Friday, April 10, 2015

የመን ለሚገኙ ወገኖቻችን እንድረስላቸው!

April 10,2015
pg7-logoየመን የሚገኙ በመቶ ሺዎች የሚገመቱ ኢትዮጵያዊያን አደጋ ላይ ናቸው። ኢትዮጵያ ውስጥ ካለው የመብት አፈና፣ ሥራ አጥነት፣ ችጋርና ተስፋ ማጣት ለመሸሽ የራሳቸውንና የዘመዶቻቸውን ጥሪት አሟጠው ወደ መካከለኛው ምሥራቅ አገሮች ለሚሰደዱ ወገኖቻችን የመን መሸጋገሪያቸው ናት። ዛሬ የህወሓት ወዳጅ የሆኑም ያልሆኑም የየመን አምባገነን ገዢዎች እርስ በርሳቸው እየተላለቁ፤ ከምድር እሳት እየነደባት መሆኑ ሳያንስ ከሰማይም እሳት እየዘነበባት ነው።
እንኳን አሁንና በሰላሙም ጊዜ የመን ለኢትዮጵያዊያን ምቹ አልነበረችም። በበረሀ ጉዞ የዛሉ እግሮች፤ ከአቅማቸው በላይ በጫኑ ታንኳዎች ባህር በመሻገር የታወኩ ኢትዮጵያዊያን ስደተኞች የመን ጠረፍ ላይ የሚጠብቃቸው ተጨማሪ እንግልት፣ ስቃይና መደፈር ነበር። የመን የሚገኙ ኢትዮጵያዊያን ሕይወት እኛ ኢትዮጵያዊያን እንደ አገር የደረስበት አሳፋሪ ደረጃ መገለጫ ሆኖ ቆይቷል። በየመን፣ ወገኖቻችን ተደብድበዋል፤ አካላቸው በስለት ተዘልዝሏል፤ ሴቶች ብቻ ሳይሆን ወንዶችም ተደፍረዋል፤ ጓዳችን አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ ታፍኖ ለህወሓት ተላልፎ ተሰጥቶብናል። አሁን የመን እየነደደች ነው።
እጅግ የሚያሳስበን ቁጥራቸው ከመቶ ሺህ ይበልጣሉ ተብሎ የሚታሰበው በአሁኑ ሰዓት የመን ውስጥ የሚገኙ ወገኖቻችን እጣ ፈንታ ነው። የሌሎች አገሮች ዜጎች መንግሥቶቻቸው ደርሰውላቸው ከእቶኑ አውጥተዋቸዋለሁ። የኛ ወገኖች ግን የሚደርስላቸው መንግሥት የላቸውም።
ወገኖቻችን በዚህ ጭንቅ ውስጥ ባሉበት ሰዓት የህወሓት አገዛዝ ያንዣበበባቸው አደጋ የሚያባብሱ ተግባራትን እየወሰደ ነው። ሌሎች አገሮች በየመን ጉዳይ ላይ ያላቸውን አቋም በይፋ ከማሳወቃቸው በፊት ዜጎቻቸውን አስወጥተዋል። ህወሓት ግን ወገኖቻችን ለማዳን አንዳችም ጥረት ሳያደረግ ኃላፊነት በጎደለው መንገድ አንዱን ተፋላሚ ወገን በይፋ በመደገፍ በመቶ ሺህ የሚገመቱ ወገኖቻችን ከወላፈኑ ወደ እቶኑ ወርዉሯቸዋል። ገንዘብ የሚያገኝበት ከሆነ ወያኔ ወታደር ከመላክም ወደ ኋላ አይልም። እናም ለወገኖቻችን ካለ እኛ ማን አላቸው?
ስለ የመን ብቻ ሳይሆን ስለ ስደተኝነት በተነሳ ቁጥር አዕምሮዓችን ውስጥ የሚጉላላ ቁም ነገር አለ። እኛ ኢትዮጵያዊያን አገራችን ውስጥ ያለውን ሥርዓት ለውጠን፤ በምንወዳት አገራችን ውስጥ በክብር እንደመኖር እስመቼ አገራችንን ለህወሓት ወንበዴዎች ትተን እየሸሸን እንኖራለን? ስቃይና ሞት ተሸሽቶም አልተመለጠም። ሞት ኢትዮጵያዊያንን ኬንያ፣ ዩጋንዳ፣ ሱዳን፣ ሰሀራ በረሃ፣ ሜዴትራኒያን ባህር፣ ቀይ ባህር፣ ሳውዲ አረቢያ እና የመን ውስጥ መሽጎ ይጠብቀናል። ኢትዮጵያዊያን በስደት ላይ እያለን የከፈልነው ዋጋ ተጠራቅሞ በአገራችን ውስጥ ለሥርዓት ለውጥ ውሎ ቢሆን ኖሮ ወያኔ አስወግደን በውሸት ሳይሆን በእውነት የበለፀገች ኢትዮጵያን መገንባት አንችልም ነበርን? እውን ወያኔ ከስልጣን ማስወገድ በስደት ምክንያት ያጣነውን ያህል ነብስና በስደት ላይ እየተቀበልነው ያለ ፍዳ ያህል ያስከፍላልን? ለምን በሀገራችንና በራሳችን ላይ እምነት አጣን? ይህ አፋጣኝ እርምት የሚሻ አብይ ጉዳይ ነው።
አርበኞች ግንቦት 7:የአንድነትና ዲሞክራሲ ንቅናቄ የመን ለሚገኙ ወገኖቻችን ለመድረስ የተቻለንን ሁሉ እንድናደርግ ጥሪ ያደርጋል። ይህ ሥራ እየተሠራም ትኩረታችን ለዚህ ሁሉ መከራ የዳረገንን የህወሓት አምባገነን አገዛዝን ለማስወገድ በርትተን እንታገል ይላል።
ድል ለኢትዮጵያ ሕዝብ!

No comments: