Sunday, November 16, 2014

ሰበር ዜና – የቅ/ሲኖዶሱን ልዕልናና ሕገ ቤተ ክርስቲያንን መፃረራቸውን የቀጠሉት አቡነ ማትያስ ማኅበረ ቅዱሳንን ‹‹የቤተ ክርስቲያን ቅኝ ገዥ›› አሉት – ‹‹አባ ማትያስ አላበደም፤ በዚኽ መግለጫ እንድትሠሩበት ነው የምነግራችኹ›› ሲሉም በማኅበሩ ላይ የጥፋት መልእክታቸውን ዐዋጁበት!

November 16,2014
  • ጥቂት አማሳኞች በማንጨብጨብ ሲከተሏቸው፣ ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳቱን ጨምሮ ብዙኃን ጉባኤተኞች በድንጋጤና በተደምሞ አዳምጠዋቸዋል፡፡ ፓትርያርኩ በቀቢጸ ተስፋ ውስጥ እንዳሉም አመላካች ኾኗል፡፡
  • ማኅበረ ቅዱሳን÷ በጉባኤያት፣ በኅትመትና በኤሌክትሮኒክስ የስብከተ ወንጌል ስርጭት፣ በቅዱሳት መካናት ልማት፣ በአብነት ት/ቤቶችና በካህናት ማሠልጠኛዎች ድጎማና ሞያዊ እገዛዎች ያከናወናቸው ተግባራት በብፁዕ ጠቅላይ ሥራ አስኪያጁ ሪፖርት በስፋት ተዳስሰዋል፤ ጉባኤተኞች ማኅበሩ ላስመዘገባቸው የሥራ ፍሬዎች ደማቅ ድጋፋቸውን ገልጸዋል፡፡
his-hholiness00ዛሬ፣ ጥቅምት ፭ ቀን ፳፻፯ ዓ.ም. በጠቅላይ ቤተ ክህነት የስብሰባ አዳራሽ በተጀመረው ፴፫ኛው የመንበረ ፓትርያርክ አጠቃላይ ሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ ዓመታዊ መደበኛ ስብሰባ ላይ የጉባኤ መክፈቻ ቃለ በረከት እንዲሰጡ የተጋበዙት ፓትርያርክ አባ ማትያስ፣ ማኅበረ ቅዱሳንን ‹‹የቤተ ክርስቲያን ቅኝ ገዥ›› በማለት ‹‹በቁጥጥር ሥር እንዲውል›› ቅስቀሳ እንዳካሔዱበት ተሰማ፡፡
ፓትርያርኩ የጉባኤ መክፈቻ ‹ቃለ በረከታቸው› ማሳረጊያ ላደረጉት ቅስቀሳ መሰል ንግግራቸው መግቢያ ያደረጉት፣ ‹‹ስለ ቤተ ክርስቲያን ወቅታዊ ኹኔታ ልገልጽ እፈልጋለኹ፤ ይህ ጉባኤ በዓመት አንዴ የሚገኝ ነው፤ ዕድሉ እንዲያመልጠኝ አልፈልግም፤›› በሚል ቃለ አጽንዖት ነበር፡፡
ከዚያም ‹‹ቤተ ክርስቲያናችን በቅኝ ገዥዎች ተይዛለች›› ካሉ በኋላ ‹‹ቅኝ ገዥው ማን ነው?››ሲሉ ጠይቁ፡፡ ምላሹን ራሳቸው ሲሰጡ፣ ‹‹ኹላችኁም የምታውቁት አንድ ማኅበር ነው›› ሲሉ ጠቆሙ፡፡ ‹‹በምን?›› ሲሉ ዳግመኛ ጠየቁና ‹‹በገንዘብ፤ በራስዋ ገንዘብ፤ ይኼን እንድታውቁ እፈልጋለኹ›› ሲሉ መለሱ፤ ‹‹እኔ ይኽን ጉዳይ ከራሴ አወርዳለኹ፤ የቤተ ክርስቲያናችን ገንዘቧ፣ ክብሯ ተወስዷል፤›› በማለትም አስረገጡ፡፡
በአምናው ዓመታዊ ስብሰባ፣ ‹‹ማኅበሩ በቁጥጥር ሥር እንዲውል›› አጠቃላይ ጉባኤው ውሳኔ አሳልፎ ነበር ያሉት ፓትርያርክ አባ ማትያስ፣ ‹‹ገንዘቡ፣ ንብረቱ በቁጥጥር ሥር እንዲውል የወሰናችኁት አንድም አልተፈጸመም፤ እነርሱም ፈቃደኛ አልኾኑም፤ ማን ጠይቆ?›› ሲሉ ኹኔታው ከአቅማቸው በላይ እንደኾነ ገልጸዋል፡፡
አስከትለውም ‹‹ቤተ ክርስቲያን ከቅኝ ተገዥነት ትውጣ፤ ካህናቱ ከመከራ ይውጡ›› በማለት መልእክታቸውን በማንኛውም ቦታ እንደሚያስተላልፉ ከተናገሩ በኋላ፣ በሓላፊነት የተቀመጡት ‹‹ይህችን ቤተ ክርስቲያን ለመጠበቅ፤ አንዷን ቅድስት፣ ኦርቶዶክሳዊትና ታሪካዊት ቤተ ክርስቲያን ልመራ እንጂ ኹለት ቤተ ክርስቲያን የለችም፤›› ብለዋል፡፡
በመጨረሻም ‹‹የቤተ ክርስቲያን ቅኝ ገዥ ነው፤›› ባሉት ማኅበረ ቅዱሳን ላይ የጥፋት መልእክታቸውን ያስተላለፉት በሚከተለው መልክ ነበር፡-
‹‹እኔ ብቻዬን የምሠራው ነገር የለም፤ በዚኽ መግለጫ እንድትሠሩበት ነው የምነግራችኹ፤ አባ ማትያስ አላበደም፤ መልእክቴን እያስተላለፍኹ ነው ያለኹት፤ መልእክቴን ተቀበሉ ብዬ እማፀናችኋለኹ፡፡››
የፓትርያርኩ አቋም ብዙም ያልተጠበቀ አልነበረም፡፡ ይኹንና የአዲስ አበባ ገዳማትና አድባራት አስተዳዳሪዎች ከተቀመጡበት አካባቢ ጥቂት አማሳኞች ቢያንጨበጭቡላቸውም በብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳቱና በጉባኤተኞች ላይ ሰፍኖ ይታይ በነበረው መደመምና ድንጋጤ የተዋጠ እንደነበር ተገልጧል፡፡ ‹‹የመልካም አስተዳደር አስተሳሰብን ማበልጸግ›› በሚል ሰበብ መስከረም ፳፯ ቀን በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት አዳራሽ፣ መስከረም ፳፱ ቀን በጠቅላይ ቤተ ክህነት አዳራሽ በማኅበረ ቅዱሳንና በቅዱስ ሲኖዶስ አባላት ላይ ከርእሱ በመውጣት በከፈቱት ዘመቻ፤ ብፁዕ ጠቅላይ ሥራ አስኪያጁንና ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳቱን ጨምሮ ከቤተ ክርስቲያናችን ከፍተኛ ሓላፊዎችና በብዙኃን መገናኛ አውታሮች ከተስተጋባው የብዙኃን አገልጋዮችና ምእመናን ብርቱ ተቃውሞ የተነሣ በቀቢጸ ተስፋ ውስጥ እንዳሉ አመላካች ተደርጎም ተወስዷል፡፡
የጉባኤተኞችን ቀልብና ስሜት ለመግዛት የተጠቀሙበት ቅስቀሳ ‹‹ከልጆቹ ጋራ እልክ መጋባታቸውን›› ያሳያል ያሉ አንዳንድ ተሳታፊዎች፣ አባ ማትያስ በፕትርክና በተሾሙበት ቀን አበ ብዙኃን ለመኾን ቃል የገቡበትን መሐላ በግላጭና በተደጋጋሚ ከመጣስ በላይ እብደት ባለመኖሩ በተጣለባቸው ታላቅ የቤተ ክርስቲያን ሓላፊነትና አባትነት ጉዳዩን በጥሞናና በተረጋጋ መንፈስ ሊመለከቱት እንደሚገባ ያሳስባሉ፡፡ የአጠቃላይ ጉባኤው መርሐ ግብር በመንበረ ፓትርያርክ ቅድስተ ቅዱሳን ማርያም ካህናት በጸሎተ ወንጌል ሲከፈት ፓትርያርኩ በንባብ ያሰሙት ቃልም‹‹ወንድምኽ ቢበድልኽ ምከረው፣ ይቅር በለው›› (ማቴ. ፲፰÷፲፭) የሚል ነበር – የማኅበረ አመራር ከፓትርያርኩ ጋራ የውይይት መርሐ ግብር እንዲያዝለት በተደጋጋሚ ባመለከተበት ኹኔታ ቀርቦ የተጠየቀበትና ምላሹ ተሰምቶ ጥፋተኝነቱ የተረጋገጠበት በደሉ ባይታወቅም!
MK on the 33rd gen assembly of Sebeka Gubae
(ፎቶ: ማኅበረ ቅዱሳን)
አባ ማትያስ የጠቀሱት ‹‹ገንዘብና የንብረት ቁጥጥር›› ጉዳይ በተመለከተ አጠቃላይ ጉባኤው ባለፈው ዓመታዊ ስብሰባው ያወጣው የጋራ ያአቋም መግለጫው፣ ‹‹እየተሠራበት ያለውን የገቢና የወጪ ሒሳብ በቤቱ የቁጥጥር አገልግሎት እያስመረመረ፣ በቤቱ ሞዴላሞዴሎች እየተገለገለ ማእከልንም በመጠበቅ አገልግሎቱን እንዲቀጥል›› ያስገነዘበበት ነበር፡፡
ማእከላዊነትን ጠብቆ ከማገልገል አንጻር፣ ማኅበሩ በ፲፱፻፺፬ ዓ.ም. ለሦስተኛ ጊዜ በቅዱስ ሲኖዶስ ተሻሽሎ በጸደቀለት መተዳደርያ ደንቡ መሠረት ከዋናው ማእከል አንሥቶ በየአህጉረ ስብከቱ በዘረጋው መዋቅሩ ከየአህጉረ ስብከቱ ሊቃነ ጳጳሳት ጋራ በመመካከርና መመሪያ በመቀበል የቤተ ክርስቲያንን ኹለንተናዊ አገልግሎት የሚደግፉ ተግባራትን እያከናወነ እንዳለ ገልጧል፡፡ በየጊዜው የአገልግሎት ዕቅዱን በማሳወቅ በየስድስት ወሩ የአገልግሎት የሥራ ዕቅድ አፈጻጸምና የሒሳብ ሪፖርት ለጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ያቀርባል፤ ተገቢውን መመሪያም ከመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽ/ቤቱ ይቀበላል፡፡
የገቢና የወጪ ሒሳብ እንቅስቃሴውን ስለመቆጣጠርም፣ ሒሳቡን በየጊዜው በውስጥ ኦዲተር እያስመረመረ ቆይቶ በየዓመቱ ደግሞ ዓለም አቀፍ ዕውቅና ባለው ሕጋዊ የውጭ ኦዲተር አስመርምሮ ለሚመለከታቸው የቤተ ክህነት አካላት እያቀረበ የሚሰጠውን መመሪያ ተከትሎ አገልግሎቱን በማከናወን ፳፫ ዓመታትን ማስቆጠሩን ገልጧል፡፡
የጠቅላይ ቤተ ክህነቱ የቁጥጥር አገልግሎት የማኅበሩን የገቢና ወጪ እንቅስቃሴ መቆጣጠር በፈለገበት ጊዜ ኹሉ ማኅበሩ በውስጥ ይኹን በውጭ ኦዲተር ያስመረመረውን ሒሳብ ማየት አልያም በማንኛውም ጊዜ በራሱ ኦዲተሮች ወይም የውጭ ኦዲተሮች አወዳድሮ በመመደብ ማስመርመር እንደሚችል አበክሮ የገለጸው ማኅበረ ቅዱሳን፣ ስንኳን የራሱን የሒሳብ አያያዝ ቀርቶ የቤተ ክርስቲያናችን የሒሳብ አሠራር በሙሉ ዘመናዊና ለኦዲት የሚመች እንዲኾን የሚያግዝ ማኅበር መኾኑን አረጋግጧል፡፡
ይኹንና የማኅበሩ የሒሳብ አሠራር ዘመናዊና በሕግ ተቀባይነት ያለው የኹለትዮሽ የሒሳብ አመዘጋገብ ሥርዐት(double entry accounting system) የሚከተል በመኾኑ፤ እጅግ ኋላ ቀር፣ በዘመናዊ የሒሳብ መዝገብ አያያዝ ሥርዐትም ተቀባይነት እንደሌለው ቋሚ ሲኖዶስና የጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ጽ/ቤት ሰሞኑን በቀረበላቸው የሦስት የበጀት ዓመታት የውጭ ኦዲት ምርመራ ሪፖርት አጋጣሚ ያመኑበትን የቤተ ክህነቱን የነጠላ የሒሳብ አመዘጋገብ ሥርዐት(single entry accounting system) ለመከተል እንደሚቸግረው በተደጋጋሚ አስተያየቱን አቅርቧል፡
በተመሳሳይ አኳኋን የጠቅላይ ቤተ ክህነቱ የገንዘብና ንብረት ገቢና ወጪ መመዝገቢያ ሰነዶች (ሞዴላሞዴሎች) ሥራ ላይ ማዋል የማኅበሩን የሒሳብ አሠራር ወደ ኋላ የሚጎትት እንደኾነ ነው የገለጸው፡፡ ማንኛውም ሕጋዊና ዘመናዊ የሒሳብ ምርመራ(ኦዲት) አሠራር በተለይም የውጭ ኦዲት የኹለትዮሽ የሒሳብ መዝገብ አያያዝ ሥርዐትን ተግባራዊነት በተሻሻለ ደረጃ የሚጠይቅ በመኾኑና በዚኽ የኦዲት ሥርዐት የቤተ ክህነቱ ሞዴላሞዴሎች ተቀባይነት እንደሌላቸው ሞያዊ አስተያየቱን ሰጥቷል፡፡
እስከ አኹን ባለው አሠራርና እውነታ ሞዴላሞዴሎቹን መጠቀም የቤተ ክርስቲያናችንን ገንዘብ፣ ሀብትና ንብረት ከብኩንነት፣ ከመዘረፍና ከመጭበርበር ማዳን እንዳልተቻለ ጥናታዊ ሪፖርቶች ያመለክታሉ፡፡ የሞዴላሞዴል አሠራር (የነጠላ የሒሳብ መዝገብ አያያዝ) ማንኛውንም ወጪ(ቋሚ ዕቃም ቢኾን) በወጪነት የሚመዘግብ እንጂ አንድ ተቋም ስላለው ሀብት በአግባቡ የሚያሳይ አይደለም፡፡ የፓትርያርኩንም ኾነ የቱኪና ጯኺ አማሳኞች የ‹‹ተቆጣጠሩት›› ዐዋጅ የሚረዳና ጥያቄያቸውን የሚመልስም አይደለም፡፡
በርግጥም ጥያቄው የማኅበሩን የገንዘብና ንብረት እንቅስቃሴ በአግባቡ ለመቆጣጠርና ተቋማዊ ለውጡን እንደ ጥርስና ከንፈር ተደጋግፎ የማራመድ ከኾነ፣ በማንኛውም የዘርፉን ሞያ በሚረዳ ወገን ዘንድ ተቀባይነት ያለው የመፍትሔ ሐሳብ በማኅበሩ ቀርቧል፡፡ ይኸውም ቁጥጥሩ፡-የማኅበር ሕገ ተፈጥሮን የተገነዘበ፣ ዓለም አቀፍ የፋይናንስ ሕግንና የቁጥጥር መርሕን የጠበቀ፣ ለቁጥጥር አመቺ የኾነና በሕግም ተቀባይነት ያላቸውን ዘመናዊ መንገዶች በመከተል ላይ ያተኩራል፡፡
ከማኅበር ሕገ ተፈጥሮ አኳያ፣ ማኅበረ ቅዱሳን ከቤተ ክህነት በሚመደብ በጀት እንደሚተዳደሩት መምሪያዎች ወይም ድርጅቶች ሳይኾን በበጎ ፈቃድ ክፍተቶችን ለመሙላት፣ አባቶችን በፍቅር ለመታዘዝና ለማገዝ የተሰባሰቡ አባላቱ ያቋቋሙት ራሱን የቻለ የቤተ ክርስቲያን አጋዥና ድጋፍ ሰጭ አካል በመኾኑ በአባላቱ መዋጮና በበጎ አድራጊዎች ርዳታ/ድጋፍ ነው የሚንቀሳቀሰው፡፡ የማኅበሩን ሒሳብ ሊያንቀሳቅስና ንብረቱን ሊያስተዳድር የሚችለው ጠቅላላ ጉባኤው የመረጠው የማኅበሩ አባልና አካል የኾነ ብቻ ነው፡፡
ተቆጣጣሪው አካል በዕለት ተዕለት የሥራ እንቅስቃሴው ውስጥ ከገባ ዓለም አቀፍ የቁጥጥር መርሕን ይጥሳል፡፡ ይኹንና ተቆጣጣሪው አካልቁጥጥሩን ሊያጠብቁለት የሚችሉ ሥርዐቶችን መዘርጋትና ተግባራቱን በአግባቡ መከታተል ብቻ የማኅበሩን አገልግሎት፣ የገንዘብና ንብረት እንቅስቃሴ ለመቆጣጠር ያስችለዋል፡፡
በአግባቡ ከተደራጀ ተቆጣጣሪ አካል የሚጠበቁት እኒኽ የሥርዐት ዝርጋታዎችና ክትትሎችም፡-
  • የኦዲት ሥራን ማሠራትና ከውጤቱ ተነሥቶ ተገቢውን አስተያየትና መመሪያ መስጠት፤
  • ዕቅዶችንና ሪፖርቶችን በመገምገም አስተያየት መስጠት፤
  • የገንዘብና ንብረት የገቢና የወጪ ሰነዶች ኅትመት በተቆጣጣሪነት መፍቀድ፤
  • የባንክ ሒሳብ እንዲከፈት ማኅበሩ ሲጠይቅ ለባንክ ማሳወቅ፤
  • የባንክ ፈራሚዎችን ስም ማኅበሩ ሲያቀርብ ለባንክ ማሳወቅ፤
  • በማኅበሩ ጠቅላላ ጉባኤያት ላይ እየተገኙ ሐሳብን መስጠት… የመሳሰሉት ናቸው፡፡
በማኅበሩ መተዳደርያ ደንብ መሠረት ማኅበሩ አገልግሎቱን የሚያቆመው፣ ትክክለኛነቱ በቅ/ሲኖዶስ በተረጋገጠ የጠቅላላ አባላቱ ውሳኔ አልያም በቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ ውሳኔ ሲኾን ያፈራው የማይንቀሳቀስ፣ ተንቀሳቃሽ የኾነና ጥሬ ገንዘብ በሙሉ ንብረትነቱና ሀብትነቱ ለኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን እንደኾነ ሰፍሯል፡፡ ማኅበሩ ከሚከተለው የሒሳብ አያያዝ ሥርዐት አኳያ የንብረት መሸጥና መለወጥ፣ ቱኪዎቹ እንደሚሉት ‹‹ማሸሽ›› ሳይኾን፤ በአጠቃላይ ንብረቱ ላይ የሚያመጣው ለውጥም የለም፤ የሚጨምረውና የሚቀንሰው ነገር በግልጽ በሚረዳ መንገድ በአሠራሩ የሚታይ ነውና፡፡፡፡
በአጠቃላይ የማኅበረ ቅዱሳን የማገልገል አቅም ከፍተኛ ደረጃ ላይ መድረሱ በቤተ ክርስቲያናችን ከፍተኛ አካል በታመነበትና የሚገኝበትን የዕድገት ደረጃ የሚመጥን፣ ለቤተ ክርስቲያን ኹለንተናዊ ዕድገት የሚጠቅም፣ የላቀና የተሻለ መንፈሳዊና ማኅበራዊ አገልግሎት ለማበርከት የሚያስችለው መዋቅራዊ አደረጃጀትና ምቹ ኹኔታ እንዲፈጠርለት እየተጠየቀ ባለበት ወቅት፣ የፓትርያርክ አባ ማትያስ ቅኝ ገዥ ነው፤ አጥፉትቅስቀሳ በእጅጉ አሳዛኝና በብርቱ ሊታሰብበት የሚያስፈልግ ነው፡፡
ደጉ ነገር! በዛሬው የአጠቃላይ ጉባኤው ዓመታዊ ስብሰባ በስፋት የተደመጠው የጠቅላይ ሥራ አስኪያጁ አጠቃላይ ሪፖርት፣ ይህን በአማሳኞች፣ ጎጠኞች፣ አድርብዬ ፖሊቲከኞችና የፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ ግንባር ቀደም መሪዎች ክፉ ምክር የተፈጠረ እልከኝነትና ምናልባትም የውጭ ኃይልን አጀንዳ በሌላ ገጽታ የሚገፋ የውክልና ጫና የወለደው ክሥ ከንቱ የሚያደርግ መኾኑ ነው፡፡
ጠቅላይ ሥራ አስኪያጁ በጥቅልና በዝርዝር ያቀረቧቸው የማኅበሩ የሥራ ፍሬዎች፣ አባ ማትያስ ማኅበሩን በቅኝ ገዥነት እንደወረፉት ሳይኾን፤ለታሪካዊት፣ ብሔራዊትና ሐዋርያዊት ቤተ ክርስቲያን ክብርና መብት መጠበቅ፤ ለትምህርተ ሃይማኖቷ፣ ሥርዐተ እምነቷና ክርስቲያናዊ ትውፊቷ ከትውልድ ወደ ትውልድ ሳይበረዝና ሳይከለስ መተላለፍ ትጉህ ዘኢይነውም ኾኖ ጥብቅና መቆሙን ነው፡፡
ከአጥቢያ ቤተ ክርስቲያን እስከ ልዩ ጽ/ቤት በተዘረጋው የአማሳኞች፣ ጎጠኞችና አድርብዬ ፖሊቲከኞች የሙስና ኤምፓየር የቤተ ክርስቲያንን‹‹ክብሯንና ገንዘቧን በቅኝ ገዥነት የወሰደ›› ሳይኾን፤ የሰበካ ጉባኤ ማደራጃ መምሪያ ሓላፊ ሊቀ ማእምራን ፋንታኹን ሙጬ የዘንድሮውን የአህጉረ ስብከት ውጤታማነት በገለጹበት ቋንቋ ‹‹የቤተ ክርስቲያናችን ምጣኔ ሀብት በዓለት ላይ የተመሠረተ ይኾን ዘንድ›› የአባላቱንና የበጎ አድራጊ ምእመናንን ጉልበት፣ ሞያና ገንዘብ አስተባብሮ ስኬታማ የልማት ሥራ የሠራ መኾኑን ነው፡፡
‹‹ካህናቱን ለጭቆናና ለመከራ ቀንበር የዳረገ›› ሳይኾን ከማንኛውም ክፍያ ነፃ በኾነና ያለስስት በልግስና በሚናኘው ሞያዊ አበርክቶው፣ ለተቀደሰው የክህነት ሞያቸው መከበርና ለኑሯቸው መመቻቸት የተጠበበና ከአማሳኞች፣ ጎጠኞችና ዐምባገነኖች ጋራ በየመድረኩ ፊት ለፊት የተሟገተ መኾኑን ነው፡፡
ፓትርያርኩም ኾነ መላው ኦርቶዶክሳዊ የሚጨነቅለት የኦርቶዶክሳውያን ቁጥር መቀነስ አሳስቦት፣ በንግግር ብዛት ሳይኾን በተግባር፣ ሚልዮኖችና መቶ ሺሕዎች የቃለ እግዚአብሔርን ማዕድ በሚቋደሱባቸው ሐዋርያዊ ጉዞዎችና በዘመናዊ ቴክኖሎጂ በታገዙ አውታሮች ስብከተ ወንጌልን ማስፋፋቱንና ማጠናከሩን ነው፡፡

No comments: