Tuesday, March 24, 2015

የጦማርያንና ጋዜጠኞቹ አቤቱታዎች ውድቅ ተደረጉ

March 24,2015
በእነ ሶልያና ሽመልስ የክስ መዝገብ የሽብር ክስ ተመስርቶባቸው የሚገኙት የዞን ዘጠኝ ጦማርያንና ሦስቱ ወዳጅ ጋዜጠኞች መጋቢት 15/2007 ዓ.ም ከሰዓት 8፡00 የፌደራሉ ከፍተኛው ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 19ኛ ወንጀል ችሎት ቀርበዋል፡፡
 
መዝገቡ ተቀጥሮ የነበረው ተከሳሾች ባቀረቧቸው ሁለት አቤቱታዎች ላይ ፍርድ ቤቱ መርምሮ ብይን ለመስጠት ነበር፡፡ በዚህም አንደኛ አቃቤ ህግ በተከሳሾች ላይ አለኝ ካለው ማስረጃ ዝርዝር ውስጥ 12 የኦዲዮ-ቪዲዮ ሲዲዎች አያይዞ ያቀረበ ቢሆንም፣ ሲዲዎቹ ለተከሳሾች እስካሁን ባለመድረሳቸው ተከሳሾች የቀረበባቸውን ማስረጃ ተመልክተው መልስ ለማዘጋጀት ሲዲዎቹ እንዲሰጧቸው ያቀረቡት አቤቱታ ሲሆን፣ ሁለተኛው ጉዳይ ደግሞ 4ኛ ተከሳሽ ማህሌት ፋንታሁን እና 9ኛ ተከሳሽ ኤዶም ካሳዬ በቃሊቲ እስር ቤት አስተዳደር ላይ ከጎብኝዎቻቸው መከልከል ጋር በተያያዘ አቅርበውት በነበረው አቤቱታ ላይ ብይን መስጠት ነበር፡፡ ፍርድ ቤቱም ሁለቱንም አቤቱታዎች ውድቅ አድርጓል፡፡

የሲዲ ማስረጃውን በተመለከተ አቃቤ ህግ ማስረጃዎችን ኢግዚቪት ብሎ ስላስመዘገበ አሁን በዚህ ደረጃ ሲዲዎቹ ለተከሳሾች የሚደርሱበት አግባብ የለም በሚል ፍርድ ቤቱ የተከሳሾችን አቤቱታ እንዳልተቀበለው ገልጹዋል፡፡ በመሆኑም ተከሳሾች ማስረጃ በመስማት ሂደት ወቅት ማስረጃዎችን እየተመለከቱ መልስ እንዲሰጡ እንጂ ቀድሞ እጃቸው የሚደርስበት አሰራር የለም ብሏል ፍርድ ቤቱ፡፡


ፍርድ ቤቱ የቃሊቲ እስር ቤት አስተዳደር ላይ በሁለቱ ሴት ተከሳሾች የቀረበውን አቤቱታም ሳይቀበለው ቀርቷል፡፡ በተከሳሾች የቀረበውን አቤቱታ እና የእስር ቤቱ አስተዳደር የሰጠውን መልስ መመልከቱን የገለጸው ፍርድ ቤቱ፣ ‹‹ለቀረበው አቤቱታ ማስረጃ ተያይዞ ያልቀረበ በመሆኑ…›› በሚል አቤቱታውን ቅድቅ አድርጓል፡፡ ጦማርያኑ እና ጋዜጠኞች ላይ የአቃቤ ህግ ምስክሮች ከሰኞ መጋቢት 21/2007 ጀምሮ ለሦሰት ቀናት ይሰማሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡

No comments: