Wednesday, June 22, 2016

ህወሃት “አምባሳደሮችን” በታማኞቹ ሊተካ ነው

June22,2016
“የማይታመኑ ከሆነ “አለመታመናቸውን” ማሳየት አለባቸው”
ambassadors

በተለያዩ አገራት የሚገኙ አምባሳደሮች በወሳኝ የህወሃት ሰዎች ሊተኩ እንደሆነ ተነገረ፡፡ በህወሃት ውስጥ ያለው ፍርሃቻና አለመረጋጋት ለሁኔታው አስገዳጅነት ምክንያት ሆኖ ቀርቧል፡፡ ህወሃት ለዓመታት ያገለገሉትን ሎሌዎች የማያምናቸው ከሆነ እነርሱም “አለመታመናቸውን” ማሳየት ይገባቸዋል፡፡
በአሜሪካ፤ በአውሮጳ፤ በአውስትራሊያና በኢትዮጵያ አጎራባች በሆኑ አገራት የሚገኙ አምባሳደሮች በቅርቡ ወሳኝ በሆኑ የህወሃት ሰዎች ሊተኩ መታሰቡን ማንነታቸው እንዲገለጽ ያልፈለጉ የጎልጉል መረጃ አቀባይ አስታውቀዋል፡፡ ለመረጃው ቅርብ እንደሆኑና የአገራቱም ዝርዝር እንዳላቸው የተናገሩት መረጃ አቀባይ የሹምሽሩ ምክንያት ይህ ነው ተብሎ በውል ባይታወቅም ህወሃት ከውስጥና ጫና ተጠቃሽ እንደሆነ ይጠቁማሉ፡፡
በኢህአዴግ ተለጣፊና ድቃይ ድርጅቶች ታቅፈው የሥርዓቱ ሎሌ የሆኑት አምባሳደሮች በመጪዎቹ ሳምንታትና በሐምሌ ወር ወደ ኢትዮጵያ እንዲመጡ እንደሚደረግ ታውቋል፡፡ በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የሚደረግ ዓመታዊ ስብሰባና ግምገማ ተብሎ ሽፋን የሚሠጠው ይኸው አምባሳደሮችን የመጥራት ውሳኔ በህወሃት ሰዎች የተቀነባበረና የትኞቹን አምባሳደሮች በማን ለመተካት እንደታሰበ አስቀድሞ የተወሰነ ነው፡፡ በዓለምአቀፍ የዲፕሎማሲ ህግጋት መሠረት የሚነሱት አምባሳደሮች መረጃ ለየአገራቱ ደርሷል፡፡
ለ25 ዓመታት እጅግ አሰቃቂ ወንጀሎችን በመፈጸም በነጻ አውጪ ስም ኢትዮጵያን በፍግ እየገዛ ያለው የትግራይ ነጻ አውጪ ግምባር ከፍተኛ ችግር ውስጥ በሚወድቅበት ጊዜ ታማኝ የትግራይ ተወላጆችን በተለይም ነባር ታጋዮች ላይ አመኔታውን በማድረግ “ክፉ ጊዜያትን” ሲያልፍ ቆይቷል፡፡ የአሁኑም ጉዳይ ከዚህ የተለየ እንዳልሆነ ነገራል፡፡
በተለይ በሰብዓዊ መብት ረገጣ እያደረሰ ያለው ግፍ ከበቂ በላይ በሆነ ማስረጃ በተደጋጋሚ እየወጣበት ባለበት ባሁኑ ጊዜ የወደፊቱ ሁኔታ ምን ሊሆን ይችላል የሚለው መመለስ ያለበት ጥያቄ ሆኗል፡፡ ለዚህም ይመስላል በሰሜኑ ኢትዮጵያ ከአማራው ክልል ጋር ተያይዞ ያለውን አደገኛ ሁኔታ ለማምከን የኤርትራ ካርዱን የመዘዘው በማለት አስተያየት ሰጪዎች ይናገራሉ፡፡ ወራትን ያስቆጠረው የኦሮሞ ወጣቶች ተቃውሞ ከሁሉም በላይ አረመኔነቱንና ለሥልጣኑ ሲል የማይፈጽመው ወንጀል እንደሌለ በግልጽ ያሳየ መሆኑን ሰሞኑን የወጣው የሰብዓዊ መብት ተመልካቹ መ/ቤት (ሂውማን ራይትስ ዎች) ዘገባ ያሳያል፡፡
በተለይም በያዝነው ዓመት ጥር ወር አካባቢ የአውሮጳ ፓርላማ ኢህአዴግን “ልክ የሚያስገባ” ባለ 19 ነጥብ ውሳኔ ማስተላለፉ ይታወቃል፡፡ በወቅቱ ውሳኔው ኢህአዴግ “ልክ ሊገባ ይሆን” የሚል አመለካከት መጫሩን ጎልጉል ጠቅሶ በጻፈበት ወቅት “ረቂቁ ለውይይት እንዳይቀርብ የቻሉትን ያህል የጣሩት ቴድሮስ አድሃኖም “ዲፕሎማሲያቸው” አለመሥራቱን፤ ጉዳዩን በቅርበት የሚከታተሉ ውሳኔው “ውስጡ በብረት የተወጠረ የቦክስ ጓንቲ ነው” ማለታቸውን ጨምሮ ዘግቦ ነበር፡፡ ይህ በዝርዝር መረጃ ቀርቦበት ለውሳኔ የበቃው ሰነድ ቀኑን ጠብቆ ህወሃት ላይ ሰይፉን እንደሚመዝ የወንጀሉ ተዋናዮች ከማንም በላይ የሚረዱት እውነታ ሆኗል፡፡
በአሜሪካ፤ ወሳኝ በሆኑ የአውሮጳ ከተሞች (ህብረቱ ያለበትንም ጨምሮ) እንዲሁም በኢትዮጵያ አጎራባች አገራት ያሉ አምባሳደሮች በታማኝ የህወሃት ተጋዳላዮች ለመተካት መታሰቡ የዲፕሎማሲው ተጽዕኖ ያስከተለው ጫና ብቻ ሳይሆን በህወሃት ውስጥ ሌላም ፍርሃቻ ስለአለ ነው በማለት ጉዳዩን ከሌላ አንጻር የሚመለከቱ ይናገራሉ፡፡
አሊ ኦጃሊ
አሊ ኦጃሊ
ምዕራባውያን ኃይላት ትኩረታቸውን ሊቢያ ላይ አድርገው ጋዳፊን ከሥልጣን ለማውረድ እንቅስቃሴ በጀመሩበት ወቅት ዓመጹ እየተፋፋመ ሲሄድ በየአገሩ የነበሩ የጋዳፊ ታማኞች መክዳታቸው ይታወሳል፡፡ ጋዳፊ ህይወታቸው በOctober 2011 ከማለፉ ስምንት ወራት በፊት በዋሽንግተን ዲሲ ታማኝ አድርገው ያስቀመጧቸው አምባሳደር አሊ ኦጃሊ ጋዳፊን መክዳታቸው ይታወቃል፡፡ ለጋዳፊ ታማኝ በመሆን አርባ ዓመት ያህል ያገለገሉት አምባሳደሩ በወቅቱ ከከዱ በኋላ የአማጺውን ኃይል ተቀላቅለው ነበር፡፡ ከዚህ አልፈው በአሜሪካ የአማጺው አፈቀላጤና ተወካይ በመሆን ሲሰሩ ከቆዩ በኋላ የጋዳፊ መውደቅ እውን እየሆነ ሲሄድ አሜሪካ መልሳ በቦታቸው አስቀምጣቸው ነበር፡፡ ከዚህ አንጻር ህወሃትን ያስፈራው ይህንን መሰል የፖለቲካ ቁማር እንደሆነ ይነገራል፡፡
ከሎሌነት ባላለፈ አገልግሎት የሚሰጡትን “የራሴ፤ ታማኞቼ” ከሚላቸው ጋር ፈጽሞ እኩል ሊያደርጋቸው የማይፈልገው ህወሃት የፖለቲካው ትኩሳት አቅጣጫውን የቀየረ ዕለት የአሊ ኦጃሊን መንገድ ሊከተሉ ይችላሉ ብሎ የጠረጠራቸውን በቶሎ ለመተካት መወሰኑ “ከጋዳፊ ተምረናል” የሚል እንድምታ እንዳለው ይነገራል፡፡ በየትኛውም የለውጥ እንቅስቃሴ ጊዜ በተለይ በጎረቤትና በኃያላን አገራት ያሉ አምባሳደሮች መክዳት አልፎም ንቅናቄውን መቀላቀል የአምባገነኖችን ዕድሜ በማሳጠር በኩል ቁልፍ ሚና ይኖረዋል የሚሉ አስተያየት ሰጪዎች ህወሃት ምዕራባውያን በተገኘው አጋጣሚ ፊታቸውን እንደሚያዞሩበት በመገመት ይህንን መሰሉን ጥንቃቄ ማድረጉ ሥልጣኑን እንዴት እንደሚንከባከብ የሚያሳይ ነው፡፡ በተለይ የኦህዴድ መሸርሸርና በክልሉ ያለው ዓመጽ እስካሁን አለመብረድ ከአምባሳደር ጀምሮ እስከ በታች እርከን የቆንስላ ተግባራት ላ የተሰማሩ ኦሮሞ ዲፕሎማቶችንና ሠራተኞችን በዓይነቁራኛ እንዲታዩ እያደረጋቸው ነው፡፡ ከዚህ አንጻር “ለችግር ጊዜ አትታመኑም” ተብለው እንደሸቀጥ እንዲመለሱ የሚጠሩት አምባሳደሮች ቀን ፊቷን ሳታዞርባቸው ለምንስ በእርግጥ “የማይታመኑ መሆናቸውን” ለህወሃት አያሳዩትም በማለት የዜናው አቀባይ ለዲፕሎማቶቹ ጥሪ አዘል ምክር ለግሰዋል፡፡   (ፎቶ: ያለፈው አመት ሹመኞች)
ምንጭ ጎልጉል

No comments: