቀስተደመና ቀለማት ያሉት ነጠላ አጣፍታ፣ ፀጉሯንም የቀስተ ደመና ቀለም ዙሪያውን ባቀለመው ሻሽ አስራለች፡፡ ማህበረ ስላሴ ዘ ደቂቀ ኤልያስ “የኢትዮጵያን ትንሣኤ ሊያረጋግጥ ሃያል ባለስልጣን ነብዩ ኤልያስ ከብሔረ ህያዋን ጳጉሜ 1/2003 ዓ.ም ወደ ምድር መጥቶ በመካከላችን ይገኛል፣ ኦርቶዶክስ የሚባለው የሃይማኖት ስም ስህተት ነው ተዋህዶ ነው መባል ያለበት፣ ሰንበት ቅዳሜ ብቻ ነው፣ መለበስ ያለበት እግዚአብሔር ለኖህ ቃል ኪዳን የገባበትን ቀስተ ደመና ቀለማት ያካተተ ጥለት ያላቸው ነጭ አልባሳት ናቸው” የሚሉትን የተለያዩ ጉባኤዎችን እያዘጋጀ የሚያስተምር ማህበር መሆኑን ያነጋገርናቸው የማህበሩ አባላት ገልፀውልናል፡፡
 
 በተለያዩ ገዳማትም የሀይማኖቱ አራማጆች እንደሚገኙና እንደሚያስተምሩ ያገኘናቸው የሃይማኖቱ ተከታዮች ነግረውናል፡፡ በጉዳዩ ዙሪያ ከፖሊስ መረጃ ለማግኘት ጥረት ብናደርግም፣ ከመምሪያው የተፃፈ ፈቃድ ያስፈልጋል በሚል የወረዳው ፖሊስ መረጃ ከመስጠት ተቆጥቧል፡፡
 

No comments:

Post a Comment