Thursday, January 17, 2013

‹‹አላሁ አእለም! ይቅርታ አንጠይቅም››
ሁለት ወቅታዊ ጉዳዮች
1. ከመለስ ሞት በኋላ መረጋጋት የተሳነው ኢህአዴግ ከበርካታ ችግሮች ጋር ፊት ለፊት ተፋጧል፡፡ ከችግሮቹ በከፊልም የሚከተሉት ይጠቀሳሉ፡፡ …በረከት ስምኦን የነበራው ተደማጭነት እየተሸረሸረ ነው፣ የበረከት ባለቤት የበረከትን መፅሃፍ ለመሸጥ (ገዥ ፍለጋ) በየተቋማቱ እየተንከራተቱ ነው፤ አዲሱ ለገሰ የተደማጭነት መስመሩን ‹‹ኢህአዴግን ለማጠናከር›› በሚል ምክንያት ይበልጥ እያደረጀ ነው፤ ደብረፅዮን ገ/ሚካኤል ከቀን ወደ ቀን በህወሓት ውስጥ ተሰሚነቱ እየጨመረ ነው፣ በእርግጥም ከድርጅቱ ከፍተኛ አመራሮች የአስጊ ህመም ችግር የሌለባቸው ተብለው የሚመደቡት ደብረፅዮን፣ አባይ ፀሀዬና ቴውድሮስ አድሃኖም ናቸው፣ አቦይ ስብሃት ነጋ ‹‹መፈንቅለ ፓርቲ›› በህወሓት ውስጥ ለማድረግ ቀን ከለሌት እያሴሩ ነው፣ ከሁለት ወርበኋላ የሚደረገው የኢህአዴግ ጠቀላላ ጉባኤ አዲስ ነገር ያስተናግዳል ተብሎ ይጠበቃል፤ ኦህዴድ በሹም ሽር ሊናጥ ነው፣ አለማየሁ አቱምሳ በሩቅ ምስራቅ ለሚከታተለው ህክምና እስከአሁን ያለውንም ሆነ በቀጣይ የሚያስፈልገውን ወጪውን እየሸፈነ ያለው ሼክ መሀመድ አላሙዲ ነው፤ ለምን? አለማየሁ የመንግስት ባለስልጣን ነው፣ በተጨማሪም ሆን ተብሎ በተሰጠው መርዝ ነው ታማሚ የሆነው የሚባለውን ወሬ ይዘን፣ ከዚህ ጀርባ ማን ነው ያለው? የሚል ጥያቄ መቀርቡ አይቀርም (የሰማሁት መረጃ ጆሮ ያቃጥላል) ግን ለምን? ኩማ ደመቅሳ መልካም አስተዳደር ባለማስፈንና ሙስናን መቆጣጠር ባለመቻል እየተወቀሰ ሲሆን፣ በተቃራኒው አባዱላ ገመዳ በኦህዴድ ውስጥ መረጋጋትን በማስፈንና ስራውን በብቃት በመወጣት በሚል ተመስግኗል፣ (የማኪያቬሊ ከፋፍለ ግዛ ማለት ይህ ይሆን?) በሚያዚያ ወር የሚደረገውን ምርጫ ተከትሎ የቱኒዝያንና የግብፅን መሰል ህዝባዊ አመፅ ይቀሰቀሳል በሚል አገዛዙ ፍርሃት አድሮበታል፣ 33ት ፓርቲዎች ነገ በምርጫው ላይ የሚኖራቸውን አቁም በሰማያዊ ፓርቲ ፅፈት ቤት ከጠዋቱ አራት ሰአት ላይ የፋ ያደርጋሉ (በእርግጥ የደረሱበት ውሳኔን ብግሌ ትክክል ነው ብዬ አምናለሁ፣ ከዚህ ውጪም ገዥው ፓርቲን ለድርድር የሚያስገድድ ዕድል የላቸውም)፣ በአማራ ክልል ደቡብ ጎንደር ኦስትሪያዊውን አገር ጎብኚ ማን ገደለው? ለምን ተገደለ? የደብረማርቆስ ማረሚያ ቤት ድራማስ በማን የተቀነባበረ ነው? ኃላፊነቱንስ ማን ነው የሚወስደው? የብሄራዊ መረጃና ደህንነት ኤጀንሲ ¬¬‹‹ለሽብር ድርጊት ሊውል ሲል ደረስኩበት›› በማለት ከተቀበረበት እንዳወጣው የነገረንን የጦር መሳሪያ ማነው የቀበረው? ይህ መሳሪያስ በእነማን የክስ መዝገብ ላይ ማስረጃ ሆኖ ሊቀርብ ነው የታቀደው? በቀጣይስ የቦንብ ፍንዳታ በየትኛው ከተማ፣ መቼ፣ ስንት ሰዓት ላይና በምን ሁኔታ ይደርስ ይሆን? …ይህኛው መንገድስ የት ድረስ ያስኬዳል? ‹‹አዲስ ታይምስ›› መፅሄትን ማፈኑስ ለምን አስፈለገ?
2. በሽብርተኝነት የተከሰሱትን የህዝብ ሙስሊም መሪዎችን በይቅርታ ለመፍታት መንግስት የማጭበርበሪያ ስልቱን እየተጠቀመ ነው፡፡ በዕለት ሀሙስ ጥር 2 ቀን 2005 ዓ.ም በፕሮፌሰር ኤፍሬም ይሳቅ ይመሩ ከነበሩት ሽማግሌዎች ውስጥ የተዘጋጀ ሶስት ሰዎች ያሉት አንድ ቡድን በቃሊቲ ማረሚያ ቤት ተገኝቶ ነበር፡፡ ከቡድኑ አባላት ፓስተር ዳንኤል እና ፕሮፌሰር አህመድ ዘካርያስ ለታሳሪዎቹ እንዲህ የሚል የማጭበርበሪያ መደራደሪያ አቅርቦ ነበር፡- ‹‹ጉዳያችሁ በፍርድ ቤት እየታየ ነው፤ ስለዚህም ክሱ አሁን ባለበት ደረጃ ሊቋረጥ አይችልም፡፡ እናም ክርክራችሁን አቋርጡና ጥፋተኛ ነን በሉ፣ ከዛም ፍርድ ቤቱ ከፈረደባችሁበኋላ ‹ይቅርታ› ጠይቃችሁ እናስፈታችኋለን›› ሆኖም የሙስሊሙ መሪዎች ‹‹ይህንን በጭራሽ አንቀበለውም፣ ጥፋተኛ ነኝም አንልም፣ አላሁ አእለም! ይቅርታ አንጠይቅም›› ሲሉ በድፍረትና በቁርጠኝነት መልሰውላቸው ወደ እስር ክፍላቸው ተመልሰዋል፡፡ በእርግጥም የኮሚቴው አባላት ትክክለኛ ውሳኔ ነው የወሰኑት፡፡ ምክንያቱም ይህ የሽምግልና ቡድን ቀንደኛ የስርአቱ ደጋፊ ሲሆን፣ መደራደሪያ ብሎ የሚያቀርበው ሁሉም ነገር የአገዛዙን የፖለቲካ ጥቅም የሚያስከብር ነውና፡፡ በድህረ ምርጫ 97 የታሰሩትን የቅንጅት አመራርንም በዚህ አይነት መልኩ መሸወዱ ይታወሳል፡፡(በነገራችን ላይ ሽማግሌዎቹ በተጠቀሰው ዕለት አንዱአለም አራጌን ጠርተው አናግረውታል፤ እስክንድር ነጋን ግን ዘለውታል፡፡ ለምን? ሌላው አስገራሚ ጉዳይ ደግሞ የሽማግሌ ቡድኑ ለሙስሊሙ መሪዎች ‹‹የመጣነው አንዱአለምን ፈልገን ነው፣ እናንተን እግረ መንገዳችንን ሰላም እንበላችሁ ብለን ነው›› ሲሏቸው፣ ለአንዱአለም ደግሞ የዚህን ግልባጭ ምክንያት ሰጥተውታል፡፡
http://www.ecadforum.com

No comments: