Saturday, January 2, 2016

“ከአገዛዝ ወደ ነፃነት የምንሸጋገርበት ትግል ላይ ነን”

January 2,2016
ኢ/ር ይልቃል ጌትነት፤ የሰማያዊ ፓርቲ ሊ/መንበር
yilkal
አለማየሁ አንበሴ
የሰማያዊና ኦፌኮ ፓርቲ አባላትና አመራሮች መታሰራቸውን ሰማያዊ ፓርቲ ያወገዘ ሲሆን፤ “አሁን የፓርቲ ፖለቲካ የምናደርግበት ጊዜ ላይ አይደለንም፤ ከአገዛዝ ወደ ነፃነት የምንሸጋገርበት ትግል ላይ ነን” ብለዋል የፓርቲው ሊ/መንበር ኢ/ር ይልቃል ጌትነት፡፡
የሰማያዊ አመራሮች ባለፈው ረቡዕ በፅ/ቤታቸው በሰጡት መግለጫ፤ በኦሮሚያ ክልል የተፈጠረውን ተቃውሞ ተከትሎ ዜጎች መገደላቸውንና በርካቶች መታሰራቸውን በመጥቀስ “መንግስት ፋና ወጊ የሆኑትን ተራ በተራ እየለቀመ የእሳት እራት እያደረጋቸው ነው” ሲሉ ወቅሰዋል፡፡
የፓርቲው ልሳን የሆነው የ“ነገረ ኢትዮጵያ” ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ፣ ጋዜጠኛ ጌታቸው ሽፈራው፣ የፓርቲው የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ የነበረው ዮናታን ተስፋዬ፣ የፓርቲው አባላት፡- ቴዎድሮስ አስፋው፣ ዳንኤል ተስፋዬ፣ ኤርሚያስ ፀጋዬና ፍሬው ተክሌ መታሰራቸውን የጠቆመው ሰማያዊ፤ የታሰሩት አባላት ፍ/ቤት ቀርበው፣ ፖሊስ በሽብር ወንጀል እንደጠረጠራቸው በመግለፅ ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ ቀጠሮ ጠይቆባቸዋል ብሏል፡፡
በቅርቡ ጠ/ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ፤ በኢትዮጵያና ሱዳን ድንበር ዙሪያ ለፓርላማ ያደረጉትን ንግግር የተቹት የፓርቲው ሊቀመንበር ኢንጂነር ይልቃል፤ “ጠ/ሚኒስትሩ  ለፓርላማ ባደረጉት ንግግር፤ ኢትዮጵያውያን የሱዳንን ድንበር የደፈሩ አስመስለው ዜጎችን “ሽፍቶች” በማለት የማይረሳ ታሪካዊ የክህደት ምስክርነት ሰጥተዋል” ሲል ብለዋል፡፡
ምንጭ – አዲስ አድማስ

No comments: