Sunday, July 17, 2016

የዴሞከራሲና የሰብዓዊ መብት ጥያቄን በጠብ-መንጃ አፈሙዝ ማቆም አይቻልም (ከሰማያዊ ፓርቲ የተሰጠ መግለጫ)

July17,2106
በአሁኑ ሰዓት ኢትዮጵያ ከመቼውም ጊዜ በላይ በከፋ የፖለቲካ፣ ማሕበራዊና ኢኮኖሚያዊ ምስቅልቅል ውስጥ ትገኛለች፡፡ ለሁሉም የሕዝብ ጥያቄ ምላሹ የኃይል እርምጃ የሆነው አገዛዙ መግደል፣ ማፈናቀል፣ ማሰደድ እንዲሁም የእርስ በርስ ግጭቶችን መቀስቀስ ዋና ተግባሩ አድርጐታል፡፡ በተለያዩ የሀገራችን አካባቢዎች የሚነሱ የሕዝብ ጥያቄዎችን ተገቢውን ምላሽ መስጠት ሲገባው የኃይል እርምጃ መውሰዱ አገዛዙ ወደለየለት አምባገነንነት ማምራቱን ያሳያል፡፡Semayawi party on Gondar Protest
በጐንደር ከተማ ከማንነት ጥያቄ ጋር በተያያዘ የተነሳው ተቃውሞ እንዲሁም በአዲስ አበባ ን/ስ/ላፍቶ ሀና ማሪያም ቀርሳ ኮንቶማ አከባቢ የተፈጠረው ግጭት አገዛዙ የፈጠረው ጭቆናና አፈና ውጤት መሆኑን እንገነዘባለን፡፡
በጐንደር ከተማ እና በአዲስ አበባ ን/ስ/ላፍቶ ሀና ማሪያም ቀርሳ ኮንቶማ ነዎሪዎች ላይ የተወሰደው እርምጃ ኃላፊነት የጐደለውና በማናለብኘነት የተወሰደ ነው፡፡ በተጨማሪም የሕዝቡን ጥያቄ “የሌላ ኃይል ፍላጐት አስፈፃሚዎች ያነሳሱት ነው” በማለት መግለፁ ለሕዝብ ያለውን ንቀት የሚያሳይ ሆኖ አግኝተነዋል፡፡
በመሆኑም አገዛዙ በንፁሃን ዜጐች ላይ የወሰደውን ኃላፊነት የጐደለው እርምጃ እያወገዝን የኢትዮጵያ ሕዝብ ልዩነቱን ወደ ጐን በመተው ለዚህ ምስቅልቅል ምክንያት የሆነውን አፋኝ ስርዓት ለማስወገድ ከመቼውም ጊዜ በላይ ቆርጦ እንዲነሳና ከሰማያዊ ፓርቲ ጐን እንዲሰለፉ ጥሪያችንን እናስተላልፋለን፡፡
ኢትዮጵያ በክብር ለዘላለም ትኑር
ሀምሌ 8 ቀን 2ዐዐ8 ዓ.ም

No comments: