Saturday, August 27, 2016

ሕዝባዊ ተቃውሞው ኢኮኖሚውን እየጎዳው ነው!

August 27,2016

“ጥብቅ እርምጃ እንወስዳለን” ህወሃት
protest business
ህወሃት ለማመን ባይፈልግም ለአስር ወራት የዘለቀው የኦሮሞ ተቃውሞ በክልሉ የንግድና ሌሎች ተቋማት ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ አሳድሯል፡፡ ከክልሉ ወደሌሎች የሚደረገው የንግድ፣ የዕቃ፣ የገበያ፣ የሰው ኃይል፣ የገንዘብ፣ … ዝውውር በተቃውሞው ምክንያት በርካታ መስተጓጎሎች ደርሰውበታል፡፡ ከዚህም አልፎ አገሪቱ ለውጭ ንግድ በምታቀርበው ምርትና በምትሰበስበው ግብር ላይ የሚያስከትለውን ጫና ከክልሉ ስፋት አኳያ እጅግ ሰፊ እንደሚሆን ይገመታል፡፡
ከዚህ ጋር በተያያዘ በአማራው ክልል የተነሳው ተቃውሞ ችግሩን በይበልጥ እያባባሰው እንደሆነ ይነገራል፡፡ በተለይ የቤት ውስጥ አድማ በሚመታበት ጊዜ የዜጎች እንቅስቃሴ ይገታል፤ ንግድ ይቀዘቅዛል፣ በየዕለቱ ለመንግሥት የሚሰበሰበው ግብር (ቫት) ይቀንሳል፤ የንግድ ተቋማት ሽያጭና ትርፍ ይቀንሳል፤ በዚህ ምክንያት መንግሥት ከንግድ ተቋማት የሚሰበስበው የትርፍ ግብር ይቀንሳል፤ … እንዲህ እያለ ተጽዕኖው በራሱ እየተቀጣጠለ ሌሎች ችግሮችን በመውለድ ኢኮኖሚውን እስከ ማሽመድመድ ይደርሳል፡፡
bure4
ቡሬ ጎጃም
ነውጥ አልባ የትግል ስልት የሚከተለው የኦሮሞ ተቃውሞ በትግሉ መርኽ መሠረት ሰሞኑን በኢኮኖሚ ላይ ያነጣጠረ እርምጃዎችን እንደሚወስድ ይፋ አድርጓል፡፡ ጳጉሜን 1 ይጀመራል የተባለው እርምጃ በምን መልኩ እንደሚደረግ ዝርዝሩን እንደሚያሳውቁ አስተባባሪዎቹ ተናግረዋል፡፡ በየትኛውም መልኩ ይደረግ የኢኮኖሚ ተቃውሞ ሥርዓትን በማሽመድመድ ከፍተኛ ተጽዕኖ እንደሚያሳድር ይታወቃል፡፡ ከዚህ አንጻር በኢኮኖሚ ላይ ያነጣጠረው የኦሮሞ ተቃውሞ የህወሃትን ኮሮጆ አደጋ ላይ እንደሚጥለው ካሁኑ እየተገመተ ነው፡፡ ተጽዕኖው ደግሞ በአንድና በሁለት ሳምንታት ብቻ የሚቋጭ ሳይሆን የበርካታ ጊዜያት ተደራራቢ ውጤት ማስከተሉ የማይቀር ሐቅ እንደሆነ በሌሎች አገራት የተካሄዱት ተቃውሞዎች ምስክር ናቸው፡፡
በሙስና እና በዝርፊያ ለ25 ዓመታት ብቃቱን ያዳበረው ህወሃት/ኢህአዴግ በውጭ ንግድ (ኤክስፖርት) ከሚያገኘው የውጭ ምንዛሪ ይልቅ ዳያስፖራው ከሚልከው ዶላር የሚያገኘው እንደሚበልጥ የራሱ የገንዘብ መ/ቤት ይመሰክራል፡፡ ከ2003 ዓም በኋላ ባሉት አምስት ዓመታት የውጪ ንግዱን በእጥፍ አሳድጋለሁ ብሎ ቃል የገባው ህወሃት/ኢህአዴግ አሁንም ያኔ ከነበረበት የ3 ቢሊዮን ዶላር ገቢ አለመነቃነቁን አዲስ አድማስ ዘግቧል፡፡ ከዚህ ይልቅ ግን በዓመት ከዳያስፖራው የሚያገኘው የውጭ ምንዛሪ የዛሬ አራት ዓመት 2.5ቢሊዮን ዶላር የነበረው በአሁኑ ጊዜ በዓመት 4ቢሊዮን ዶላር መድረሱ አብሮ ተዘግቧል፡፡ ከዚህ አንጻር ቀጣዩ የኢኮኖሚ ተቃውሞ በዚህ ዙሪያ ያጠነጠነ ቢሆን የህወሃትን አከርካሪ በመምታትና ዕድሜውን ወደማሳጠር በቶሎ ይደረሳል በማለት አስተያየት ሰጪዎች ይናገራሉ፡፡
እንደ አዲስ አድማስ ዘገባ ከሆነ ከአራት አመት በፊት፣ የኢትዮጵያ ጠቅላላ የውጭ እዳ ወደ 9 ቢሊዮን ገደማ ሲሆን በአሁኑ ጊዜ የዕዳው ክምችት 20.6 ቢሊዮን ዶላር ደርሷል፡፡ ለዕዳ ክፍያ የውጭ ምንዛሬ የግድ አስፈላጊ በመሆኑ ዕቃ ከውጭ ለማስመጣት የሚሰጠውን የዱቤ ፍቃድ እንዲቀንስ በማድረግ ወይም ረጅም ጊዜ እንዲወስድ በማድረግ የራሱን አሉታዊ ተጽዕኖ በኢኮኖሚው ላይ ያሳድራል፡፡
ከዚህ ጋር በተያያዘ ባለፈው እሁድ በአዲስ አበባ የተጠራው ተቃውሞ ሰልፍ አገዛዙን ለከፍተኛ የገንዘብ ወጪ እንደዳረገው ተሰምቷል፡፡ ቁጥሩን ለማረጋገጥ ባይቻልም እስከ 30 እና 40ሺህ ፖሊስ፣ ወታደሮችንና የስለላ ሰዎችን ያሰማራው ህወሃት ለእነዚህ ሁሉ ከአምስት መቶ ብር ጀምሮ የውሎ አበል ከፍሏል፡፡ ይኽም እስከ 10ሚሊዮን ብር ለሚሆን ወጪ እንደዳረገው ስሌቱ ያሳያል፡፡ የአዲስ አበባው ሰልፍ በተለያዩ ምክንያቶች እንደታሰበው ባይሳካም atnafበሥርዓቱ ላይ ጉዳት ከማስከተል አንጻር ዓላማው ግቡን እንደመታ ይነገራል፡፡
ተመሳሳይ የተቃውሞ ሰልፍ ይካሄዳል በሚል ፍርሃት ውስጥ የገባው ህወሃት አዲስ አበባ ላይ ከፍተኛ የቁጥጥር ሸክም መጫኑ ነዋሪዎች ይመሰክራሉ፡፡ በአማራ ክልል የተነሣው ብረት አከል ተቃውሞ ወደ አዲስ አበባ ይዛመታል በሚል ፍርሃቻ ሆቴሎች ቁጥጥሩ ጠብቆባቸዋል፡፡ የዞን 9 ጦማሪ የሆነው አጥናፍ ብርሃኔ በትዊተር በለቀቀው መልዕክት “ከአማራ ክልል ወደ አዲስ አበባ መጥቶ የሚያርፍ እንግዳ ካለ በ24 ሰአት ውስጥ ለፖሊስ እንዲያሳውቁ ትእዛዝ ለየሆቴሎቹ ተላልፏል” በማለት ትላንት መልዕክት አስተላልፎ ነበር፡፡
በየማኅበራዊ ድረገጹ ላይ አፍቃሪ ህወሃቶች አሠራሩ በቀድሞ አገዛዞችም ሲሠራበት የኖረና የተለመደ ነው ብለው ለማስተባበል ቢፈልጉም ሁኔታው ግን ከዚያ የተለየ ነው፡፡ በእርግጥ ሆቴሎች እንግዶቻቸውን ለፖሊስ ማሳወቅ የተለመደ አሠራር ነው የሚሉ አስተያየት ሰጪዎች  የአሁኑ ትዕዛዝ ግን ለየት ያለ እንደሆነ ይናገራሉ፡፡ በአገር ውስጥ የሚያሰጋ ነገር ሲከሰት ህወሃት ተመሳሳይ ትዕዛዝ ሲያስተላልፍ መቆየቱን የሚናገሩ ወገኖች ከዚህ በፊት በኦነግ ሰዎች ላይ ተመሳሳይ ፍርሃቻ በነበረበት ጊዜ ትዕዛዙ መተላለፉን ያስታውሳሉ፡፡ ከዚያም በሶማሌ ክልል ተመሳሳይ አለመረጋጋት በነበረበት ወቅት ከክልሉ የሚመጡ ተስተናጋጆችን ወዲያውኑ ሪፖርት እንዲያደርጉ መታዘዙን የሆቴል ባለቤቶች ይናገራሉ፡፡ ያሁኑ ደግሞ ከአማራው ክልል በሚመጡ ላይ መደረጉ በክልሉ የተነሳው ተቃውሞ በህወሃት ላይ ያስከተለውን ተጽዕኖ ያሳያል፡፡
ethflagበተያያዘ ዜና ለዘመናት የኦሮሞንና የአማራን ወገኖች በመከፋፈል እርስበርስ እንዲናቆሩ በሰፊው የሰራው ህወሃት የሁለቱ ጥምረት ኅልውናውን አደጋ ላይ መጣሉን የራሱ ሰዎች መናገራቸውን ባለፈውጎልጉል ዘግቦ ነበር፡፡ እነ አባይ ጸሃዬ ወደ አሜሪካ መጥተው ጥምረቱ ስጋት እንደሆነባቸው ለጌቶቻቸው አስረድተዋል፡፡ አሁንም ይህ ጥምረት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መምጣቱ በሚደረጉት ሰልፎች እና በየማኅበራዊ ድረገጾች ላይ በሚጻፉት እየተንጸባረቀ ነው፡፡
በኦሮሚያ ከህጻናት እስከ አዛውንት በደም ኩሬ ሲጠምቅ የነበረው ህወሃት ሰሞኑን እየከረረ የመጣውን ተቃውሞ ለማክሸፍ “ጥብቅ እርምጃ” እወስዳለሁ ብሏል፡፡ ሲገድል፣ ሲረሽን፣ ሲያስር፣ ሲያሰቃይ፣ … ወዘተ የቆየው ህወሃት አሁን ከዚህ የተለየ ምን “ጥብቅ እርምጃ” እንደሚወስድ ግልጽ አላደረገም፡፡ ስቃይና ሞት በተለያየ መልኩ ሲፈጸምበት የኖረ ሕዝብ ከዚህ በላይ ምንም እንደማይመጣበት በማወቅ ትግሉን አጠናክሮ እንደሚቀጥል ከአስተባባሪዎችና ከአገር ቤት ከሚሰሙት ድምጾች ለመረዳት ይቻላል፡፡
በመለስ ሞት ፊታቸውን ያዞሩት ምዕራባውያኑ የህወሃት አንጋሾች ይህንን የህወሃት አካሄድ ካለመደገፍ ጀምሮ እስከ ጀርባ መስጠት እያደረሳቸው መሆኑን መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡

No comments: