ኢሳት ዜና:-በአፍሪካ ውስጥ ካሉ ሶስት የፈንጅ አምካኝ ድርጅቶች መካከል በአገልግሎት ዘመኑም ሆነ በተግባሩ በግንባር ቀደምነት ስሙ የሚጠቀሰው የኢትዮጵያ ፈንጅ አምካኝ ድርጅት ምክንያቱ ባልታወቀ ሁኔታ እንደፈርስ መደረጉን ተከትሎ፣ ከተለያዩ የውጭ አገራት በእርዳታ ከተሰጠው በመቶ... ሚሊዮኖች ከሚቆጠር ገንዘብ በተጨማሪ፣ ቋሚና ተንቀሳቃሽ ንብረቶቹ በወታደራዊ መኮንኖች እንዲዘረፍ መደረጉን የውስጥ ምንጮች ገለጹ።
አብዛኞቹ የድርጅቱ ከባድ መኪናዎች እና ሌሎች ንብረቶች በወታደራዊ አዛዦች መወሰዳቸውን የገለጡት ምንጮች ጉዳዩ ያሳሳበው የጸረ ሙስና ኮሚሽን ምርመራ ቢጀምርም ምክንያቱ ባልታወቀ ሁኔታ ምርመራውን አቋርጣል።
ከ100 እስከ 150 ሚሊዮን የሚጠጋ ገንዘብ መዘረፉን የገለጡት ምንጮች፣ ከዝርፊያው ጋር እጃቸው አለበት የተባሉት መኮንኖች በዘረፉት ገንዘብ ከፍተኛ ህንጻዎችን እያስገነቡበት መሆናቸውን ተናግረዋል።
በአንድ የመምሪያ ሀላፊነት ቦታ ላይ የነበሩ ሰው ድርጅቱ ከአውሮፓ እና ከአሜሪካ መንግስት ከፍተኛ የገንዘብ ድጋፍ እየተደረገለት በጥሩ ሁኔታ ሲሰራ ከቆየ በሁዋላ፣ በድንገት የተወሰኑ ወታደራዊ አዛዦች በድንገት ተመካክረውና በቂ ጥናት ሳይደረግበት ከ7 መቶ በላይ ሰራተኞችን በማባረር እንዲፈርስ አድርገውታል ብለዋል። ወታደራዊ አዛዦቹ የተወሰኑ ቁሳቁሶችን ለፌደራል ፖሊስ ያስረከቡ ቢሆንም፣ አብዛኛውን ንብረት ያለጠያቂ በመከፋፈል መውሰዳቸውን እኝሁ ባለስልጣን ገልጸዋል።
ከ3 ወራት በፊት ሰላማዊ ሰልፍ አድርገው የነበሩት የድርጅቱ ሰራተኞች ሰሚ አጥተው ለከፍተኛ ችግር መዳረጋቸውንም እኝህ ባለስልጣን ገልጸዋል።
ድርጊቱ በህወሀት ታማኝ ጀኔራሎች መካከል የጥቅም አለመግባባት ፈጥሮ እንደነበርም ታውቋል።
በኦሮሚያ ክልል ፍቼ ከተማ የነበረው ጽህፈት ቤት ፈርሶ በአሁኑ ጊዜ ሌላ ጽህፈት ቤት መቀሌ ውስጥ እንዲከፈት መደረጉንም እኝሁ ባለስልጣን ገልጸዋል።
በጉዳዩ ዙሪያ የመንግስት ባለስልጣናትን ለማነጋገር ያደረግነው ሙከራ አልተሳካም።
በኢትዮጵያ ውስጥ ከላይ እስከታች የሚገኙ ባለስልጣናት የሚፈጽሙት ሙስና በአገሪቱ ውስጥ የሚታየውን የኑሮ ውድነት ከማባባስ በተጨማሪ በህብረተሰቡ ውስጥ ያለው የኑሮ ልዩነት እንዲሰፋ እያደረገው ነው።
ለገዢው ፓርቲ ቅርብ የሆኑ ሰዎች በአንድ ጀምበር ሚሊየነር የሚሆኑበት አሰራር በመጨረሻ አገሪቱን እንደሚጎዳ ብዙዎች አስተያየት ይሰጣሉ።
ፋይናንሻል ኢንተግሪቲ የተባለው ተቋም ባለፉት ስምንት አመታት ከኢትዮጵያ ከ 180 ቢሊዮን ብር በላይ ተዘርፎ በውጭ አገራት ባንኮች መከማቸቱን ይፋ ማድረጉ ይታወሳል። በሌላ በኩል ግን አገሪቱ ከቻይናና ከህንድ የተበደረችውን ገንዘብ ሳይጨምር 150 በሊዮን ብር የሚጠጋ ገንዘብ የውጭ እዳ አለባት።
ከፍተኛ ወታደራዊ መኮንኖች እና የመንግስት ባለስልጣናት በአዲስ አበባ እና በተለያዩ የአገሪቱ ከተሞች የሚገነቡዋቸውን አንዳንድ ህንጻዎች በፎቶ ግራፍ በማስደገፍ ማቅረባችን ይታወሳል።
ኢህአዴግ በ9ኛው ጉባኤ ሙስናን ለመዋጋት ቃል መግባቱ ይታወሳል።See More
No comments:
Post a Comment