Saturday, July 30, 2016

የረሃብ አድማ ላይ ያሉት ብርሃኑ ተ/ያሬድ እና ዮናታን ተስፋዬ ፍርድ ቤት ቀረቡ

July 30,2016


በቂሊንጦ የሚደርስባቸውን በደል በመቃወም ለ9 ቀን የረሃብ አድማ ያደረጉት እነ ብርሃኑ ተ/ያሬድ እና ዮናታን ተስፋዬ ትላንት ፍርድ ቤት ቀርበው ነበር። እነ ብርሃኑ (ብርሃኑ ተ/ያሬድ፣ እየሩስ ተስፋው፣ ፍቅረማርያም አስማማው እና ደሴ ካህሳይ) የቅጣት ማቅለያ እንዲያመጡ ነበር የተቀጠሩት።

የተሰጣቸው ቀጠሮ አጭር ስለነበረ እና የእስር ቤቱ አስተደዳደር በሚያደርስባቸው በደል ከቤተሰብ ጋር ባለመገናኘታቸው ማቅለያው ሊደርስላቸው እንዳልቻለ ተናግረዋል። በተጨማሪም አራተኛ ተከሳሽ ደሴ ካህሳይ ቤተሰቦቹ ሩቅ ሃገር በመሆናቸው ከነሱ ጋር ተነጋግሮ ማቅለያ ለማስገባት ጊዜ ስለሚፈልግ ረጅም ቀጠሮ እንዲሰጣቸው ቢጠይቁም ዳኛዋ የተሰጣችሁ ጊዜ በቂ ነው በማለት ከሃምሌ 29 በፊት በቢሮ ማቅለያዎቻቸውን እንዲያስገቡ እና ሃምሌ 29,2008 ፍርድ ለመስጠት ቀጠሮ ሰጥታለች። አቃቢ ህግ የቅጣት አስተያየቱን (ማክበጃ) አስገብቷል።

ብርሃኑ በረሃብ አድማው ምክንያት በመድከሙ ይሰጠው የነበረው ጉልኮስ ጠዋት ወደ ፍርድ ቤት ሲመጣ ነው የተነቀለለት። በዚህም ምክንያት ችሎት ውስጥ መቆም ባለመቻሉ ቁጭ ብሎ ነው የተከታተለው። ዮናታንም በተመሳሳይ ምክንያት ችሎት ውስጥ መቆም አልቻለም ነበር። ዮናታን ተቀጥሮ የነበረው የአቃቤ ህግን የደረጃ ምስክሮች ለመስማት የነበረ ቢሆንም የደረጃ ምስክሮቹ የሚሰጡትን ምስክርነት ዮናታን የሚክደው ስላልሆነ ምስክርነታቸው መሰማቱ ውድቅ ተደርጎ ለሃምሌ 28, 2008 ይከላከል ወይም አይከላከል የሚል ብይን ለመስጠት ቀጠሮ ተሰጥቷል።

No comments: