Monday, December 3, 2012

Sunday, December 2, 2012


ኃላፊነቴን ከህዝቡ ጋር በአግባቡ እወጣለሁ – ዶ/ር ቴዎድሮስ አድሃኖም ሹመቱ ኢህአዴግ ያለበትን የፖለቲካ ሽኩቻ ለማስታገስ ያደረገው ነው የተሰጠው ሹመት በብቃት ላይ የተመሰረተ አይደለም ሹመቱ የቀድሞ ጠቅላይ ሚ/ር አሻራ አለበት (ተቃዋሚዎች) የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ከትናንት በስቲያ ያፀደቀውን የምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርነት፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትርነት፣ የንግድ ሚኒስትርነት፣ የጤና ጥበቃ ሚኒስትርነትና ሌሎች ሹመቶችን አስመልክቶ ሹመቱ በአግባቡና በሥርዓት ያልተሰጠና ህጋዊ ሥርዓት የሚጐድለው ነው ሲሉ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ተናገሩ፡፡ ሹመቱ ህገመንግስቱን የሚጋፋና ከህግና ሥርዓት ውጪ የተሰጠ ነው ሲሉም ተችተውታል፡፡

በአንድ ድምፀ ተአቅቦና በሙሉ ድምጽ ድጋፍ በፀደቀው ሹመት መሠረት ሁለት ተጨማሪ ጠቅላይ ሚኒስትሮችም ተሹመዋል፡፡ ከትናንት በስቲያ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በተከናወነው ሥነሥርዓት ሹመታቸው የፀደቀላቸው አቶ ሙክታር ከድር በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የመልካም አስተዳደር እና ሪፎርም ክላስተር አስተባባሪና የሲቪል ሰርቪስ ሚኒስቴር ሚኒስትር፣ ዶ/ር ደብረጽዮን ገብረሚካኤል በምክትል ጠቅላይ ሚ/ር ማዕረግ የፋይናንስና ኢኮኖሚ ክላስተር አስተባባሪና የመገናኛና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ሚኒስትር፣ ዶ/ር ቴዎድሮስ አድሃኖም የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ሚኒስትር፣ አቶ ታደለ ጫኔ የንግድ ሚኒስቴር ሚኒስትር እና ዶ/ር ከስተብርሃን አድማሱ የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ሚኒስትር ሆነው ተሹመዋል፡፡ ብቸኛው የመድረክ ተወካይና የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል የሆኑት አቶ ግርማ ሰይፉ በሹመቱ ወቅት ድምፀ ተአቅቦ አድርገዋል፡፡ አቶ ግርማ ድምፀ ተአቅቦ ያደረጉበትን ምክንያት ሲናገሩም፤ ሹመቱ ከመሰጠቱ በፊት ስለተሿሚዎቹ ለምክር ቤቱ አባላት መረጃ እንዳልደረሳቸው አመልክተው፤ ሹመቱ የተሰጠበት አሠራር ቀደም ሲል ተቃውሞአቸውን ሲያሰሙ በቆዩበት ህግ መሠረት በመሆኑና መዋቅሩ አስቀድሞ መጽደቅ ቢገባውም ባለመጽደቁ እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡

ፓርቲያቸው ምክር ቤቱ የሰጠው ሹመት ትክክል ነው ብሎ እንደማያምን የገለፁት አቶ ግርማ፤ በተለይ በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርነት ማዕረግ የተሰጠው ሹመት ህግና አሠራርን የተከተለና አግባብ የሆነ ነው ብሎ መቀበል እንደሚቸገሩ ተናግረዋል፡፡ ሹመቱ ኢህአዴግ ያለበትን የፖለቲካ ሽኩቻ ለማስታገስ ያቀረበው መፍትሄ ነው ያሉት አቶ ግርማ፤ ህጋዊ አሠራርን ያልተከተለና በብቃት ላይ ያልተመሰረተ ሹመት ነው ሲሉ ገልፀውታል፡፡ የኢዴፓ ሊቀመንበር አቶ ሙሼ ሰሙ በበኩላቸው፤ ፓርቲው እንደ ፓርቲ አቋም ለመያዝና መግለጫ ለማውጣት ገና አለመገናኘቱን ጠቁመው እንደግለሰብ ግን ሹመቱ ህጋዊ አሠራርን የተከተለ ነው ብሎ ማመን እንደማይችሉ ተናግረዋል፡፡ ይህ ሹመት የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር አሻራ ያለበትና ከዚህ ቀደም ይወራ የነበረውን ጉዳይ በይፋ ያረጋገጠ ሹመት ሆኖ እንደሚሰማቸውም ተናግረዋል፡፡ ሹመቱ የተሰጠበት አግባብ ህገመንግስታዊ ሥርዓቱን የተጋፋ ነው ያሉት አቶ ሙሼ፤ ይህንን ለማድረግ ከፈለጉም በቅድሚያ ህገመንግስቱን ማረም ያስፈልጋል ብለዋል፡፡ ኢህአዴግ ቀደም ሲል የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር በሚሰሩት ደረጃ ለመሥራት አቅም የለንም የሚለውን ሃሳብ የሚያጠናክርና በራሳቸው አቅም ማስቀጠል አለመቻላቸውን አመላካች ነው ሲሉም አክለዋል፡፡ “በጠቅላይ ሚኒስትሩ ሥር በርካታ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሮችን በመሾም የጠቅላይ ሚኒስትሩን ስልጣኖች ቀንሰው ለሌሎች ኃላፊነት መስጠት ምን ማለት እንደሆነ ግልጽ አይደለም፡፡ በሹመቱ ላይ ያለው ሁኔታ ግን ቀደም ሲል ሲወራ የቆየውን ጉዳይ ተግባራዊ ማድረግ ነው፤ ምንም አዲስ ነገር የለውም” ሲሉ ተናግረዋል – አቶ ሙሼ፡፡ በውጪ ጉዳይ ሚኒስትርነት የተሾሙት ዶ/ር ቴዎድሮስ አድሃኖም ሹመቱን አስመልክቶ በስልክ በሰጡን አስተያየት፤ የተጣለባቸው ሃላፊነት እጅግ ከፍ ያለ መሆኑን ጠቁመው፤ ህዝብ እምነት አሳድሮ እስከመረጠኝ ድረስ ሃላፊነቴን በአግባቡ ለመወጣት ዝግጁ ነኝ ብለዋል፡፡ ለአመታት የሰሩበትን የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር መ/ቤትን አስመልክተው ሲናገሩም፤ ቀደም ሲል በተዘጋጁ መስመሮች በመጓዝ ህዝቡን በሚያሳትፍ መልኩ ሥራዎችን መሥራት ከተተኪው ሚኒስትር የሚጠበቅ ተግባር መሆኑንም ዶ/ር ቴዎድሮስ ጠቁመዋል

No comments:

Post a Comment