Monday, March 18, 2013

የግራዚያኒን ሀውልት ግንባታ በመቃወም ታሰረው የተፈቱ ዜጎች ዘራቸው እየተጠቀሰ መሰደባቸው ታወቀ

መጋቢት ፱ (ዘጠኝ) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-የፋሽስት ኢጣሊያ መንግስት ወኪል በመሆን በአንድ ቀን ከ30 ሺ በላይ ኢትዮጵያውያንን በስድስት ኪሎ አደባባይ የጨፈጨፈውን የሮዶልፎ ግራዚያኒን ሀውልት ለማቆም እየተደረገ ያለውን እንቅስቃሴ ለመቃወም ትናንት እሁድ በስድስት ኪሎ የተሰባሰቡ የባለራእይ ወጣቶች ማህበር አባላት፣ የሰማያዊ ፓርቲ አባላትና አገር ወዳድ ኢትዮጵያውያን እንዲታሰሩ ተደርጓል።
የጸጥታ ሀይሎች ታዋቂውን የህግ ባለሙያና ፖለቲከኛ ዶ/ር ያእቆብ ሀይለማርያምን ጨምሮ የሰማያዊ ፓርቲ ሊቀመንበር ኢ/ር ይልቃል ጌትነትን ለአንድ ቀን ካሰሩዋቸው በሁዋላ በመታወቂያ ዋስ ለቀዋቸዋል። ከእስረኞች መካከል አንዳንዶቹ ብሄር ተብለው ሲጠየቁ ኢትዮጵያውዊ በማለት የመለሱ ዘራቸው ሳይቀር እንደተሰደበ ታውቋል። በርካታ ወጣቶች የኢሜል እና የፌስ ቡክ የሚስጢር ቁልፋቸውን ( ፓስወርድ) እንዲሰጡ መጠየቃቸውንም ለማወቅ ተችሎአል።
በጉዳዩ ዙሪያ አስተያየታቸውን የሰጡት ለአንድ ቀን ታስረው የተፈቱት ዶ/ር ያእቆብ ፣ እርሳቸውና ሌሎች ሰዎች የታሰሩት ሰላማዊ ሰልፍ ለማድረግ ፈቃድ አልተጠየቀም በሚል ምክንያት መሆኑን ተናግረዋል። ።
ዶ/ር ያእቆብ የጸጥታ ሀይሎች የወሰዱት እርምጃ መንግስት ለግራዚያኒ እንደቆመ ያስቆጥርበታል ብለዋል።
የባለራእይ ወጣቶች ማህበር መሪ ወጣት ሀብታሙ አያሌው በበኩሉ ፈቃድ የጠየቁት ከ 14 ቀናት በፊት እንደነበር ገልጿል::
በታሰሩት ላይ የተደረገው ምርመራ ከጉዳዩ ጋር ምንም አይነት ግንኙነት እንዳልነበረው ወጣት ሀብታሙ ተናግሯል::
ወጣት ሀብታሙ ዛሬም አንድ አባላቸው ታስሮ እንደነበር ገልጾ ወዴት እየሄድን እንደሆን አናውቅም ብሎአል:: በጉዳዩ ዙሪያ የመንግስትን አቋም ለማወቅ ያደረግነው ጥረት አልተሳካም።

No comments:

Post a Comment