Saturday, February 13, 2016

ህዝቡ ወያኔን በቃኝ ብሏል እኛም የወያኔ እድሜ የሚያጥርበትን ከፍተኛ ስራዎች እየሰራን ነው ያለነው (አርበኛ ታጋይ መንግስቱ ወ/ስላሴ)

February 13,2016
(የአርበኞች ግንቦት 7 ድምፅ ሬድዮ)
አርበኛ ታጋይ መንግስቱ ወ/ስላሴ የአርበኞች ግንቦት 7 ለአንድነትና ዴሞክራሲ ንቅናቄ ህዝባዊ እምቢተኝነት መምሪያ ኃላፊ የኢትዮጵያን ወቅታዊ የፖለቲካ ሁኔታና ወደ ኤርትራ በረሃ የሚጎርፉ ወጣቶች ቁጥር እየናረ መምጣትን በሚመለከት ከአርበኞች ግንቦት 7 ድምፅ ሬድዮ ጋር ያደረጉት አጭር ቃለ ምልልስ በፅሁፍ፡፡


ጥያቄ
"አርበኛ ታጋይ መንግስቱ ወ/ስላሴ እርስዎ የአርበኞች ግንቦት 7 ለአንድነትና ዴሞክራሲ ንቅናቄ ህዝባዊ እምቢተኝነት መምሪያ ሀላፊ ነዎት፤ በሀገሪቱ ላይ በተለይ አሁን በየቦታው ውጥረት አለ፤ በኦሮምያ የአዲስ አበባን ማስተር ፕላን ምክንያት አድርጎ የመንግስት ለውጥ መምጣት አለበት በሚል ህዝባዊ ትግል እየተካሄደ ነው የሚገኘው፡፡ ብዙ ወጣቶች እየተገደሉ ነው፡፡ ጋምቤላ ውስጥ አሁንም ከፍተኛ ግጭት ተፈጥሯል፡፡ ጎንደር ላይ እንደዚሁ ህወሓት ለሱዳን መሬት ቆርሶ ለመስጠት ተስማምቷል፡፡ በዚህ ምክንያት አሁን ከፍተኛ የሆነ አመፅ አለ፤ ከመከላከያ ሰራዊቱ ጋር ህዝቡ ፍልሚያ ላይ ነው ያለው፡፡ እና ይህንን ወደ ዘር ግጭት እንዲያመራ ህወሓት ደግሞ እየስራ ይገኛል፡፡ ህዝቡ ትግል እያደረገ ነው፡፡ ይህን ትግል ከማደራጀትና ከመምራት ጋር በተያያዘ ህዝባዊ እምቢተኝነት ያለው ሚና ምንድን ነው?"
አርበኛ ታጋይ መንግስቱ ወ/ስላሴ
"አመሰግናለሁ! እንግዲህ አርበኞች ግንቦት 7 የቀድሞው ግንቦት 7 እና አርበኞች ግንባር ከተዋሀደ በኋላ መዋቅሩን አስፍቶ በብዙ መልኩ ትግሉን በሀገር ውስጥ እያደረገ መሆኑን እንግዲህ በእናንተም በተለያየ መገናኛ ብዙሃን እየተገለፀ ይገኛል፡፡ ድርጅታችን በህዝባዊ እምቢተኝነት መምሪያ በኩል ሃገር ውስጥ ሰፊ የሆነ መዋቅር አለው፡፡ ህዝቡን ማደራጀት እና የተቀበረ ፈንጅ የማስቀመጥ ያክል በብዙ የሃገሪቱ ክፍል ላይ ከፍተኛ መዋቅር ዘርግተን እያደራጀን ነው ያለነው፡፡ በዚህ ሂደት ምን፣ ምን እንቅሰቃሴዎች ያደርጋሉ በህዝባዊ እምቢተኝነት ውሰጥ ያሉት...? ዘርፈ ብዙ ነውና ህዝቡ በሚያደርጋቸው አመፆች በሙሉ የህዝባዊ እምቢተኝነት መምሪያ አባላት እጃቸው እንዳለ መግለፅ እወዳለሁ፡፡
"ሌላው እንደገና ደግሞ ህዝቡም እምቢ ማለቱ ትልቁ ምልክት አሁን በቅርቡ በኦሮምያ የአዲስ አበባ ማስተር ፕላንን መሰረት አድርጎ የተደረገው እንቅስቃሴ በአዲስ አበባና አካባቢዋ ብቻ አይደለም በሙሉ ኦሮምያ ክልል ብቻ ሳይሆን ሃዋሳ፣ ጎንደር፣ ጋምቤላ ሁሉ ያለው ተቃውሞ የስርአቱን ብልሹነት ወይም ስርአቱን በቃኝ ባይነት ምልክት መሆኑን ነው እኛ ምናየው፡፡ ስለዚህ ይሄ አሁን ተቀጣጥሎ ያለው የአዲሰ አበባን ማስተር ፕላን ምክንያት አድርጎ የተነሳው የኦሮሞ ወገናችንን ብቻ የሚመለከት ሳይሆን የኢትዮጵያ ህዝብ ጥያቄ ሆኖ የተነሳበትና ከፍተኛ እንቅስቃሴ የተደረገ ያለበት ነው፡፡ ሌላው ምንድን ነው? በጎንደር አካባቢ ያለውን የኢትዮጵያን መሬት ለሱዳን አሳልፎ የሚሰጥበት ሁኔታ የጎንደርን ወይም በአማራ አካባቢ ያለውን ተወላጅ ብቻ ጥያቄ ብቻ ሳይሆን የኢትዮጵያዊያን ሙሉ ጥያቄ ሆኖ ከፍተኛ እንቅስቃሴ እየተደረገ ነው፡፡ እንግዲህ በነዚህ ሁሉ መሃል ውስጥ የአርበኞች ግንቦት 7 ህዝባዊ እምቢተኝነት መምሪያ የሚሰራቸው አሉ፤ እነዚህ ሂደቶች በሙሉ እንቅስቃሴው እየተጋጋለ እዲሄድና ህዝቡ በሙሉ እንቢ ብሎ በወያኔ ላይ ሊያምፅ ሚችልበትን አይነት ስራዎች እየተሰሩ ነው ያሉት፡፡ እነዚህ ፖፕሌቶችን መበተን ለሊቱን ሙሉ... ሲነጋ ግድግዳዎች በሙሉ፣ ግንቡ በሙሉ ወያኔን የሚቃወሙ ፁሁፎች ማውጣት፤ እደገና ህዝቡ በሚንቀሳቀስበት አይነት ነገሮች ላይ ያ ገላጭ የሆነ የወያኔን ተቃውሞ ሊገልፅ ሚችል አይነት እንቅስቃሴዎችን በማድረግ እረገድ የኛ መምሪያ አባሎች እየሰሩ ነው፡፡
"በዚህ በትግሉ እንቅስቃሴ ውስጥ ወደ ህዝባዊ አመፅ መቀላቀል የሚፈልጉ አካሎች ወደ ኤርትራ እየመጡ የሄዱበት ነው፡፡ ወደ ህዝባዊ አመፅ ሊቀላቀሉ እና ወያኔን በብረት እንፋለማለን ብለው የወሰኑ ወጣቶች ያለፈውን ጊዜ እንተወውና በዚህ ወር ብቻ ከ60 በላይ ተከዜን ተሻግረው ኤርትራ ገብተዋል፡፡ እነዚህም በስልጠና ሂደት ውስጥ ይገኛሉ፡፡ ይሄ ብቻ አገር ውስጥ ያለው ሰራዊታችንን በውጊያ ላይ ያለውን የሚቀላቀሉትን ቁጥር ሳይጨምር ማለት ነው ወደ ኤርትራ በረሃ በዚህ ወር ብቻ የመጡትን ይህንን የምገልፅልህ፡፡ ይህንን እና በዚህ መሰል ሁኔታዎች ከፍተኛ እንቅስቃሴ እያደረገ ነው የህዝባዊ እምቢተኝነት መምሪያ፡፡"
ጥያቄ
"አመሰግናለሁ አርበኛ ታጋይ መንግስቱ ወ/ስላሴ! አሁን አገር ቤት ከፍተኛ የሆነ ግድያ አለ፤ ጭቆና አለ፤ ህወሓት ምንም የማይሰራው ነገር የለውም፤ የማይፈፅመው ነገር የለውም፤ በህዝቡ ላይ ያለውን... የህዝቡን እንቅስቃሴ ለማክሸፍና በነበረው ለማስኬድ ደግሞ ልምድ አለው፤ ከ1997 ዓ.ም ጀምሮ ሲሰራበት የቆየው ነው፡፡ አሁን እንደ በፊቱ በቀላሉ የህዝቡን የነፃነት ትግል፣ የነፃነት እንቅስቃሴ እና አመፅ የሚያከፍሽፍበት ደረጃ ላይ አይደለም ያለው፡፡ ከቁጥጥሩ ውጭ ሆኗል ማለት ይቻላል፡፡ በዚህም ምክንያት ይመስላል ድንበር አካባቢ ከፍተኛ የሆነ ሰራዊት አስፍሮ የኤርትራንና የኢዮጵያን ድንበር በከፍተኛ ሁኔታ አጥሮት ነው የሚገኘው፡፡ ነገር ግን ሰዎች ይመጣሉ፤ ሰዎች ይጎርፋሉ፡፡ በየቀኑ በጣም በርካታ ሰዎች እንዲያውም ከትግራይ፤ ምንም የህወሓት ተቃዋሚ የለም የትግራይ ህዝብ ወያኔ ነው ካለበት ከትግራይ ብዙ ወጣቶች እየመጡ ነው፡፡ ተከዜን እየተሻገሩ አሁን የአርኞች ግንቦት 7 ኤርትራ በርሃ ውስጥ ሚገኙ የተለያዩ ማሰልጠኛዎች በኢትዮጵያ ወጣቶች እየተጥለቀለቁ ነው የሚኙት፡፡ በህዝባዊ እምቢተኝነት መምሪያ ስር ተደራጅተው ሀገር ቤት ለሚሰሩ ወጣቶች ሆነ ትግሉን መቀላቀል ለሚፈልጉ ሌሎች የአገሪቱ ወጣቶች ምን መልዕክት ነው ሚያስተላልፉላቸው?
አርበኛ ታጋይ መንግስቱ ወ/ስላሴ
"መልካም! መጀመሪያ ወያኔ በአልሞትባይ ተጋዳይነት እርምጃ እየወሰደ ነው ያለው፡፡ ሰሞኑን የምናየው አለ፡፡ አዋሳ ላይ በአደባባይ ነው፣ በጠራራ ፀሐይ ሰው እየተገደለ ያለበት ሁኔታ ነው ያለው፡፡ በጎንደር እንደገና ደግሞ ጥያቄ ያነሱ የወልቃይት ተወላጆችን ሰብስቦ አዲስ አበባ ለጥያቄ የሄዱትን ያሰረበት ሁኔታና በአጠቃላይ ወያኔ በአሁኑ ሰዓት እንዳልከው የህዝቡን አመፅ ሊያፍን የሚችልበት አይነት ሁኔታ ላይ አይደለም ያለው፡፡ ረግጦ ሊገዛ የሚችልበት አይነት ሁኔታ ላይ አይደለም ያለው፡፡ ለምን በሁሉም የአገሪቱ ክፍል ወያኔ ላይ እምቢ ብሏል ህዝቡ፡፡ እምቢ ማለቱ ምልክቶች የምታየው ነው፡፡ ወያኔም በእንደዚህ አይነት ሁኔታዎች በተለያየ መልኩ ትግሉን ሊያፍን የሚችልበት አይነት አርምጃዎች ይወስዳል፡፡ ሆኖም ግን አልተሳካለትም፡፡ አሁን አንተ ራሱ የጠቀስከው እንደምሳሌ የማነሳልህ በሰሜኑ የአገራችን ክፍል የአርበኞች ግንቦት 7 ሰራዊትን ለመቀላቀል የሚመጡ የማህበረሰብ አካላትን ለማፈን ሲል ሰራዊቱን አፍስሶታል፡፡ ሆኖም ግን ይመጣል፡፡ በነገራችን ላይ በወያኔ መከላከያ ሰራዊት ውስጥ ያለው ወጣት ኢትዮጵያዊ ነው፡፡ ከ10ኛ ክፍል በላይ መቀጠል ሳይችል ቀርቶ ሰርቶ የሚበላው ያጣ፡፡ ለሆዱና ለኑሮው ራሱን ለማሸነፍ ሲል የገባ ሰራዊት እንጂ የወያኔ ደጋፊ እንደላሆነ አይደለም በሰራዊቱ ውስጥ በሌላው የወያኔ መዋቅር ውስጥ ያሉ ከታች እስከ አመራር ድረስ ማሳያ ብዙ መልኮች አሉ፡፡ ይህም በመሆኑ ነው ወያኔ የመጨረሻ ደረጃ ላይ ደርሷል የምልህ፡፡

"ሌላው በህዝባዊ እምቢተኝነት መምሪያ ተደራጅተው ወደ አርበኞች ግንቦት 7 ሰራዊት እየተቀላቀሉ ያሉት በአብዛኛው በዚህ አሁን ከስልሳ በላይ ካልኩህ ቁጥር በዚህ ወር እንኳን ከገቡት አብዛኛውን ቁጥር የሚይዘው የትግራይ ተወላጅ ነው፡፡ የትግራይ ተወላጅ ትግሬ ስለሆነ የወያኔ ደጋፊ ነው፤ ወያኔን ተቃውሞ ሊወጣ የሚችል ሃይል የለም፤ ይሄ የወያኔ ፕሮፓጋንዳ ነው፡፡ እንደገና የትግራይን ህዝብ ከሌላው ብሄረሰብ ጋር ለማጋጨት የሚያደርገው፤ ወያኔ የትግራይን ህዝብ ነጥሎ ምናልባት በኋላ መጠጊያ መሸሻየ ይሆነኛል ብሎ ስለሚያስብ የሚያደርገው ነገር ነው እንጂ የትግራይ ህዝብ ኢትዮጵያዊ ነው፡፡ ከጥንትም ጀምሮ ለኢትዮጵያ ትልቅ ታሪክ ሲሰራ የመጣ ንፁህ ኢትዮጵያዊ ዜጋ ነው፡፡ ወያኔን በመቃወም ደግሞ ቅድሚያ ተሰልፎ ከእኛ ጋር እየተዋደቀ መሆኑን ይሄው ምናይበት ደረጃ ነው፡፡

"ሌላው በአገራችን ክፍል ያለው ሁሉም እዛ ቦታ ላይ መንቀሳቀስ በሚገባው መልኩ ይንቀሳቀሳል፡፡ እዚህ ጋ በገንዘብ፣ በጉልበት፣ በእውቀት በማደራጀት ረገድ በእድሜ ገደብ ሳይኖረው ጠቅላላ እምቢ ብሎ ያለበት ሁኔታ ነው፡፡ ይህ ህዝባዊ እምቢተኝነት ደግሞ ምን ያክል ሰርቷል? እንዴት ነው ያለው? አሁን ካለው እንቅሰቃሴ በተጨማሪ ወደፊት ያ ጊዜውን ጠብቆ ሊፈነዳ የሚችለው ፈንጅ ረጅም እንደማይሆን የሚያሳዩ አይነት ሁኔታዎች ያሉበትና ወያኔም ያንን ተከትሎ በያካባቢው እያፈሰ እያጎረ ያለ ነው፡፡ እንግዲህ በተለያየ ሚዲያ ይገለፃል በይበልጥ በዚህ በሰሜን ምዕራብ የአገራችን ክፍል በአብዛኛው የአርበኞች ግንቦት 7 ሰራዊት የሚንቀሳቀስበት ላይ ወያኔ እንዳለ ሙሉ ኃይሉን አፍስሶ እዛ ቦታ ላይ ነው ያለው፡፡ ሆኖም ሊቋቋመው ያልቻለበትና የአርበኞች ግንቦት 7 ደግሞ የሽምቅ ተዋጊዎች ከፍተኛ እንቅቃሴ እያደረጉ አገር ውስጥ እንደገና ገብተው ህዝባዊ የሆነ አመፅ ባንዴ ሊቀጣጠል የሚችልበትን አይነት ሁኔታ የአርበኞች ግንቦት 7 እየሰራ ነው ያለው፡፡ የሚሰራውም ይህን ነው፡፡ ደም ጠማኝ ብሎ የወጣም ድርጅት ስላልሆነ ህዝባዊ ዴሞክራሲያዊ የሆነች አንድነቷን የጠበቀች ሉዓላዊት ኢትዮጵያን ለመመስረት የሚታገልና በኢትዮጵያ ላይ እንደገና ደግሞ የህዝብ ድምፅ ሊከበር የሚችልለት ህዝቡ ራሱ የመረጠው ስርዓት ሊኖር የሚችልበትን በማመቻቸት ረገድ ህዝቡ የፈቀደው ሊወጣ ህዝብ የተቃወመው ሊወርድ የሚችልበት አይነት ስርዓት ለመዘርጋት የአርበኝነት ትግል ስለሆነ ይህ ድርጅት ወደፊትም እንደገና ደግሞ ኢትዮጵያ ላይ ጥቅም አንግቦ የተነሳ ባለመሆኑ ያን ዓላማ የያዘ ኃይል ደግሞ አገርና ህዝብ ማንኛውም ዜጋ ማይደግፍበት ምክንያት የለም ሁሉም ዜጋ ከእኛ ጋር ነው፡፡ ኢትዮጵያ የሚያስፈልጋት የአርበኝነት ትግል ነው፡፡ ብረት ይዞ በብረት የሚገዛበት አይነት ዘመን ማብቃት አለበት ብለን የተነሳን ኃይሎች ነን፡፡ አርበኞች ግንቦት 7 ኢትዮጵያ ከብረት አገዛዝ ነፃ የሆነች ኢትዮጵያ መኖር አለባት ብለን በአርበኝነት በነፃ ለነፃነታችን ህይወጣችንን ልንሰጥ የተነሳንበት ስለሆነ ይህንን ዓላማ፣ ይህን የተቀደሰ ዓላማ የማይደግፍ ህዝብ የለም፡፡ ሁሉም ከጎናችን ነው፡፡ ለምን እኛ ምሳሌ ሆነን ወጥተናል፤ ህዝቡም በስራችን እንዲደራጅ ጠይቀነዋል፤ ዓላማችንን ተረድቷል፤ ወያኔን በቃኝ ብሏል፤ ከፍተኛ እንቅስቃሴ እያደረገ ይገኛል፡፡ የወያኔ እድሜ የሚያጥርበትን ከፍተኛ ስራዎች እየሰራን ነው ያለነው፡፡

"ሌላው በአርበኞች ግንቦት 7 ህዘባዊ እምቢተኝነት ያልደረሰበት የማህበረሰብ አካል የለም ማለት እችላለሁ፡፡ በዛ ደረጃ ላይ ባለው አደረጃጀት በእርግጥ በህቡዕ የተደራጀ አካል ስለሆነ ሁሉም በዛ በህቡዕ ሊገባ የሚችልበት በአርበኞች ግንቦት 7 የትግል መስመርና ህዝባዊ እምቢተኝነት ያሰራር ሂደት መሰረት በዛ ውስጥ ተካቶ ሁሉም የራሱን አስተዋፆ ሊያደርግ እንዲችል መልዕክቴን አስተላልፋለሁ፡፡ በአሁኑ ሰአት በህዝባዊ እምቢተኝነት በዚህ ቦታ ይህን ያህል ሰው እንደዚህ ተደራጅቷል፤ ይሄን ሊያደርግ ተዘጋጅቷል፤ ብለን መግለፅ ባንችልም ባጠቃላይ ግን ሰአቱ በደረሰበት ጊዜ ላይ ሊፈነዳ የሚችለውና የወያኔን ግብአተ መሬት ሊያፋጥን የሚችልበት አይነት ሁኔታዎች ሰርተናል፡፡ ለዚህም አሁንም ጠንክረን እየሰራን ነው፡፡ በተረፈ ከዚህ ሂደት ባለው ሁሉም ወጣቱ በይበልጥ የወያኔን እድሜ በማሳጠር ረገድ የተፋጠነ ስራ ልንሰራ እንድንችል ወደ አመፅ ትግሉ ሊቀላቀል እንዲችል ወደ አርበኞች ግንቦት 7 የስልጠና ማዕከል ሊገባ የሚችልበትን ከአሁን በፊት መጥተው ወደ ኤርትራ በኛ ስልጠና ማዕከል የተገኙትን ምን ያክል እንደሆኑ በዚህ ወር ብቻ ገልፀናል፡፡ እስከ አሁን ድርስ ከፍተኛ ቁጥር አለው፡፡ በዚህ ቦታ ላይ ሰልጥነን የድርጀቱን የትግል መስመር እና አላማና ፕሮግራም ተከትለን በድርጅታችን መዋቅር እና መተዳደሪያ ደንብ መሰረት ህጉን የተከተለ ብቃት ያለው ሰራዊት ሆነን ወደ ሃገር ውስጥ ተመልሰን ገብተን ለሃገራችን እና ለህዝባችን እንድንደርስ ልታደርጉ ይገባል የሚል ጥሪየን አሰተላልፋለሁ፡፡ አመሰግናለሁ!"

No comments: