Thursday, October 1, 2015

ከመከላከያ ሰራዊት ውስጥ የስንብት ጥያቄ የሚያቀርቡ መኮንኖች ቁጥር እያሻቀበ ነው

October 1,2015
መቶ በመቶ ለማለት በሚያስደፍር ሁኔታ ከአንድ አካባቢ በወጡ የህወሓት አባላት ድኩማን ወታደራዊ አዛዦች ብቻ ቁጥጥር ስር ሆኖ በከፋ አስተዳደራዊ በደል እየማቀቀ በዘር ሸለቆ ውስጥ የሚገኘው ብዙኃኑ የመከላከያ ሰራዊት የሰባት ዓመታት አገልግሎት የኮንትራት ጊዜውን የጨረሰው የስንብት ጥያቄ ያዘሉ ደብዳቤዎችን ያለማቋረጥ እያስገባ በየእርከኑ የሚገኙ የመከላከያ የአስተዳደር ቢሮዎች በማመልከቻ ማዕበል ክፉኛ እየተመቱ የሚገኙ ሲሆን የአገልግሎት ጊዜው አልሞላ ብሎት የስንብት ደብዳቤ ማስገባት ያልቻለው የሰራዊቱ አባል ደግሞ የሰቀቀን ኑሮውን ለማሳጠር በራሱ እርምጃ እየወሰደ ያለምንም ፋታ እየከዳ ነው ሲል የአርበኞች ግንቦት 7 ድምፅ ዘግቧል::
(Photo File)
(Photo File)















ድኩማኖቹ ህወሓታዊያን የመከላከያ ሰራዊቱ አዛዦች የአገልግሎት ጊዜ ኮንትራታቸውን ጨርሰው የስንብት ደብዳቤ ለሚያስገቡት በስርዓቱ የተንገሸገሹ እና በእጅጉ ተማረው ተስፋ የቆረጡ ስፍር ቁጥር የሌላቸው የሰራዊቱ አባላት “ከመከላከያ ሰራዊቱ ፈፅሞ መልቀቅ አይቻልም…” የሚል አሉታዊና ድፍን ያለ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡
በተጨማሪም ድኩማኖቹ ወታደራዊ አዛዦች የአገልግሎት ዘመኑን የጨረሰ ማንኛውም የመከላከያ ሰራዊት አባል በአሁኑ ሰዓት የስንብት ጥያቄ የማቅረብ መብት እንደሌለውና አሰናብቱኝ ብሎ በሚያመለክት ላይ እርምጃ የሚወስዱ መሆናቸውን ጠንከር ያለ መመሪያ አስተላልፈዋል፡፡
ከየማሰልጠኛው ተመርቀው በየጊዜው ሰራዊቱን የሚቀላቀሉ አዳዲስ አባላት ብዙም ሳይቆዩ ስለሚከዱ “ነባሩ ሰራዊት” ከተሰናበተ በእነሱ ላይ ቅንጣት ታክል እምነት ስለሌላቸው በአገዛዙ ላይ የከፋ አደጋ ሊከሰት እንደሚችል በማብራራት በማሳመን ለማባበል እየሞከሩ ይገኛሉ፡፡
የህወሓት አገዛዝ በየጊዜው ከመከላከያ ሰራዊቱ የሚከዱትን አባላት ከየተሸሸጉበት አድኖ የመያዝ ሰፊ እንቅስቃሴ አድርጎ ሳይሳካለት ቀርቷል፡፡
በየጊዜው ያለምንም ፋታ የሚከዱ የሰራዊቱ አባላት ወደየ ትውልድ ቀያቸው አይደለም የሚመለሱት፤ ገሚሶቹ ከነትጥቃቸው በረሃ ወርደው ይሸፍታሉ፤ አብዛኞቹ የነፃነት ትግሉን ይቀላቀላሉ፤ ቀሪዎቹ ደግሞ ድምበር ተሻግረው እግራቸው ወደመራቸው ይሰደዳሉ፡፡
በአጠቃላይ አሁን እጅግ በጣም በርካታ አባላት ላነሱት የስንብት ጥያቄ የተሰጠውን “አይቻልም” የሚል ድኩማን ህወሓታዊ ወታደራዊ አዛዦች ምላሽ ተከትሎ በመከላከያ ሰራዊቱ ውስጥ ከዳር እስከ ዳር ሰፍኖ የቆየውን ውጥረትና አለመተማመን ከጫፍ አድርሶት አገዛዙ ሊቆጣጠረው ከሚችለው በላይ የሆነ ከባድ አደጋ እያንዣበበ ይገኛል፡፡

No comments: